ለተጎጅ የውጭ አገር ተመላሾች ማቋቋሚያ ደንብ እየተዘጋጀ ነው

ወደ ውጭ አገራት ለሥራ አምርተው የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ለሚመለሱ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚሆን አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ እንደሆነ ታወቀ።
ብሔራዊ የትብብር ጥምረትን ሥልጣንን እና ተግባር እና የተጎጅዎችን ፈንድ አስተዳደር እና አጠቃቀምን ለመወሰን የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደምብ እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
አላማው በሰው የመነገድ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና ከአገር የማስወጣት ወንጀሎች ተፈጽሞባቸው በዚህ መንገድ የተጎዱ ሰዎችን ለማቋቋም የሚረዳ እንደሆነ በኢፌድሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከፍተኛ አቃቤ ሕግ የሆኑት አቤል ገብረእግዛብሄር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ይህ ተጎጅዎች ማቋቋሚ ፈንድ በቦርድ የሚተዳደር እና በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሰብሳቢነት እንዲሁም በሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፀሐፊነት የሚተዳደር እንደሆነ እና በስሩ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ተቋም የፌድራል ፖሊስ የሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትን እንደሚያካትት ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

ይህን ፈንድ የሚያገኙ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው ስንል ደግሞ ተጎጅዎች ማለትም ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ ከፍለው ከአገር የወጡ እና ስለ ተጎጅዎች ወጭ ያወጡ ማለትም በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እና በደላሎች ለታገቱ ቤተሰቦቻቸው ቤት ንብረት ሸጠው ገንዘብ የላኩ ሰዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ሰዎች ከተከሳሽ ደላሎች እና ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የካሳ ክፍያ በማያገኙበት ጊዜ ማለትም ተከሳሾቹ በስማቸው የተመዘገበ ሀብት ሳይገኝባቸው ሲቀር ከመንግሥት ካሳ ያገኛሉ ብለዋል።

የተጎጅዎች ፈንድ አስተዳደር የሚያገኘው ገቢ አንደኛው የፍርድ ቤት ውርስ ይሆናል ብለዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተሰማርተው ክስ ቀርቦባቸው ንብረታቸው የተወረሰባቸው ድርጅቶች ንብረት ገቢ የሚደረገው ለዚህ ተቋም እንደሆነ አስታውቀዋል።
እነዚህ የስደት ተመላሾች የሚደርስባቸው ከገንዘብ መጭበርበር በተጨማሪ የጤና እና የሥነልቦና ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል። ለነዚህ ተጎጅዎች የሕክምና ወጭም በዚህ ፈንድ እንደሚሸፈን ዐቃቤ ሕጉ ገልጸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ከባድ የሆነ የጤና እክል ገጥሟቸው የመጡበትን ሥፍራ የማያስታውሱ ሊሆኑ ይችላሉ እነዚህን ጉዳተኞች ከቤተሰቦቻቸው የማገኛኘት ሥራም እንደሚሠሩ አሳውቀዋል።

ዐቃቤ ሕጉ መንግሥት እስከዛሬ ተግባራዊ አላደረገውም እንጂ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ ቆይቷል ይህንን የመንግሥት ኀላፊነት እየሠሩ የሚገኙት እንደ አጋር ኢትዮያ እና ኦፕሪፕስ ያሉ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ናቸው እነርሱ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ የአእምሮ እክ የገጠማቸውን የውጭ አገር ተመላሾች ያሳክማሉ ይንከባከባሉ ብለዋል። ይሕ ፈንድ ለነዚህ አይነት ተቋማት የመጠለያ ግንባታ እንደሚያደርግ አሳውቀዋል።

አጋር ኢትዮጵያ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደ ኤሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ 2005 ጀምሮ ከስደት የሚመለሱ ዜጎች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ የድርጅቱ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አበራ አደባ(ዶ/ር) ገልጸዋል። እስካሁን 20 ሺሕ ለሚሆኑ ከስደት ተመላሾች ድጋፍ ማረጉን ተናረው ከእነዚህ መካከል 6 ሺሕ 900 ያህሉ በጽኑ ያታመሙ እንደሆኑ እና በተቋሙ የመጠለያ ጣቢያ እንክብካቤ የተደረገላቸው እንደሆኑ አሳውቀዋል።

እነዚህ በጽኑ የታመሙ ከስደት ተመላሾች በመጠለያ ጣቢያቸው የሕክምና የምግብ የልብስ የምክር እና የንጽህና አጠባበቅ እንክብካቤ ሲደረግላቸው ቆይተው በሕክምና ሙሉ ጤንነታቸው መመለሱ ሲረጋገጥ የሙያ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸው እና ጥቂት ማቋቋሚያ ገንዘብ ተሰጥቷቸው እና ከሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ጋር አገናኝተናቸው ወደየመጡበት ቦታ ይመለሳሉ ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here