መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛበሰላማዊ ሰልፍ ሰበብ ‹‹ትንኮሳ?!››

በሰላማዊ ሰልፍ ሰበብ ‹‹ትንኮሳ?!››

ማክሰኞ፣ ጥር 25 በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እና ዞኖች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን እና የብልጽግና ፓርቲን ድጋፍ ለማሳየት ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸው የብዙኀንን ትኩረት አግኝተዋል። ሰልፎቹ ትኩረት የማግኘታቸውን ያክል፥ በአንዳንድ ሰልፈኞች የተላለፈው መፈክሮች እና ንግግሮች ትንኮሳ አዘል መሆናቸው ብዙዎች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮችም ሆነ በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን ሲተቹት ከርመዋል።

የሰልፎቹ ፈቃድ ማግኘት የመጀመሪያው መነታረኪያ ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን ለዚህም ዋና ምክንያት ተደርጎ የተነሳው፥ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) የተባለው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ፓርቲ በአዲስ አበባ የአገር ሉዓላዊነት ይከበር በሚል ሊያካሂድ የነበረው ሰልፍ ያለአግባብ በፖሊስ መከልከሉ በተሰማበት በቀናት ልዩነት በርካታ ሰልፎች ያለምንም ከልካይ በኦሮሚያ መካሄዳቸው ነበር።

አዲስ አበባ ላይ በተቃዋሚዎች የሚጠሩ የሚጠሩ ሰልፎችን ፈቃድ መስጠት በተደጋጋሚ ጣር የሆነበት መንግሥት፥ ለራሱ ድጋፍ ሲሆን ግን ያለምንም ማቅማማት ማካሄድ ይቻላል። ‹‹አይ አለማፈር!›› ይህ የአድልዖ አካሄድ የኢሕአዴግ/ሕወሓት መንግሥትን ያስታውሳል ሲሉ አንዳንዶች መድልዖውን አውግዘዋል፤ አምባገነን ለመሆን የሚንደረደር መንግሥት፥ ከራሱ ውድቀት እንጂ ከቀድሞዎቹ የመማር ዝንባሌ እንደሌለው ማሳያ ነው ሲሉም ተችተዋል።

በኦሮሚያ በተካሄዱት ሰልፎች ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ ተሳታፊ እንደነበር በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሆኑት ፍቃዱ ተሰማ ኀሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። በሰልፎቹ ላይ ከተነሱት አወዛጋቢ ነገሮች መካከል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕልውናውን ያጣው ሕወሓት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) እና ባልደራስ የተባሉትን ፓርቲዎች በሥም በመጥቀስ ‹‹ጁንታ›› ሲሉ ማውገዛቸው ይገኝበታል። ይህንንም ተከትሎ አብን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቅርቧል። በሰልፎቹ ላይ ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል፤ ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የሥነ ምግባር ደንብ የጣሰ ነው ሲል በግልጽ ቅሬታ አዘል አቤቱታውን አቅርቧል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፍጥነት የአብን’ን አቤቱታ ተመልክቶ መግለጫ ያወጣ ሲሆን በመግለጫውም ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁ ንግግሮች እና መፈክሮች በሕግ የተጠቀሰውን ሥም የማጥፋት ንግግር እና ክልከላ ድንጋጌን እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሃት የመፍጠር ሥነ ምግባር ጥሰት ተፈጽሞ አግኝቷል። ከዚህም በተጨማሪም ሥማቸው የተጠቀሱት ፓርቲዎች እና ገዢው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው የፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን ‹‹ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሐሳብ ወይም የዘር ልዩነት፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሰረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚጻረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈጸም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው›› የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነው ሲል በግልጽ አስጠንቅቋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርዱ ለወደፊት በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1165/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሰረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ እና ሌሎች ለሕዝብ የሚሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከ እጩ መሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በማኅበራዊ ትስስር መድረኮችም ሆነ በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን አንዳንዶች የቦርዱን ፈጣን እርምጃ በማድነቅ፥ የዱሮው ምርጫ ቦርድ ስላልሆነ ብልጽግና ፓረቲ ቢጠነቀቅ ይሻለዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። ከፓርቲ መሪዎች ደግሞ፥ በቅርቡ የትዊተር ገጽ የከፈቱት የኢዜማው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የምርጫ ቦርድ በኦሮሚያ ለሚገኙ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ለሰጡ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ማስጠንቀቀያ መስጠቱን ከማወደስ ባሻገር እንደዚህ ዓይነት ማስጠንቀቂያዎች መጪው አገራዊ ምርጫ ተዓማኒ እንዲሆን አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው ሰልፎቹን ለማጠልሸት ሲሰሙ የነበሩት ጥቃቅን ድምጾች የሕዝብ ክብር እና ድጋፍ ካለማወቅና ካለመረዳት የመጡ ስለሆነ በሕዝብ ዘንድ ቦታ የላቸውም ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ተነካን የሚሉ ፓርቲዎች ራሳቸውን ይመልከቱ ሲሉ ከምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ያሉት አስመስሎባቸዋል።

የሆነው ሆኖ ብዙዎች የምርጫ ቦርድ ለገዢው ፓርቲ ፈጣን የማስጠንቀቂያ ምላሽ መልዕክቱ ትዕምርታዊ ነው ሲሉ አወድሰውታል። ገዢው ፓርቲም የድሮው የኢሕአዴግ ምርጫ ቦርድ አለመሆኑን አውቆ መገዳደሩን ቢያቆም ይሻለዋል በማለት በተለይ የቦርዱን ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳን አድንቀዋል። መጪው ምርጫ ተስፍ የሚጣልበት ነው ሲሉ አንዳንዶች ለቦርዱ ያላቸውን አድናቆት ከመግለጽ አልተቆጠቡም።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች