መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየጠቅላዩ ‹‹መከሰት››

የጠቅላዩ ‹‹መከሰት››

ሰሞነኛ መነጋገሪያ አርዕስት ከሆኑት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመገናኛ ብዙኀን ድምጻቸውንም ሆነ ምስላቸውን መጥፋት የተመለከተው ቀዳሚ ጉዳይ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታኅሣሥ 14 ቀን ጀምሮ አልታዩም፤ ሲናገሩም አልተሰሙም በማለት ቀን ቆጥረው ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መሪ እንደመሆናቸው የእሳቸው አንድ ነገር መሆን በእሳቸው ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑ ስጋቱን ያንረዋል። በማኅበራዊ ትስሰር መድረኮች ከተዘዋወሩት መላምቶች መካከል በጽኑ ታምመው ሕክምናቸውን በውጪ አገር እየተከታተሉ ነው የሚለው ይገኝበታል። ከጤናው ጉዳይ ሳይራቅ ደግሞ በኮሮና ተይዘው ራሳቸውን ወሻባ አስገብተው ነው የሚልም ተሰምቷል።

ጤና እንደዋና የመጥፋታቸው ሰበብ ይቆጠር እንጂ፥ በትግራይ የተጀመረው የሕግ ማስከበር አለመጠናቀቅ እንዲሁም በዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ በመሆናቸው በትኩረት ሥራቸው ላይ አድፍጠው ነው ያሉ አንዳንዶች መላምታቸውን አጋርተዋል። ሌላው መላምት ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባቸዋል፤ እንዲያውም አስረዋቸዋል፤ ቢየኝስ በቁም እስር ላይ ናቸው ያሉም አሉ። ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር በተያያዠ ገድለዋቸዋል የሚልም ወሬ በከባዱ ተናፈሷል። በተለይ ይህ ተገድለዋ መላምት ብዙዎችን ያሸበረ ሲሆን ይህንን ለሚሉት ማርከሻ ተደርጎ ምላሽ ይሆናል ተብሎ የተሰጠቀሰው ደግሞ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት የሚካሄደው በጓዳ ውስጥ ነው እንዴ?›› ሲሉ አቃልለውታል፤ ተሳልቀውበታል።

አንዳንዶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጥፋት ከሥራ ጫና ወይም ደግሞ ከእረፍት ጋር የተያያዘ ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም ሲሉ በልበ ሙሉነት ሲከራከሩ ሰንብተዋል። ለዚህ አቋማቸው እንደአመክንዮ የሚጠቅሱት፥ ቀዳማይ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ባለፈት ኹለት እና ሦስት ሳምንታት በየክልሉ እየዞሩ ያስመረቋቸውን ትምህርት ቤቶች ያነሳሉ። ባለቤታቸው አንድ ነገር ቢሆኑ ኖሮ፥ እንዴት እሳቸው ክልል ሲያካልሉ ይከርማሉ ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ። በፍፁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም አልሆኑም!

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥፋት ዙሪያ ኹለት ዓይነት ስሜቶች በዋናነት ተንጸባርቀዋል። ሕወሓት (በሕይወት ካለ?!) እና አጋሮቹ የጠቅላዩን እንደድል ብስራት ሲቆጥሩት፤ ደጋፊዎቻቸውን ግን ከባድ ስጋት ላይ ጥሏል። በሦስተኛ ወገን ሊጠቀስ የሚችሉት ብዙኀን ሁኔታውን በጥንቃቄ እና በማጤን ያለምንም አቋም ማንጸባረቅ አልፈውታል።

ባለፈው ሳምንት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ ማስተባበያ መልዕክት ሰፍሮ ነበር፤ ይሁንና አንዳንዶች የመልዕክቱን ይዘት ባያምኑትም።
የሆነው ሆኖ ኀሙስ፣ ጥር 20 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስድስት ሰዐቱ ዜና እወጃ ላይ በሰው ሰራሽ አካል እና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅትን ሲጎበኙ የሚያሳይ በምስል የተደገፈ ዜና አቀረበ። ከመቅጽበት የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት መከሰትን አስተጋቡ። አንዳንዶች እስካሁን ድረስ ባለማመን የቆየ ጉብኝት ነው፤ እሳቸው አይደሉም ሲሉ ጽፈዋል።

ከሰዐታት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስተሩ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ‹‹ለተጎዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሲቪሎች የሚሠራውን ሰው ሠራሽ አካል ዛሬ ጎብኝቻለሁ።በሕግማስከበር ሒደትና በሌሎች ጊዜያት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው በበጎ ፈቃደኛችና በድርጅቱ ባለሙያዎች የሚከናወነውን የሰው ሠራሽ አካል ማምረቻ ድርጅት ሠራተኞች የሚደነቅ ሥራ እየሠሩ ነው። ከውጪ መጥተው በበጎ ፈቃደኝነት ይሄንን ታላቅ ሥራ የሚሠሩ ሰሎሞን አማረን የመሰሉ ወገኖች ሊበረታቱ ይገባል።›› የሚል መልዕክት አስፍረዋል።

እርግጥ ነው! የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥፋት የተራ ሰው መጥፋት አይደለምና እንዲህ ድርግም ብለው ባይጠፉ እና አገሩን ባያሸብሩት ጥሩ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች