‹‹ብልጽግና መጥቶ ያድናችሁ እያሉ ነው የገደሉን››

0
671

በመተከል ዞን ከግድያ የተረፉ ሰዎች ከተናገሩት

በኮማንድ ፖስት ስር በሚገኘዉ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ቆርቃ ቀበሌ ከ 174 በላይ የሚሆኑ ንፁሀን ዜጎች በአንድ ቀን በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸውን በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

በጥር 4 ቀን 2013 ዓመት ጠዋት 12 ሰአት አካባቢ ወደ ቀበሌው በመግባት የታጠቁ ኃይሉች በአሰቃቂ ሁኔታ ንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያውን እንደፈፀሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በመተከል ዞን በንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያ መፈፀሙ እንደቀጠለ ነው መንግስት ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየሰራ ባለበት ሁኔታ ቀበሌ እና አቅጣጫ ቀይሮ ይሕ ነገር መፈፀሙ ያሳዝናል ሲሉ የአይን እማኞቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኮማንድ ፖስቱ መግለጫ በሰጠበት እና አካባቢው በአንጻራዊም ቢሆን መረጋጋት እያሳየ ነው ተብሎ በተነገረበት ማግስት ይህ ነገር መፈፀሙ መንግስት ሳይሆን እኛ እራሳችን ነን አካባቢውን የምናስተዳድረው የሚል ቡድን እንዳለ ያመላክታል ብለዋል።

የአካባቢውን ሁኔታ ያጋሩት ማንነታቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአዲስ ማለዳ ታማኝ ምንጭ እንደተናገሩት በመተከል ዞን ያለው ማንነት ላይ ያተኮረ ግድያ ቀጥሏል በዚህም የመከተል ዞን ነዋሪዎች ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል።

እማኛችን እንገለፁት በመተለከል ዞን መንግስት ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሰላም ለማስፈን እየሰራሁ ነው፤ አንፃራዊ ሰላም አለ በሚልበት ወቅት ነው ጥቃቱ የተፈፀመው በጣም ያሳዝናል ሲሉ ተናግረዋል።

ነዋሪው እንደተናገሩት ችግሩ ከመፈጠሩ ከኹለት ሳምንት በፊት የጥፋት ቡድኑ እየተዘጋጀ እንደነበር ለሚመለከተው አካል ሁሉ የድረሱልን ጥሪ እያቀረብን ነበር የደህንነት ስጋት እንዳለብን ተናግረን ነበር ነገር ግን ሊደርሱን አልቻሉም ብለዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት አካባቢ በብዛት የአማራ ማህበረሰብ እንደሚበዛም ተናግረዋል። አጥፊው ቡድን እየመረጠ ቀይ የሆነዉን እንደሚገድል እና ሲገድሉ ብልፅግና መጥቶ ያድናችሁ እያሉ እንደሆነም በስፍራው የነበሩ ከጥቃት ያመለጡ ነዎሪዎች ተናግረዋል።

በአሰቃቂ ሁኔታ በቀስት እና አንገት በማረድ ንፁሀንን እየጨፈጨፉ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ማክሰኞ ከሰአት በኋላ ግድያ ወደ ተፈፀመበት ቦታ መግባቱን አክለው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ መከላከያ ሰራዊት ወደ ቦታው ቢገባም አሁንም ድረስ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት አለብን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
የአዲስ ማለዳ ታማኝ ምንጭ እንዳስረዱት በመተከል ዞን በተለይም በቡለን ወረዳ የሚገኙ ሰዎች ቤት ንብረቶቻቸውን ትተው ህይወታቸውን ለማትረፍ አካባቢውን ለቀው በመውጣት ላይ ናቸው ብለዋል።

ከአሁን በፊት በመተከል ዞን የጅምላ ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል እንደነበረ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ዛሬም ዘርን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አዲስ ማለዳ ከቦታዎ ያገኛችው መረጃ ያመላክታል።

በመተከል በየጊዜው በተደጋጋሚ የሚደረገውን ማንነት ላይ ያተኮረ ግድያ እና ማፈናቀልን ለመከላከል በመንግስት ኮማንድ ፖስት ቢቋቋምም ነገር ግን አሁንም ጭፍጨፋው አልቆመም ስጋታችን ቀን በቀን እየጨመረ ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የሟቾችን አስክሬን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አፈር ለማልበስ መቸገራቸውንም ከጥቃቱ የተረፉ ዜጎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን አጥፊው ኃይል ሌላ ስፍራ ላይ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል ብለው እንደሚያስቡ በዚህም ከባድ የደህንነት ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢው ሰው እራሱን የመከላከል አቅም ነበረው ነገር ግን ኮማንድ ፖስት ተብሎ መሳሪያ እንዳይጠቀም በመታወጁ ምክንያት እራሳችንን መከላከልም አልቻልንም ብለዋል። ነገር ግን አጥፊው ቡድን እንደፈለገ መሳሪያ ይዞ ንፁሀን ዜጎችን እየጨረሰ ነው ሲሉ ያላቸውን የማያቋርጥ ስጋት ተናግረዋል።

ከ97 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በጫካ እና በመጠለያ ጣቢያ ተደብቀው እና ተጠልለው እንደሚገኙም አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ለማወቅ ችላለች ።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here