በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣንን የ2013 በጀት ዓመት የኹለተኛ ሩብ የዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የትራፊክ አደጋ በሚጠበቀው መጠን ባለመቀነሱ በትኩረት እንዲሰራበት አሳስቧል፡፡
በዕለቱ የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ያደታ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡ ሲሆን በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጁ ጥያቄዎችም ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ባለስልጣኑ የወጪና ገቢ ንግዱን በማፋጠን፣ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ በማስገጠም እንዲሁም የመንገድ ዳር ምልክቶችንና ማመላከቻዎችን በመትከል ጥሩ አፈጻጸም እንደነበረውና በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መጓተት፣ የትራፊክ አደጋን በሚጠበቀው መጠን አለመቀነስ፣ በአዲስ አበባ እና በአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ዘርፍ ያለው እንግልትና የተሽከርካሪዎች ከደረጃ በታች መሆን እንዲሁም፣ ሞዴል የአሽከርካሪ ብቃት ማሰልጠኛዎችን ማብቃት ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት የቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ነበሩ፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች አግባብነት እንዳላቸው የገለጹት የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ያደታ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች ጋር ያለው ችግር ተቀርፎ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013



