የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥር 29/2013 የካቲት ወር የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ባደረገው መሰረት አንድ ሊትር ቤንዚን 25 ብር ከ82 ሳንቲም በመደረጉ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ከግማሽ አስከ እጥፍ ድረስ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
የነዳጅ ወጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ውጪ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የትራንስፖርት ዋጋ አዲስ ማለዳ ለማጣራት ባደረገችው ጥረት የዋጋ ጭማሪው ከግማሽ እስከ እጥፍ ድረስ መሆኑን ከተጓዦች አረጋግጣለች።
አዲስ ማለዳ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ ከሚጓዙ ተጓዦች ውስጥ ያነጋገረችው ወጣት ነጋ ዝናቤ የሥራ ቅጥር ለመከታተል ከአማራ ክልል ራያ ቆቦ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ 600 ብር እንደከፈለ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
ወጣቱ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው አዲስ አበባ የሥራ ቅጥር ማመልከቻ አስገብቶ ለመከታተል ሲል በእጥፍ የጨመረውን ዋጋ ከፍሎ ወደ አዲስ አበባ አንዲጓዝ እንዳስገደደው ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
ከራያ ቆቦ አዲስ አበባ በአገር የአቋራጭ አውቶብስ ዋጋ ሕጋዊ ታሪፍ 250 ብር ሲሆን በነዳጅ መጨመር ምክኒያት ባለንብረቶች ዋጋ ካልጨመራችሁ አንሄድም በማለታቸው ተጓዦች መፍትሔ እስከሚሰጥና ዋጋው ወደ ነበረበት እስኪመለስ ጉዟቸውን ለመሰረዝ የተገደዱ አንዳሉም ነው ወጣቱ የተናገረው።
የአጭር ርቀት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችም ከግማሽ ያላነሰ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል። አዲስ ማለዳ የአጭር ርቀት ዋጋ ጭማሪ መኖሩን ለማረጋገጥ ባደረገችው ማጣራት ከራያ ቆቦ ከተማ ደሴ መደበኛ ታሪፍ 100 ብር ሲሆን በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሰበብ 150 ብር ገብቷል።
የየካቲት ወር የነዳጅ ወጋ ክለሳ ጭማሪ መሳየቱን ተከትሎ በአንደዳንድ ከተሞች በገጠር ከተሞች ሳይቀር የዋጋ ጭማሪ መታየቱ የታዘበችው አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ትራንስፖረት ባለስልጣን በጉዳዩ ላይ ያለውን ምላሽ ጠይቃለች። የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይግዛው ዳኘው በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገ ምንም አይነት የታሪፍ ማሻሻያ ጭማሪ አንደሌለ ተናግረዋል።
ኃላፊው አንደሚሉት ከሆነ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክኒያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚሰሙት የሕዝብ ቅሬታ እውነት መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ባለስልጣኑ በግልጽ የተደረገ የታሪፍ ማሻሻያ ካልተደረገ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ባለስልጣኑ የሰማቸውን መረጃዎችና ቅሬታዎች በመያዝ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ በተደረገባቸው አካባቢዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር አንዲደረግ ለክልሎች እንደሚያሳውቅ ኃላፊው አመላክተዋል።
የትራንፖረት ሚኒስቴር በበኩሉ በአገር ደረጃ የተደረገ የታሪፍ ማሻሻያ ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በሕግ የሚያስጠይቅ ድርጊት ነው ብሏል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዳልካቸው ጸጋየ የዋጋ ጭማሪውን ሕገ ወጥ ተግባር ነው ብለውታል።
የክልልና የዞን ከተሞች የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ መሳየቱን እና አንዳንድ ክልሎችና ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የዋጋ ጭማሪውን እንዳቆሙ ሲሳስቡ አዲስ ማለዳ ታዝባለች። አንዳንድ ዞኖችም የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ አድርገዋል። የታሪፍ ማሻሻያ ካደረኩ ዞኖች መካከል ጋሞ ዞን አንዱ ነው። ዞኑ የታሪፍ ማሻሻ ያደረገው የተሸከርካሪ መለዋወጫ እና ነዳጅ በመጨመሩ ነው ብሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ይሄው የዋጋ ጭማሪ እየታየነው የሚል ጥቆማ የደረሰው የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ትራንስፖርት ባለስልጣን የታሪፍ ማሻሻያ ጥናት አድርጌ እስከማሳውቅ ድረስ ባለበት ይቆይ ብሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013



