የአዲስ አበባ ኢንቨስትመን ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ባስጠናው ጥናት መሰረት ከ2008 እስከ 2012 አመት ወደ ኢንቨስትመንት ስራ ሊገቡ ፍቃድ የወሰዱ 18 ሺሕ 201 ኢንቨስተሮች ሲሆኑ ወደ ስራ የገቡት ግን 5 ሺሕ ስድስት መቶ ሀያ ሰባት ብቻ መሆናቸውን ባጠናው ጥናት ማግኘቱን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
መቶ በመቶ ወደ ስራ ያልገቡበት ምክንያት መካከል በዋናነት የመሬት እንዲሁም የመሰረተ ልማት አለመሟላት መሆኑን አዲስ ማለዳ ያየቻቸው መረጃዎች ያያመላክታሉ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአዲስ አበባ ኢንቨስትመን ኮሚሽን ጥናቱ ሲሰራ የጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ እንዲም በኮሚሽኑ የፀረ ሙስና ዳይሬክተር ተስፋዬ ጫካ ኮሚሽኑ ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆነ ሁኔታን ለመፍጠር ባለፉት ስድስት ወራት ኹለት ጥናት ማስጠናቱን ጠቁመዋል።
በከተማ ኢንቨስትመንቱ ላይ ያሉትን ችግሮች እንዲሁም አዋጭ ኢንቨስትመንት የቱ ነው የሚለውን የሚጠቁሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።በኹለቱም ጥናቶች በርካታ የሆኑ አመላካች ነጥቦችን ማንሳቱን አስታውቀዋል።
በዚህም የመጀመሪያው ጥናት የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ስራ አመራር ኢንስቲቲዩት በጋራ በመሆን እንደተጠና ተናግረዋል።
ለአጠቃላይ ለከተማዉ ጥቅል እድገት እንዲሁም የዉጭ ምንዛሬ ከማስገኘት አንፃር ያበረከተዉን አስዋፆ በዚህ ጥናትየተካተተ ሲሆን በዚህም ኢንቨስትመንት በአጠቃላይ ለከተማዉ ጥቅል እድገት (GCP) አምስት ነጥብ አምስት በመቶ ለኤክስፖርት 35 ነጥብ አምስት በመቶ ለስራ እድል ፈጠራ ኹለት ነጥብ ኹለት በመቶ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጥናቱ አመላክቷል።
ነገር ግን ፍቃድ ከወሰዱ ኢንቨስተሮች ወደ ስራ የገቡት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ይህም የሆነበት ምክንያት ለኢንቨስተሩ አመቺ የሆነ ሁኔታ ባለመኖሩ እንደሆነም እንደሆነም ጥናቱ ማመላከቱን ተናግረዋል።
በዚህም የመሬት አቅርቦት ከፍተኛውን ስፍራ እንደሚይዝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የኢንቨስትመንት ስራዉ ሰፊ ቦታን የሚፈልግ ነው ኢንቨስተሮችን እንጠራለን ነገር ግን ቦታ አናዘጋጅላቸውም ብለዋል።
ሌላኛው ችግር የውጪ ምንዛሬ እጥረት ነው።የምንዛሬ እጥረቱ እንደ አገር እንዳለ ይታወቃል ነገር ግን ኢንቨስተሮች ማሽነሪዎችን ለማስገባት እንዲሁም ጥሬቃዎች ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል ይህም የተፈለገውን ያህል ወደ ስራ እንዳይገቡ አስተጓጉሏቸዋ ብለዋል።
ኹለተኛው ጥናት ከኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩንቨርስቲ ጋር በኢንቨስትመንት እድሎች፣ ተግዳሮቶች እና አማራጮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ ከጥናቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የከተማዉን ኢንቨስትመንት ለማሻሻል ቅድሚያ ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ዘርፎችን የተለዩ ሲሆን በቂ የመሬት አቅርቦት አለመኖር የመብራት ፣ የቴሌኮም ችግሮች የከተማዋ የኢንቨስትመንት ዋና ዋና ማቆዎች እንደሆኑም በጥናቱ መመላከቱን አክለው ገልፀዋል።
የኹለቱም ጥናት ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ተስፋዩ ለኢንቨስተሩ አመቺ የሆነው ምርት የትኛው እንደሆነ ለመጠቆም ጥናቶቹ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል። ጥናቱ ካመላከታቸው የመፍትሄ ነጥቦች መካከል ባለሀብቱን በተሻለ መንገድ ወደ ሰራ ለማስገባት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቁሟል።
እንደ አዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በቀጣይም ጥናቱን መነሻ በማድረግ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመወያየት ለባለሃብቱ ምቹ ማድረግ ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013



