አገር በቀል መድኀኒቶች ያለማግኘት ሥጋት እና የእንስሳትና የሰብል ዝርያዎች መጥፋት

Views: 3250

በሐዋሳ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና የሥራ ሒደት አስተባባሪ ደሳለኝ ዓለማየሁ፣ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ጉማሬዎች ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ያላቸው ሚና በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። አንዳንድ ሰዎች ሊፈጽሙት ቀርቶ ሊያስቡት የማይችሉትን ተግባር በሐዋሳ ሐይቅ ላይ መፈጸሙን ለአብነት ይናገራሉ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ በሐይቁ ውስጥ ከሚኖሩ የተለያዩ እንስሳት መካከል ጉማሬ የተለየ ባሕሪ አለው። በአንድም ይሁን በሌላ ጉማሬዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የሐይቁን ህልውና ላለመጉዳት የራሳቸውን ሚና የሚጫወቱ ያስመስላቸዋል። በሐይቁ ውስጥ የሚኖሩ ጉማሬዎች በሚቆስሉበት ጊዜ ወደ ሐይቁ ዳር ይወጣሉ። ይህም ሐይቁን ከቁስላቸው በሚወጡ ባክቴሪያዎች እንዳይበከል ያደርገዋል። ሲወልዱም ባልና ሚስቱ ብቻ ከመንጋው ተነጥለው ወደ ጥግ በመውጣት ነው። ሞታቸው እውን መሆኑን በተረዱ ጊዜም ወደ ውሃው ዳርቻ ወጥተው ሞታቸውን የሚጠባበቁ በመሆኑ ሀይቁ ውስጥ ሳይበሰብሱ አውጥቶ ሌላ ቦታ ለመጣል ያመቻል።

ለሀይቁ መበከል ምክንያት እየሆኑ ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎችና ተቋማት ናቸው። ሰዎች ከየቤቱ የሚያስወግዷቸው ፍሳሾች ወደ ሀይቁ እንዲገቡ መደረጉም አንዱ ነው፤ ይህም የሚሰነፍጥ ጠረን እንዲኖረው አድርጓል። ‹‹ከኢንዱስትሪዎች፣ ከጋራጅ፣ ከሆቴል፣ ከህክምና ተቋማትና ከየመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሾች ሀይቁን እየበከሉት ይገኛሉ›› እንደ ደሳለኝ ገለጻ። ሰዎች የጉማሬዎችን ያህል ለብዝሃ ሕይወት መጠንቀቅ ባለመቻላቸው በርካታ የሰብል፣ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል።

የብዝሃ ሕይወት መጎዳት በሐዋሳ ሀይቅ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሌሎችም አካባቢዎች በሰፊው የሚታይ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ባለፉት 100 ዓመታት በኢትዮጵያ 90 በመቶ የሰብል ዝርያዎች፣ እንዲሁም 50 በመቶ የእንስሳት ዝርያዎች በመጥፋታቸው አገር በቀል መድኀኒቶችን ማግኘት አልተቻለም።

በኢትዮጵያ ሰማንያ ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚመገበው ምግብ የመድኀኒትነት ይዘት ያላቸው መሆናቸውን የሚናገሩት ፈለቀ (ዶ/ር)፣ ባህላዊ መድኀኒት የሚያዘጋጁ በርካታ ተቋማት መድኀኒት የሚያዘጋጁት ህብረተሰቡ ከሚያውቃቸው ምግቦች መሆኑን አውስተዋል። ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው አካላት ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠታቸው ሰብሎቹ ለጥፋት ተዳርገዋል ነው የሚሉት።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በተለይ በየጊዜው እየተራቆተ ያለውን የብርቅዬ እንሰሳት መኖሪያ የሆነውን ደን መልሶ እንዲያገግም ባለመደረጉ ሰፊው የብዝሃ ሕይወት ሃብት አደጋ ላይ ሊወድቅ ችሏል። ከተለያዩ አዝርዕትና ከሆርቲ ካልቸር ሌላ የደን፣ የእጽዋት፤ የእንስሳትና የደቂቅ አካላት ብዝሃ ሕይወትም ትኩረት ተነፍጓቸው ቆይቷል። በዚህም አገሪቷ እነዚህን ዝርያዎች በማጣቷ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች።

ዝርያዎቹ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የተዛባ የባዮሎጂካል ዳይቨርስቲ (1995) መረጃ መሠረት፣ ከ30,000 የሚበልጡ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ባለፉት 100 ዓመታት 484 የእንስሳት ዝርያዎችና 654 ዓይነት ተክሎች ጠፍተዋል።

34,000 የእጽዋት ዝርያዎች እና 5,200 የአእዋፍ ዝርያዎች እንዲሁም፣ በግብርናው መስክ 30 ከመቶ የሚሆኑት ዋነኛ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። የተለያዩ የአትክልቶችና የእንስሳት ዝርያዎች ከምድር ገጽ እየጠፉ ያሉበት ፍጥነት እጅግ በጣም የሚያስደንቅ ነው የሚለው የተመድ ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ በ2050 ከሚመጡት የዝርያ ዝርያዎች መካከል 30 በመቶ ገደማ የሚሆኑት እንደሚጠፉ ዘግቧል። በተጨማሪም የሳይንስ ሊቃውንት በየዓመቱ 140 ሺሕ የሚሆኑ ዝርያዎች እየጠፉ መሆኑን አመላክተዋል ሲል ዋቤ አድርጓቸዋል።

በኢትዮጵያም በተመሳሳይ በርካታ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎች መጥፋታቸውን የሚያወሱት ፈለቀ፣ በተለይ በርካታ ለባህል ህክምና አገልግሎት የሚውሉ ዕፀዋትና ሰብሎች መጥፋታቸውን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የጠፉትን ዝርያዎች ዓለም ዓቀፉ ተቋማት ከሚናገሩት ባለፈ በዝርዝር ይህን ያህል ብሎ የኢትዮጵያን ብቻ ለይቶ መናገር እንደሚያስቸግር አውስተዋል። ኢትዮጵያ ለብዝሃ ሕይወት በሰጠችው አናሳ ግምት ሳቢያ በራሷ ያጠናችው ጥናት አለመኖሩን በመግለጽ።

በኢትዮጵያ 284 የአጥቢ እንስሣት፣ 861 የወፍ፣ 200 የዓሳ፣ 201 ተሳቢ፣ 324 የቢራቢሮ ዝርያዎች እንዳሉ ከብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከነዚህ ውስጥ 29 አጥቢ እንስሣት፣ 18 የወፍ፣ 10 ተሳቢ፣ 40 የዓሳ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው። 28 የቀንድ ከብት፣ 9 የበግ፣ 8 የፍየል፣ 7 የግመል፣ 6 የአህያ፣ 2 ውርንጭላና 7 የዶሮ ዝርያዎችም በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ከመቶ ዓመት በፊት ከእነዚህ የእንስሳት ዝርያዎች 50 እጥፍ በላይ ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደነበሩ የኢንስቲትዩቱ መረጃዎች ያሳያሉ። ጠፍተዋል ከተባሉት የእስንሳት ዝርያዎች መካከል የቀበሮ፣ የጭላዳ ዝንጀሮ፣ የንስርና ግንደቆርቁር ወፍ ዝርያዎች ይገኙበታል።

ከ400 በላይ የእጽዋት ዝርያዎችም መኖራቸውንም ተቋሙ የገለጸ ሲሆን፣ ከመቶ ዓመት በፊት ከነዚህ ከዘጠና በመቶ በላይ እጽዋቶች መኖራቸውን አሳውቋል። ጠፍተዋል ከተባሉት እጽዋት ዝርያዎች መካከል፣ የአካሽያ ዛፍ፣ የጥድ፣ ዝግባ፣ ዳማከሴ ዝርያዎች ይገኙበታል።

ባህላዊ መድኀኒቶቹ
በኢትዮጵያ በርካታ ለባህል መድኀኒትነት የሚያገለግሉ ዕፀዋት እንዲሁም ዕፀዋት አዋቂዎች ቢኖሩም ይህንንም ያህል በመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቷቸው በስፋት ሲሠሩ፣ ሲተዋወቁ አይስተዋሉም። ሆኖም በርካቶች የባህል ሕክምናን ሽተው ወደ ባህል ሐኪሞቹ ሲነጉዱ ይስተዋላሉ።

ከዕፀዋት መድኀኒቶችን፣ ቅባቶችን በምርምር በማውጣት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብዝሃ ሕይወት ኤንድ ፕላንት ባዮሎጂና ባዮዳይቨርሲቲ ትምህርት ክፍል፣ ከአሥር ልዩ ልዩ ዓይነት መድኀኒታዊ ዕፀዋት ለሰው ቆዳ የሚጠቅሙ አምስት የክሬም ቅባቶችን እንዳመረተ አዲስ ማለዳ ከትምህርት ክፍሉ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

በምርምርና በጥናት በተደገፈ እንቅስቃሴ የተመረቱት እነዚሁ ክሬም ቅባቶች ምንም ዓይነት መርዛማነት ወይም ጎጂ ባህሪ እንደሌላቸው ተረጋግጧል።
የትምህርት ቤቱ ማኔጅመንት አባልና የድኅረ ምረቃ አስተባባሪ ኤርሚያስ ልዑለቃል በጥናታቸው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዕፀዋቱ የተሰበሰቡት ከሰሜን ሸዋ አንኮበር አካባቢ ሲሆን፣ ዕፀዋቱ አንቲባክቴሪያል የሆነ አክቲቪቲ ያላቸው ወይም የባክቴሪያውን ዕድገት በተለያየ መጠን ማቆም የሚችሉ ሆነው እንደተገኙ፣ ከዚህም ግኝት በኋላ መርዛማ ናቸው? ወይስ አይደሉም? የሚለውን ለማረጋገጥ በአይጦችና ጥንቸሎች ላይ ፍተሻ ተደርጎ ውጤቱና ግኝቱ ጎጂነት የሌላቸው መሆኑን እንዳሳየ ተናግረዋል።

ክሬም ቅባቶች ከተመረቱባቸው ዕፀዋቶች መካከል የጦስኝ፣ የጥብስ (ሮዝመሪን)፣ ነጭ የባህርዛፍ ቅጠሎች ተጠቃሾች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አስተባባሪው አነጋገር፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ኤንድ ፕላንት ባዮሎጂና ባዮዳይቨርሲቲ ትምህርት ክፍል በፒኤችዲና በማስተርስ ደረጃዎች ባካሔዳቸው 69 ጥናቶች አማካይነት፣ በቁጥር ከ1032 በላይ የመድኀኒት ዕፀዋት ለማስመዝገብ ችሏል። ከተመዘገቡትም ዕፀዋት መካከል 80 በመቶ ያህሉ የተሰበሰቡት ከዋይልድ ኢንቫይሮመንት ማለትም ከዱርና ገደላገደል ከሆኑ አካባቢዎች ነው እንጂ ትኩረት ተሰጥቷቸው የተተከሉ ወይም የለሙ አይደሉም።

በመቶኛ ከተቀመጡት ዕፀዋት መካከልም 29 በመቶ የሚሆኑት ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸው ስራቸውን ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በጣም ትልቅ ኪሳራ እንደሚያስከትል፣ አንድ ሰው የአንድን መድኀኒት ዕፀዋት ሥሩን ነቅሎ ከተጠቀመ፣ ሰውዬው ድኖ ወይም ተፈውሶ ዕፀዋቱ ግን እንደሚጠፋ፣ በእርግጥ ሥራቸው መፍትሔ የሚሰጡ ልዩ ልዩ ዓይነት መድኀኒቶች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል ድንገተኛ የተባለው የዕፀዋት ስር አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ከአባታቸው ባህላዊ ህክምናን በመውረስ በሥራ ላይ የሚገኙት ብጽኢት አበበ፣ ከ20 ዓመት በፊት ባህላዊ መድኀኒት የሚቀመምባቸው ስራስሮች በአሁን ሰዓት አለመኖራቸውን ይገልጻሉ። ሲላ ተብላ በምትጠራው ወፍ አጥንት በርካታ መድኀኒቶች ይቀምሙ እንደነበር የሚናገሩት ብጽኢት፣ በአሁኑ ሰዓት ለመድኀኒትነት የሚጠቀሙባቸው የወፍ ዝርያዎችና ስራ ስሮች ባለመኖራቸው መድኀኒት ለመሥራት መቸገራቸውን ያወሳሉ።

“እናት ቁርጥ” በማለት የሚታወቀው ቅጥልና “ባለወተት ግንድ” የተሰኘው የሰንሰል ቅጠል በመጥፋታቸው ለ24 በሽታዎች የሚቀምሟቸውን መድኀኒቶች ለማግኘት ሰሜን ሸዋ አንኮበር ድረስ መሔድ ግድ እንደሆነባቸው ያወሳሉ። በዛም ቢሆን እነዚህ ተክሎች እየተመናመኑ መምጣታቸውን ነው የሚገልጹት። እነዚህን ተክሎች ለማምረት መሬት መጠየቅ የማይታሰብ መሆኑን የሚናገሩት ብጽኢት ለ20 ዓመት አባታቸው መሬት ጠይቀው ማግኘት አለመቻላቸውንና መንግሥትም ትኩረት እንዳልሰጠው ያወጋሉ።

የብዝሃ ሕይወት መቀነስ ምክንያቶች
እንደፈለቀ ገለጻ፣ የሰፈራ መንደሮች መዘርጋት፣ የንጽህና ንጥረ ነገሮችን በየጊዜው ወደ ከባቢ አየር መለዋወጥ፣ ተፈጥሯዊ ማለስለሻዎች ወደ የእርሻ መሣሪያዎች መለወጥ፣ ግብርናን በኬሚካል መጠቀም፣ የውሃ አካላትንና አፈር ብክለት፣ የመንገድ ግንባታ እና መገናኛዎች ለብዝሃ ሕይወት መመናመን ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
ከነዚህ ውስጥ 39 ከመቶ የሚሆኑት መኖሪያቸው በሰዎች ሰፈራ ምክንያት በመራቆታቸው፣ 36 ከመቶዎቹ በመንገድ ሥራና በኢንዱስትሪ ማስፋፊያዎች፣ 23 ከመቶዎቹ በአደን እና 2 ከመቶ የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ዝርያቸው መጥፋቱን ጥናቱ ያመላክታል።

ለብዝሃ ሕይወት መመናመን ምክንያት ከሆኑት መካከል መጤና ወራሪ የሆኑ ዝርያዎች በስፋት መሰራጨታቸው መሆኑን ኢንስቲትዩቱ በጥናት ማረጋገጡን ያስታወቀ ሲሆን፣ መጤና ወራሪ የሆኑ እንደ እንቦጭና ሌሎችም አረሞች በኢትዮጵያ በስፋት ሲበቅሉ ትኩረት ስላልተሰጣቸው አደጋ ሊያደርሱ መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በከባቢ አየር ውስጥ የሚከሰቱ ዓለም አቀፍ ለውጦች፣ ለምሳሌ የኦዞን ሽፋን ባዮሎጂያዊ ገራፊ (የፀሐይ ጨረር) ሳቢያ በሚከሰት የዓለም ሙቀት መጨመር ሌሎቹ ምክንያቶች መሆናቸውን አክለዋል።

መፍትሔ
እየተባባሰ ለመጣው ችግር እልባት ለማበጀት ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑም ታውቋል። በዚህም ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ከ80 በላይ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል የማራባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት ፈለቀ።

አገር በቀል የሰብል ዝርያዎችን በውጭ አገር የሰብል ዝርያዎች በመተካት ምርታማ መሆን ይቻላል የሚለውን የተዛባ አመለካከት ለማስትካከልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ፈለቀ ገልጸዋል። ለብዝሃ ሕይወት መመናመን ምክንያት ከሆኑት መካከል መጤና ወራሪ የሆኑ ዝርያዎች እንደ እንቦጭና ሌሎችንም አረሞች ለማጥፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ በቀጣይ ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ እንዲቻል ከአስፈፃሚ እስከ ፈፃሚ አካላት አስተባብሮ ለመሥራት ጠንካራ የአሠራር ስርዓት ተዘርግቷል። ለውጭ አገር ምርምር የሚፈለጉ የሰብል ዝርያዎች ተለይተው በኢንስቲትዩቱ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲተላለፉ እየተደረገ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች የባለቤትነት ጥያቄ እንዳይነሳባቸው በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የብዝሃ ሕይወት ስምምነት ከፈረመች በኋላ፣ 89 አዝርዕትና የሆርቲ ካልቸር ዝርያዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፤ ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ ናሙናዎችን መሰብሰቡን ገልጿል።

በተለይ በየጊዜው እየተራቆተ ያለውን የብርቅዬ እንሰሳት መኖሪያ የሆነውን ደን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። በመሆኑም ፓርኮች አካባቢ የልማት ሥራን በመሥራትና የግንዛቤ ማስጨበጫን በመፍጠር ሰፊውን የብዝሃ ሕይወት ሃብት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከተለያዩ አዝርዕትና ከሆርቲ ካልቸር ሌላ የደን፣ የእጽዋት፤ የእንስሳትና የደቂቅ አካላት ብዝሃ ሕይወትም ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com