በትግራይ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተከልም እንዲደገም ተጠየቀ

0
401

መንግስት በትግራይ ክልል የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም የመተከል ዞን የጸጥታ ችግርንም ሊፈታ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በመተከል ዞን የንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ አካል ጉዳትና መፈናቀል ሊቆም ያልቻለው ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው አካላት እንደሆነም የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በመተከል ዞንና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸመውን የዜጎች ግድያ አስመልክቶ በቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቷል።
ቋሚ ኮሚቴዎች በምርምራ ሂደታቸው በደረሱባቸው ዋና ዋና ጭብጦች በመተከል ዞንና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው የጸጥታ ችግር ማንነትን መሰረት ያደረገ የንጹሃን ዜጎች ህይወት መቀጠፉን፣ የአካለ ጉዳትና ንብረት ውድመት መድረሱ ተነስቷል።
የተፈጠረው ችግር የተወሳሰበና በፍጥነት ሊቆም ያልቻለው የፖለቲካ ዓላማ ባለቸው አካላት ስለመሆኑ ቋሚ ከሚቴዎቹ አስረድተዋል።
የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ እንደገለጹት መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማስፋት አሳሪ ሕጎችን የማሻሻልና አዳዲስ ሕግጎችን በማውጣት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል።
ለውጡ ያልተዋጠላቸው የጥፋት ሃይሎች ግን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለሚፈጠሩ ግጭቶችና ለንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆነዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከጥፋት ሃይሎች ጋር በማበር ችግሩ እንዲባባስ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት በትግራይ ከልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም ችግሩን ሊፈታ ይገባዋል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here