የሐዋሳ የኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ ችግር ላይ መሆኑ ተገለጸ

ለሥራ ማስኬጃ የሚመደበው 10 ሺሕ ብር ብቻ ነው

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቡድን አባላት በኢሚግሬሽን እና ወሳኝ ኹነቶች ኤጄንሲ የሐዋሳውን ቅርንጫፍ በጎበኙበት ወቅት የቅርንጫፉ ሠራተኞች በበርካታ ችግር ላይ እንደሚገኙ መገንዘባቸውን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን የሐዋሳ የኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ ምን እንደሚመስል እና በምን አይነት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ ትዝብቱን ለቅርንጫፉ ማኔጅሜንት ዘርዝሯል።

የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አድነው ተስፋዬ ቀደም ሲል ቅርንጫፉ በዕቅድ ሳይሆን በዘፈቀደ ሲመራ እንደነበር ከቅርንጫፉ አዲስ አስተባባሪ ከሆኑት ገነት ኃይሉ መረዳታቸውን ጠቅሰው አሁን ግን ከሌለ ነገር ተነስቶ የስድስት ወራት ዕቅድ አዘጋጅቶ መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
ከሐዋሳ የኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ ባልተመቻቸ ሁኔታ የሚሰበሰበው የዕለት ገቢ ለፌዴራሉ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ እየተላከ መሆኑም ጥሩ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የቡድኑ አባል የተከበሩ ገረመው ኡጋ በበኩላቸው፤ የዜጎች ስደት በማስቀረት በሀገራቸው የሚሠሩበት እና የሚያመርቱበት መንገድ በክልሉ እና በፌደራል መንግስት መመቻቸት አለበት ብለዋል። እንደ ቅርንጫፉ አስተባባሪ ገነት ገለጻ መሠረት 10 ሺህ ብቻ የሆነው የቅርንጫፉ የሥራ ማስኬጃም ዝቅተኛ ስለሆነ በቋሚ ኮሚቴው በኩል ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚወያዩበት አስታውቀዋል። በአንጻሩ ፎርጅድ መረጃዎችን ከማጣራት አኳያ የሚታየው ጥንካሬ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የተከበሩ ሙሀጅብ አብዱ በበኩላቸው፤ በቅርንጫፉ ውስጥ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው በተገልጋዮች የሚደርሰው ዕንግልት ሊፈታ ይገባል ብለዋል።

ገነት ለቋሚ ኮሚቴው ቡድን አባላት አክለው እንዳስገነዘቡት፤ በቅርንጫፉ የበይነ-መረብ ተደራሽነት ውስንነት እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ዕጥረት አለ ሠራተኛውም የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም እና የደንብ ልብስ እንዲሁም የደረጃ ዕድገት ስለማያገኝ ደስተኛ አይደሉም ብለዋል።

የቅርንጫፉ ሱፐርቫይዘር አበራ ኤርሚያስለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለመቅጠር ብንሞክርም፤ ጥቅማ-ጥቅም ባለመኖሩ ተረጋግተው አለመቀመጣቸውን እንደገለጹላቸው በሪፖርቸው ገልጸዋል።

የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከ2013 ጀምሮ የፓስፖርት ጥያቄን በበይነ መረብ (ኦንላይን) እንደሚያደርግ መግለጹ የሚታወስ ነው።የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሙህጂብ ጀማል ሐምሌ 30/ 2012 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከፓስፖርት ጥያቄ በተጨማሪ የቪዛ ማራዘም፣ የትውልድ መታወቂያና የመኖሪያ ፈቃድ ከ2013 ጀምሮ በበይነ መረብ ተግባራዊ እንደሚደረግ በወቅቱ ገልጸዋል።

አዲስ ፓስፖርት የሚያወጡ፣የፓስፖርት እድሳት የሚፈልጉ እና ሌሎች የፓስፖርት አገልግሎት የበይነ መረብ ወይንም የኦንላይን ተመዝጋቢዎች ምዝገባቸውን በኦንላይን ካካሄዱ በኋላ ሲስተሙ በሚሰጣችሁ የመክፈያ ቁጥር በባንክ ቅርንጫፎች ወይንም በCBE ብር ብቻ መክፈል እንዳለባቸውም ኤጀንሲው በድረ ገጹ አስታውቋል።

በተጨማሪም እነዚህን መስፈርቶች አሟልተው ከጨረሱ በኋላ ተገልጋዮች ፓስፖርታቸውን ለመውሰድ ወደ ኤጀንሲው በሚያመሩበት ወቅት በኦንላይን ምዝገባ ወቅተ ያስገቧቸውን ኦሪጅናል ሰነዶችእንዲሁም በድረ ገጽ ምዝገባ ጊዜ የተሰጣቸውን መለያ ቁጥር በመያዝ መሄድ እንደሚኖርባቸው ገልጿል።

አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት የሚያስፈልጉት የልደት ምስክር ወረቀት እና የአገልግሎት ጊዜው ያላለቀ የቀበሌ መታወቂያ ሲሆኑ ምንም አይነት ተጨማሪ ማስረጃ አያስፈልግም። የሚወስደው ጊዜ ካመለከቱ በኋላ በኹለት ወር ውስጥ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ፓስፖርት በአስቸኳይ ማግኘት ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ደግሞ ጉዳዩ የስሥራ ከሆነ ከመሥሪያቤት የተፃፈ ህጋዊ ደብዳቤ እና የመሥሪያ ቤቱ መታወቂያ ለዲቪ የህክምና ወረቀት(ሪፈር) ጊዜ ያለው የውጪ ሃገር መኖሪያ ፍቃድ ጊዜ ያለው የውጪ አገር የሥራ ፍቃድ የኢምባሲ ቀጠሮ ተመላላሽ መንገደኞች ሆነው ፓስፖርት ገፁ ያለቀባቸው ፓስፖርቱን ይዞ መቅረብ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ጊዜ ያለው የባህረኞች መታወቂያ (ሲማንቡክ) ይዘው በመቅረብ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ኤጀንሲው አሳውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here