መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛ‹‹አቧራ ያስነሳው›› ታማኝ በየነ

‹‹አቧራ ያስነሳው›› ታማኝ በየነ

ታዋቂው የመደረክ ፈርጥ ታማኝ በየነ ከጥበብ ሕይወቱ ባልተናነሰ በተግባር በተገለጸ አገር ወዳድነቱ፣ በሰብኣዊ መብት ተሟጋችነቱ እና ለወገኖቹ ችግር ፈጥኖ ደራሽነቱ ይታወቃል። በተለይ ሰብኣዊ እርዳታን አስተባብሮ ለወገኖቹ ለመድረስ ማንም የሚቀድመው እንደሌለ በተደጋጋሚ አስመስክሯል፤ ይህንን ለማቀላጠፍ ውጪ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ‹ግሎባል አሊያንስ› የተባለ ግብረሰናይ ድርጅትም እስከማቋቋም ደርሷል።

ከጥምቀት በዐል ቀደም ብሎ ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ አገር ቤት የመጣው ታማኝ፥ በጎንደር በተከበረው ደማቅ የጥምቀት በዐል አከባበር ላይ ተሳታፊ ነበር። ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በመሆን በእንጅባራ እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች የምረቃ ሥነ ስርዓት እንዲሁም መተከል ላይ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በአካል ሄዶ ለማየት ዕድል አግኝቷል። ይሁንና ግላዊ የቤተሰብ ጥየቃውን በመተው በትግራይ ከተካሄደው የሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ እንዲሁም በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ለተቸገሩ ወገኖቹ ለመድረስ ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ ስብስቦች ጋር በመሆን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ‹‹ሰብኣዊነትና ፍቅር፤ ለትግራይና መተከል›› ድጋፍ በዓይነት እና በገንዘብ የማስተባበር ተግባሩን በይፋ መጀመሩን አስታውቋል።

ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለወገኖቻችን ሰብኣዊ ድጋፍ ለማድረግ የግድ ከትግራይ ወይም ከአማራ መወለድ እንደማያስፈልግ፤ ነገር ግን ሰው መሆን፣ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ነው ሲል በአጽንዖት ተናግሯል። ኢትዮጵያውያንም አነሰ በዛ ሳይሉ የአቅማቸውን ያክል እጃቸውን እንዲዘረጉም ተማጽኗል። የጋዜጠዊ መግለጫውን ተከትሎ ግን በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ነቀፌታ፣ ድጋፍ እና መደናገር የሚያንጸባርቁ አቋሞች በበርካቶች የተንጸባረቁ ሲሆን በአጠቃላይ ታማኝ ሰሞነኛ መነጋገሪያ አርዕስት ለመሆን በቅቷል።
በተለይ አንዳንድ አክራሪ የሕወሓት ደጋፊ እንደሆኑ የሚጠረጠሩ ትግራዋይ፥ ታማኝን በማንጓጠጥ፣ በመሳደብ እና በማስፈራራት በትግራይ ሊያደርገው ያሰበውን ሰብኣዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲያቆም አስጠንቅቀዋል። ብዙዎቹ ከስድብ ባሻገር ይሄ ነው የሚባል ምክንያታቸውን በበቂ አመክንዮ ሊያስረዱ ግን አልቻሉም። አንዳንድ የታማኝ ነቃፊዎች፥ ሴቶች ሲደፈሩ፣ ሕዝብ በመከላከያ ሠራዊት ሲጨፈጨፍ እና መብቱ ሲረገጥ የት ነበረና ነው አሁን ድጋፍ ላድርግ የሚለው ሲሉ ጥያቄ መሰል ወቀሳ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በርካቶች፤ ታማኝ ለእረፍት እና ዘመድ ጥየቃ ብሎ ወደ አገር ቤት ተመልሶ ግላዊ እቅዱን ወደ ጎን በማድረግ የተለመደውን ለወገኑ ደራሽነት ዘመቻ ማስተባበሩን አድንቀዋል፤ አበረታትተዋል፤ ድጋፋቸውንም በተግባር ለማሳየት ቃል ገብተውለታል። አንዳንዶችም ታማኝን የሚተቹትን ተከታትለው ምላሽ በመስጠት ተጠምደዋል። ‹‹ታማኝ ምን ያድርጋችሁ?›› ለወገን ድጋፍ ባስተባበረ ሊሰደብ አይገባውም በማለት የአጸፋ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንዲሁም ሌሎች መረር አድርገው የታማኝን ተቺዎች ተችተዋል፤ የታማኝን በተግባር የተገለጸ የቀደመ ሰብኣዊ ርህራሄ ዘርዝረውም ተሟግተዋል። በተለይ አንድ ግለሰብ በፌስቡክ ገጻቸው ‹‹ታማኝ ምን ቢያደርግ ነው የማይሰደበው?›› ሲሉ ሰፋ ያለ ጽሁፍ አስነብበዋል። የትግራይ ተቆርቋሪ ነን ባዮች እንረዳዳ ስላለ ብቻ በታማኝ ላይ የጥላቻ እና ስድብ መዓት ማውረዳቸው ከራሳቸው ጋር መጣላታቸውን ማሳያ ነው ያሉት ጸሀፊው፥ በአንድ በኩል ደግሞ ራሳቸው ተሳዳቢዎቹ ይህንን ያክል ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ እርዳታ ይፈልጋል እያሉ የምግብ ድጋፍ ጥሪ ያቀርባሉ ብለዋል።

ጸሀፊው በመቀጠል የታማኝ የሰብኣዊ ድጋፍ እና የሰው ልጆች መብት ተቆርቋሪነት የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ሕይወቱ በሙሉ የኖረበት ነው ሲሉ በቅርብ ዓመታት እንኳ ለጌዲዖ ተፈናቃዮች፣ ለጋሞዎች፣ በየቦታው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሲደርስባቸው ለከረመው የአማራ ተወላጆች ያደረጋቸውን ድጋፎች ለአብነት ጠቅሰዋል።

አንዳንዶችንም በታማኝ ዙሪያ የተነሳው እሰጣገባ ግራ ቢገባቸው፥ ማገዝ ቢያቅተን እንዴት በራሳቸው ተነሳሽነት ለወገኖቻችን ድጋፍ ለማድረግ የሚጥሩና ለማኅበረሰባችን አርዓያ የሆኑ ግለሰቦችን ለማደናቀፍ እንሞክራለን ሲሉ ምክር አዘል አግራሞታቸውን አንጸባርቀዋል።
የሆነው ሆኖ ‹‹ውሾቹ ይጮኻሉ፥ ግመሎቹ ጉዟቸውን ቀጥለዋል›› እንደሚባለው በዓይነት ድጋፋ እያደረጉ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ታማኝ በጣይቱ ሆቴል እና በቀይ መስቀል ማኅበር (ስታዲየም) በአካል በመገኘት በማመስገን ድጋፎቹን ከባልደረቦቹ ጋር በመቀበል የጉልበት አገልግሎት ሲሰጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው የሒሳብ ቁጥርም መጠኑ እስካሁን ባይገለጽም የገንዘብ ድጋፉ እንደቀጠለ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች