ለስንዴ ግዥ የሚወጣውን 700 ሚሊዬን ዶላር ለማስቀረት እየተሠራ ነው

የግብርና ሚኒስቴር የቆላ ስንዴን በመስኖ የማምረት ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ መቀጠል ከተቻለ ለስንዴ ግዥ የሚወጣውን በዓመት 700 ሚሊዬን ዶላር ማስቀረት እንደሚቻል አስታወቀ።

የቆላ ስንዴን በመስኖ የማምረት ሂደት ላይ ጠንክረን ከሰራንበት ከውጭ ገበያ ለምናስገባው ስንዴ ብቻ የምናወጣውን 700 ሚሊዬን ዶላር መቆጠብ እንደምንችል እና የስንዴ ምርቱ እንደተነሳ የጥጥ እና አኩሪ አተር ዓይነት አዝዕርትን በተመሳሳይ ቦታ ላይ በመዝራት በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት የምንፈልገውን እደገት ማምጣት እንችላለን ሲሉ በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር)ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ አጠቃላይ የአገሪቱ የስንዴ ምርት በደጋው እና በወይና ደጋው አካባቢ ተወስኖ የቆየ እንደነበርም ጠቁመዋል፤ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት በዋቢ ሸበሌ፣ በሱማሌ ክልል፣ በአፋር እና አዋሽ ተፋሰስ ባሉ ቆላማ ቦታዎች ማምረት እንደሚቻል በመረጋገጡ በሰፋፊ ቦታዎች ላይ የተጀመረው የቆላ ስንዴን በመስኖ የማምረት ሂደት ውጤታማ ከሆነ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ አገራት መላክ መጀመር ትችላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎት 65 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል። ከዚህ ውስጥ 48 ሚሊዮን ኩንታል በአገር ውስጥ ምርት ሲሸፈን ቀሪው ከውጭ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ቀሪውን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማሟላት ከ600-700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምታወጣ ተገልጿል።
ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት የፖሊሲ ድጋፍ እንደሚሰጥ፣ ግብርናን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ከ35 ሽህ በላይ ታብሌቶች ለግብርና ባለሙያዎች

እንደሚተላለፉ፣ሆርቲካልቸር በልዩ ሁኔታ እንደሚሰራበት እና የኢንዱስትሪ ተቋማት፣ አምራቾች እና የመንግስት አካላት በጋራ በመስራት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ሚኒሰትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስቴር በግብርና ምርት የገበያ ትስስር ላይ ከግብርና ምርት ግብዓት ግብይት ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዳስፈለገ ጠቅሰው የመሬት ፖሊሲ፣የመሬት አጠቃቀም፣የግብዓት አቅርቦት፣ የምርት ግብይት፣ የቴክኖሎጂ እና የውሃ አጠቃቀማችን የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች በመሆናቸው በቀጣይ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ግብርናን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።
የመሬት የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና አስተዳደር፣ የቴክኖሎጂ ግብዓት እና አቅርቦት፣ የመስኖ ልማት እና የውሃ አጠቃቀም፣ የምርት ግብይት፣ የግል ዘርፍ ተሳትፎ እና ውጤታማነት ተቋማዊ አሰራርና ስርዓት ላይ ማሻሻያ የሚደረግባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።

ገበያ መር የግብርና ልማት ላይ በማተኮር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ የሚያመጡ ሰብሎች ላይ መስራት ስለሚያሰፈልግ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ተሻሽሏል በማለት ገልጸዋል። ግብር እንደ ቢዝነስ እንዲታሰብ፣ አዋጭ እንዲሆን፣ የስራ እድል እንዲፈጥር፣ የግሉን ሴክተር እንዲያሣትፍ የአገር ኢኮኖሚ እንዲያሳድግ እንዲሁም በአጠቃላይ ስርዓት እንዲዘረጋለት ታስቦ የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል ብለዋል።

ከውጭ ከሚገባው ስንዴ ዩክሬን ከ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ በማቅረብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ግዥ ከ760 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚሆን እና ኹለተኛዋ ከፍተኛ የስንዴ ምርት አቅራቢ አሜሪካ ስትሆን ከ287 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ለኢትዮጵያ በማቅረብ ከ108 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች። ሩሲያ ከ278 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ በማቅረብ ሦስተኛዋ ስትሆን 79 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፈል መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here