ሕግ አወጣጥ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት – ክፍል 1

0
1041

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።

በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት)
1. የኢትዮጵያን ሕግ የማዘመን ታሪክ ፈር ቀዳጅ ኩነት
መንደርደሪያ – የኢፌዴሪ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር እና የፌደራል ምክር ቤቶቹ
የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ሀገሪቷን በብሔርና ቋንቋ ላይ የተመሠረተ ያልተማከለ ስርዓትን “በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መልካም ፍቃድ” መስርቷል። ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችም ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል የሚደርስ ሰፊ የቡድን መብት አጎናጽፏቸዋል። ፌደሬሽኑ መጀመሪያ ሲመሰረት ኹለት ራስ ገዝ ከተሞች እና ዘጠኝ ክልሎችን ያካተተ ነበር። በቅርቡ የተካሄደ ሕዝበ ውሳኔን ተከትሎ ሲዳማ 10ኛ ክልል ሆና ፌደሬሽኑን ከመቀላቀሏ ባሻገር 11 የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልል አባል ዞኖች ወደ ክልል ከፍ ለማለት በምክር ቤቶቻቸው አጽድቀው፣ ሕዝበ ውሳኔ የሚያካሂዱበት ቀን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ክልሎች የሚዋቀሩት “በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ” ተመስርቶ እንደሚሆን ሕገ መንግሥቱ ደንግጓል። ከክልሎች ዝቅ ብለው የምናገኛቸው አስተዳደርያዊ እርከኖች ዞን እና ወረዳ ይሰኛሉ።

ክልሎች የራሳቸውን ክልላዊ ሕገ መንግሥት የማውጣጥ፣ ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ፍ/ቤቶች ያካተተ ክልላዊ አስተዳደር አቋቁመው የክልላቸውን ጉዳይ የሚያስተዳድሩ ሲሆን በአገር ዐቀፍ ጉዳዮች ደግሞ በማዕከላዊ መንግሥቱ የሚወከሉባቸው የተለያዩ ተቋማት ተመስርተዋል። ከእነዚህ ዋነኞች ኹለቱ የፌደራል ምክር ቤቶች – የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች – ናቸው።

ሀ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ጉዳዮችን – የሀገሪቷን አጠቃላይ ፖሊሲዮች፣ የውጪ ግንኙነቶችን፣ የዜግነት ጉዳዮችን፣ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነቶችን፣ የወንጀል ሕጎችን ብሎም የሀገር መከላከያ ሠራዊት አደራጃጀቶች – የመሳሰሉት ላይ በመንግሥት የሚወጡ ፖሊሲዮች የማጽደቅ ብሎም ሕግ የማውጣጥ ሥልጣኑ አለው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በሚካሔድ የሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ ይመረጣሉ። የመንግሥት አወቃቀሩ ፓርላሜንታዊ እንደመሆኑ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ያነኘ የፖለቲካ ፓርቲ መንግሥት፣ አስፈጻሚውን አካል መስርቶ ሀገሪቷን ያስተዳድራል። የአስፋጻሚው የበላይ አካል የአብላጫ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ በሚያቀርበውና በምክር ቤቱ የሚሾም ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናል። ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚቀርቡለትን ሚንስትሮች ይሾማል።
የምክር ቤቱ አባላት ተጠያቂነታቸው ለሕገ መንግሥቱ፣ ለመረጠጣቸው ሕዝብ እና ለሕሊናቸው ብቻ መሆኑን በመርሆ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ አስቀምጧል። ምክር ቤቱ ከ550 ያልበለጡ አባላት ይኖሩታል።

ምክር ቤቱ እንደየትኛውም ፓርላማ ሦስት ኃላፊነቶች አሉበት – ሕግ የማውጣጥ፣ አስፈጻሚውን የመከታተል እና የውክልና።

ለ) የፌደሬሽን ምክር ቤት
ኹለተኛው ምክር ቤት የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። በተለመደው የፌደራል ስርዓት ኹለተኛው ምክር ቤት የክልሎች ውክልና ያለው ሲሆን የፌደሬሽን ምክር ቤት ግን ከዚህ በተለየ አባላቱ የክልሎች ሳይሆኑ የብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ወኪል ናቸው። እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝብ አንድ ተወካይ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ባላቸው አንድ ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ተጨማሪ አንድ አንድ ተወካይ ይኖራቸዋል። ተወካዮቹ የክልል ምክር ቤቶች በሚያዘጋጁት ቀጥተኛ ምርጫ ሊመረጡ ወይም በምክር ቤቱ በቀጥታ ሊላኩ ይችላሉ። ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ጀምሮ ባለው አሠራር ተወካዮቹ በቀጥታ ከክልል ምክር ቤቶች ሲላኩ ቆይተዋል።

ሕገ መንግሥቱ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦችን “ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” በሚል በጥቅሉ የወል ትርጓሜ ሰጥቷቸዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት እንደ ብሔሮች ወኪልነቱ ካሉት ወነኛ ሥልጣኖቹ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን መገለጫ የሆነውን ሕገ መንግሥት መተርጎም ነው። ከብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና በክልሎች መካከል ካሉ ግንኙነቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም የፌደሬሽም ምክር ቤት ሥልጣን ናቸው።

የፌደሬሽን ምክር ቤት በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ሊሳተፍ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ኹለት ናቸው – የሕጎችን ሕገ መንግሥታዊነት ማጣራት እና ሕግ የሚሹ የሲቪል ጉዳዮችን መለየት።

የዚህ ጽሁፍ ይዘት በዋነኛነት ሕግ የማውጣጥ ሥልጣኑ ባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በተለይም ሕግ በማውጣጥ ሥልጣኑ እና በዚህ ሥራው ውስጥ ስለሚኖር የሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተወሰነ ይሆናል።

2. የሕግ አወጣጥ ሒደት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ሕግ ማውጣጥ በሚባልበት ጊዜ አዲስ ሕግ ማውጣጥ ብቻ ሳይሆን ነባር ሕችን ማሻሻል፣ መሻር ብሎም የዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ማጽደቅንም ይጨምራል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምትገባቸው ስምምነቶች አስፈጻሚው ተደራድሮ ከፈረመ በኋላ የሀገሪቷ ሕግ እንዲሆኑ በምክር ቤቱ መጽደቅ እንዳለባቸው ልብ ይሏል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ ሕጎች “አዋጅ” ይሰኛሉ።

የአስፈጻሚው አካል የሆኑት የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ምክር ቤቱ በሚሰጣቸው ሥልጣን አማካኝነት የሚወጡትን አዋጆች ለማስፈጸም የሚያግዛቸውን “መመሪያ” የሚሰኙ ሕጎች ያወጣሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ሚንስትሮቹን የሚያካተተው የሚንስትሮች ምክር ቤት ሥልጣኑን ለመተግበር የሚያወጣቸው ደግሞ “ደንብ” ይሰኛሉ።

ሀ) ቅድመ-ምክር ቤት
የፌደራል ሕጎችን የማውጣጥ ዋነኛ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን፣ ክልሎች የራሳቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ሕግ የሚያወጡት ደግሞ በክልሎቻቸው ምክር ቤቶች ነው።

ሕግ በዋናነት የሚነጨው ከሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ሆኖ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚላከው ደግሞ በሚንስትሮች ምክር ቤት በኩል ነው። እያንዳንዱ የሚንስቴር መስሪያ ቤት በየዘርፉ የመንግሥትን ፖሊሲ ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን ሕግ ሊያመነጭ ይችላል። በ2011 በወጣ አዋጅ – 1097/11 ዐሥራ ዘጠኝ የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ተዋቅረው በሥራ ላይ ይገኛሉ። የሚንስቴሮቹ የተናጠል እና የወል ኃላፊነት በዚሁ አዋጅ ላይ ተዘርዝሯል። የሚንስትሮች ምክር ቤት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ ሕጎችን የማቅረብ ሥልጣኑን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 77(11) ሰጥቶታል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አሰራር እና የአባላቱን ሥነ ምግባር ለማስተዳደር በምክር ቤቱ የወጣው ደንብ ቁጥር 6/2008ም (ከዚህ በኋላ የምክር ቤቱ ደንብ እየተባለ የሚጠቀስ) ሕግ የማንጨት መብት በዋነኛነት “የመንግሥት ተግባር” መሆኑንና በሚንስትሮች ምክር ቤት ማኅተም ጸድቆ መምጣጥ እንዳለበት ይገልጻል። (የደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 51(1)(4) ይመለከቷል)

የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች የተቋቋሙበት እና የሚተዳደሩበት አዋጅ – 1097/2011 የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ሕግ የማመንጨት ሥልጣኑ እንዳላቸው ቢደነግግም የማመንጨት እና የማርቀቅ ሒደቱ ምን ሊመስል እንደሚገባ የሚያትተው ዝርዝር የለም። ይልቁንም ሕግ ስለ ማርቀቅና ማመንጨትን በተሻለ ዝርዝር የሚገኘው የሚንስትሮች ምክር ቤትን ሥራ በሚመለከት እራሱ ጥቅምት 2/2003 ባወጣው ባለ 36 ገጽ ማንዋል ላይ ነው።

በዚህ ማንዋል ላይ እንደተገለጸው የፌደራሉ መንግሥት ለሀገሪቷ ርዕሰ መስተዳድር በሚያቀርበው መሠረት፤ ኹለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን በሚጀምሩበት ቀን በዓመቱ ውስጥ ሊወጡ የታለሙ የሕግ ዓይነቶች፣ ሊወጡ ከታሰቡበት ቅድመ-ተዋረድ ጋር ለሕዝቡ ይቀርባል። እያንዳንዱ የሚንስቴር መሥሪያ ቤት ሕግ ስለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በሚያቀርበው መሠረት የሚንስትሮች ምክር ቤት ውስጥ በሚገኝ የሕግ ጉዳዮችን የሚያማክር ቡድን የሕግ ማርቀቅ ሥራው መች እንደሚካሄድ ጥናት አድርገው ይወስናሉ። ይህ ውሳኔም በሚንስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ የማርቀቅ ሥራው ይሠራል። የሚንስቴር መስሪያ ቤቶቹ እንዲወጡላቸው የሚሹዋቸውን ሕጎች ቅድመ-ተከትልም ሆነ አዲስ ሕግ በማንኛውም ጊዜ ማቅረብ ይችላሉ።

አስፈጻሚው ሕግ የማመንጨት ዋነኛው ባለመብት ቢሆንም ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦችም – የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ፣ የምክር ቤቱ አባላት፣ ቋሚ ኮሚቴዎች እና የፓርላማ ቡድኖች – ሕግ የማንጨት ሥልጣኑ አላቸው። በሌላ ሕጎች የተፈቀደላቸው ተቋማት በተለይም ለምክር ቤቱ ተጠያቂ የሆኑ እንደ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ያሉ ተቋማትም በራሳቸው ጉዳይ ላይ ሕግ ሊያመነጩ ይችላሉ።

ረቂቅ ሕጎች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅተው፤ የሕጉን አስፈላጊነት፣ ዓላማ፣ የፖሊሲ መነሻ፣ ይዘት፣ በሒደቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትና አስተያየታቸውን እና ሌሎች መረጃዎችን ያካተተ ማብራሪያ አብረዋቸው ይቀርባሉ።

ለ) ረቂቅ ሕግ ወደ ምክር ቤቱ ከቀረበ በኋላ ያለው ሒደት
ረቂቅ ሕግ ወደ ምክር ቤት ከመጣ በኋላ ሦስት የንባብ ደረጃዎችን ሊያፍል ይችላል። በመጀመሪያ ንባብ ሕጉን ያመነጨው አካል ቀርቦ ስለ ሕጉ ዓላማ እና ይዘት ለአባላቱ ማብራሪያ የሚሰጥበት ሲሆን ስለ አጠቃላይ ይዘቱ በቂ ውይይት ተደርጎበታል ተብሎ በአፈ ጉባኤው ሲታመን ወይም ሞሽን ቀርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ ለዝርዝር ምርምራ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል። ሞሽን ማለት በምክር ቤቱ ውይይት እንዲካሔድበት ወይም ውሳኔ እንዲሰጥበት በሚል በመንግሥት ወይም በምክር ቤት አባላቱ የሚቀርቡ የተለያዩ ጉዳዮች ማለት ነው። ምክር ቤቱ ካመነበት ወደ ቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ ቀጥታ ወደ ኹለተኛ ንባብ ሊተላለፍም ይችላል።

በኹለተኛ ንባብ በተሻለ ዝርዝር ውይይት ይደረጋል። በመጀመሪያው ንባብ ረቂቅ ሕጉ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ሲሆን በዚህ ላይ ዝርዝር ውይይት ተደርጎ፣ ውይይቱ በቂ መሆኑ ከታመነበት ድምጽ ይሰጥበታል ወይም ሪፖርቱና ውሳኔ ሐሳቡ ማሻሻያ ሞሽን ከቀረበበትና ተቀባይነት ካገኘ በድጋሚ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ሊመራ ይችላል – በኹለተኛው ንባብ።

ሦስተኛ ንባብ የሚኖረው በኹለተኛው ንባብ ረቂቅ ሕጉ በድጋሚ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ከነበረ ሲሆን፣ ኮሚቴው በሚያቀርበው ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ውይይት ተካሂዶ ውሳኔ ያሳልፋል። ውሳኔ የሚሰጠው መጀመሪያ አንቀጽ በአንቀጽ ድምጽ በመስጠት ሲሆን በመጨረሻም በረቂቅ ሕጉ ላይ አጠቃላይ ድምጽ ይሰጥበታል።

በመጨረሻ ረቂቅ ሕጎች ታትመው፣ የፕሬዝዳንቱ ፊርማ አርፎባቸው እና በነጋሪት ጋዜጣ ታተመው ሕግ ሆነው ይወጣሉ።
ነጋሪት ጋዜጣ፣ ሥሙን በድሮ ጊዜ ሕጎች ሕዝቦች በተሰበሰቡባቸው የገበያ ቦታዎች ሲነገሩ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ከሚመታ ነጋሪት ከሚባል የሙዚቃ መሣሪያ የተወሰደ ሲሆን፣ እንደ ቋሚ የሕጎች ማተሚያ ጋዜጣ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በ1932 ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሕጎች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ይታተሙበታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here