የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተጓዥ ደምበኞቹ በበረራ ወቅት ለሚያቀርበው የምግብ አገልግሎት ለሚውሉ ግብዓቶች የሚደርገውን የአገር ውስጥ ግዥ ከ 10 በመቶ ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።
አየር መንገዱ በበረራ ወቅት ለተጓዥ ደምበኞቹ ለሚያቀርበው የምግብ አገልግሎት በዓመት 1 ቢሊዮን ብር ግዥ እንደሚያደርግ ገልጾ ከዚህ ውስጥ ግን ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች የሚያደርገው ግዥ 10 በመቶ ብቻ እንደነበር እና አሁን 25 በመቶ ለማድረስ ከአቅራቢዎች ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክተር በላይነህ አስፋው ገልጸዋል።
አየር መንገዱ የራሱ የሆነ እርሻ ስለሌለው የግድ አቅራቢዎች ያስፈልጉናል እኛም የምንሠራው ለትርፍ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሁም በምንፈልገው መስፈርት ከቀረበልን ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች የማንገዛበት ምክንያት የለም ብለዋል። የተለያዩ ለምግብ ፍጆታነት የምንጠቀማቸውን ግብዓቶችን በሦስት ዋና ዋና መስፈርቶች እንለካለን ሲሉ ተናግረዋል።
የመጀመርያው ተመሳሳይ የሆነ ጥራት ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ በቋሚነት ማቅረብ ነው ምክንያቱም በረራ መቆምም ሆነ መዘግየት ስለማይኖርበት ቋሚ አቅራቢ እንፈልጋለን ሦስተኛው ደግሞ የዋጋ ተመጣጣኝነት ነው የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ከነርሱ እንድንወስድ ተመጣጣኝ ዋጋ ካቀረቡ ከመግዛት ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።
እነዚህን ሁሉ አሟልተው ከሚገኙ አቅራቢዎች ጋር መሥራት ከቀጠልን ከ 25 በመቶ ከፍ ያለ ግዥ ልንፈጽም እንችላን ሲሉ ተናግረዋል። ከእኛ ጋር ለመሥራ ፍላጎት እና እውቀት ኖሯቸው አቅም ለሌላቸው አቅራቢዎች ግን በተባበሩት መንግሥታት የገንዘብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኩል 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው እና ከዚያም ያለው ለውጥ እና ውጤታማት ታይቶ 2 ሚሊየን ዶላር እንደሚጨመር ቃል መግባቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይብረሩ፣ ተፈጥሯዊ ማዕድ ይቋደሱ” ወይንም(Go-Organic) የሚል ዘመቻ ባለፈው ጥር 7/2013 መጀመሩ ይታወሳል። ዘመቻው አየር መንገዱ ለተጓዥ ደንበኞቹ የሚያቀርበውን የምግብ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊ እንደሚያደርግ የሚያስታውቅ ነው። ከአገር ውስጥ የግብዓት አቅራቢዎች የሚያደርገውን ግዥ በ15 በመቶ እንዲያሳድግ ያደረገው ምክንያት ተፈጥሯዊ ምግብ እና መጠጦች ለተጓዥ ደንበኞቹ ለማቅረብ በመወሰኑ እንደሆነም በላይነህ ተናግረዋል።
በላይነህ ዘመቻው አየር መንገዱ ካሉት 10 ሚሊዮን በላይ የበርካታ አገራት ዜግነት ያላቸው ተጓዦች አንጻር የኢትዮጵያ የሆኑ እና በኢትዮጵያዊያን የሚመረቱ ምግቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ ይረዳል ብለዋል። አክለውም በአየር መንገዱ ለሚጠቀሙ ተጓዦች ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን ሂደት የሚከታተል ራሱን የቻለ ክፍል ተቋቁሞለት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ የዓለም አገራት ለምግብ አቅርቦቱ ግብዓት የሚሆኑ እቃዎች በቀጥታ ከአምራቾቹ እንደሚገዛ በላይነህ ገልጸዋል። ከአምራቾቹ መግዛታችን ትክክለኛ የሆነ ጥሬ እቃ እንድናገኝ ይረዳናል ዋጋውም ከአምራች ሲገዛ ይቀንሳል ከቸርቻሪዎች እና ከጅምላ አከፋፋዮች አንገዛም ሁሌም ከአምራቾች ጋር ነው የምንወስደው ከእነሱ ጋር ችግር ከገጠመን ወይንም በምርቱ ላይ የጥራት ጥርጣሬ ካለን ሁሌም ኹለተኛ የምንይዘው አቅራቢ አለን ብለዋል።
አየር መንገዱ ከአውሮፓ ለሚገዛቸው እቃዎች ሌዥ በሚገኘው ካርጎ በኩል ወደ አገረ ውስጥ ያስገባል ከዱባይ ደቡብ አፍሪካ እና ቻይናም ለምግብ አገልግሎት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች እንደሚያስገባ አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ ማለዳ አገር ውስጥ ያሉ የዶሮ አርቢ እና አቅራቢ ማሕበራትን አነጋግራ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሸራተን አዲስ ላሉ ትልልቅ ተቋማት ካላቸው የፍላጎት መጠን እና እኛ አገር ያለው ዋጋ ከዶሮ መኖ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የዶሮ ዋጋ ስለሚጨምር እንዲሁም የተቋማቱ የፍላጎት መጠን ከፍ ያለ በመሆኑ አቅርበው እንደማያውቁ ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013



