የአማራ ክልል መሥተዳደር ምክር ቤት የሰባት ከተሞችን ደረጃ ሽግግር አፅድቋል። ምክር ቤቱ በአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ተጠንተው የደረጃ ሽግግር እንዲደረግላቸው የቀረቡ ሰባት ከተሞችን ደረጃ ሽግግር አፅድቋል። ወደ ከተማነት ካደጉት ውስጥ ቲሊሊ፣ ወገልጤና፣ ሃራ፣ አምደወርቅ፣ ቱለፋ፣ ጨፋሮቢት እና ሰንበቴ ከተሞች ናቸው። ሁሉም ከተሞች ከመሪ ማዘጋጃ ወደ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ነው የተሸጋገሩት።
ከተሞቹ ወደ ከተማ አስተዳድርነት አደረጃጀት መዋቀራቸው ለነዋሪዎች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ለመቀነስ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ተብሏል።
የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ባካሄደው ጥናት ቲሊሊ፣ ወገልጤና፣ ሃራ፣ አምደወርቅ፣ ቱለፋ፣ ጨፋሮቢት እና ሰንበቴ ከተሞች ወደ ከተማ አስተዳድርነት እንዲያድጉ መወሰኑን ተመላክቷል።
አንድ መሪ ማዘጋጃ ቤት ወደ ከተማ አስተዳድርነት ሲያድግ ለቢሮ መሰረተ ልማት፣ የሰው ኃይልና በጀት ያስፈልጋል። እነዚህን ወጭዎች በመንግሥት አቅም ብቻ ማሟላት ስለማይቻል ኅብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ተጠቁሟል።
በአማራ ክልል ከከተማ አስተዳድርነት ጥያቄ በተጨማሪ 5 ከተሞች ወደ የሪጂኦፖሊታንትነት የማደግ ጥያቄ በማቅረባቸው የክልሉ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጥናት አካሂዷል፣ ጥያቄውን ያቀረቡት ደብረ ታቦር፣ ወልድያ፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን እና ኮምቦልቻ መስፈርቱን ሲያሟሉ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅም ይጠበቃል።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013


