መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየግንቦቱ ምርጫ፡- ተስፋ ወይስ ስጋት?

የግንቦቱ ምርጫ፡- ተስፋ ወይስ ስጋት?

በያዝነው ዓመት ግንቦት 28 የሚካሄደውን ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ፣ የካቲት 8 የእጩዎች ምዝገባ እና የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይም የምርጫ ዘመቻ መካሄድ ጀምሯል። የእጩዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 21 እንዲሁም የምርጫ ዘመቻው ደግሞ እስከ ግንቦት 23 ድረስ እንደሚካሄዱም ታውቋል።

ይሁንና እነዚህ ትልልቅ የምርጫው አንኳር ክዋኔዎች በይፋ በሚጀምሩት ዋዜማ እሁድ፣ የካቲት 7 ብዙዎችን ያስደነገጠ አሳዛኝ ድርጊት ተፈጸመ። በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፥ ቢሾፍቱ ከተማ፣ አድአ ምርጫ ወረዳ 1 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መዋቅር ሊቀመንበር የነበሩት ግርማ ሞገስ ለገሰ በጥይት ተመተው ሕይወታቸው የማለፉ ዜና ማኅበራዊውንም ሆነ መደበኛውን መገናኛ ብዙኀን በሰፊው ተዘግቧል።

ኢዜማም በተለይ ኦሮሚያን ጨምሮ በአንዳንድ ክልሎች እንደልብ ተንቀሳቅሶ አባላትን መመልምል፣ ደጋፊዎችን ማሰባሰብ እንዲሁም ድርጅታዊ መዋቅሩን ለመዘርጋት በተለይ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የበታች አመራሮች እንቅፋት እንደሆኑበት በተደጋጋሚ ማስታወቁ ይታወቃል። ሕይወቱን የተነጠቀው ግርማም ቢሆን ከመሞቱ ከዐሥር ቀናት በፊት በትዊተር ገጹ ላይ ‹‹ፖለቲካ ውስጥ ለገባ ሁሉ ነገር ቀላል እንደይሆን በደንብ አውቅ ነበር። ቀላል የማይሆነው ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቤ ጭምር እንደሆነም አውቃለሁ። በዚህም ልጆቼ ሳይቀር የፖለቲካ ይቅርብህ ተማጽኖ ለእኔ ቀላል አይደለም። የሚገርመኝ ግን የብልጽግና ቀንደኛ ደጋፊዎችና ካድሬዎች (የእኔ በግል ወዳጅ የሆኑ) ‹አደጋ ውስጥ እንዳትገባ ለምን ልጆችህን አርፈህ አታሳድግም። ፖለቲካውን ተወው› ይሉኛል።›› ሲል ማስፈሩ ታውቋል።

ብዙዎች በድርጊቱ የተደናገጡ ሲሆን ገና በዚህ ጊዜ እንዲህ አሳዛኝ ዜና መስማት ከጀመርን፥ የምርጫው ሒደት ሞቅ እያለ በሚሄድበት ጊዜ ደግሞ ምን እንሰማይሆን ሲሉ ከወዲሁ ምርጫው ስጋት እንደሆነባቸው አልሸሰጉም። ከምርጫው ጋር በተያያዘም የአገር ኅልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ሲሉ ከወዲሁ ፍርሃታቸውንም አክለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች ‹‹ግድያው ሆን ተብሎ የተደረገ፤ እንደወረደ የቀድሞ ኢሕአዴግ/ሕወሓት ‘ስታይል’ ነው›› ሲሉ ጠንካራ ለሆኑት የገዢው ፓርቲ ተቀናቃኞች መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ሲሉ መጪው ጊዜ ቀላል እንደማይሆንም ጨምረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኢዜማ የአባሉን ግንድያ በተመለከተ መንግሥት ወንጀለኞችን አድኖ ሕግ ፊት ባስቸኳይ እንዲቀርብ፣ ቀደም ሲል ግርማን ጨምሮ በአባላቶቹ ላይ ወከባና ማስፈራሪያ ያደርጉ የነበሩት የቢሾፍቱ የፓርቲና የመንግሥት ኀላፊዎች የምርመራው አካል እንዲድሆኑ እንዲሁም ጉዳዩን ቀድሞ እንዲያውቁ የተደረጉት የክልሉም ሆኑ የፓርቲው ከፍተኛ ኀላፊዎች ግድያውን እንዲያወግዙ ጠይቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ሰኞ ተጀመረውን የምረጡኝ ዘመቻ በማስመልከት ብልጽግና ፓርቲ በይፍ የምርጫ ማንፌስቶውን እና የምርጫ ምልክቱን በፕሬዘዳንቱ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲመርቅ አድርጓል። ዐቢይ በሚቀጥለው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የብልጽግና ማኒፌስቶና እሳቤ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም ዋናው ፍላጎታችን ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ነው ሲሉ ንግግር አሰምተዋል። ‹‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ማለት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉም በነጻነት የሚሳተፍበት፣ በሐሳብ ልዕልና የሚመረጥ ወይንም የሚወድቅበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።›› ሲሉም አክለዋል።

ዐቢይ ተፎካካሪ ብለው ለሚጠሯቸው ፓርቲዎች ፖሊሲ እየጻፍን ነው ያለነው የሚሉትን በማጣጣል ድርሰት እንጂ ፖሊሲ ሊሆን አይችልም ብለዋል። ይሁንና ተፎካካሪዎች ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው እንዲወዳደሩ፣ የትብብርና የፉክክር መንፈስን እንዳናበላሽ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች መታገዝ የሚገባቸውን ነገር ማገዝ ይኖርብናል ሲሉ ለፓርቲያቸው አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢዜማ’ም በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ በተቀመጠው መሰረት ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢ በሚገኙ የምርጫ ወረዳ መዋቅሮቹ የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምሯል። በአዲስ አበባ የኢዜማ ከፍተኛ ኃላፊዎች የተሳተፉበት ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ተሳፋሪዎች ኢዜማን በተመለከተ ያላቸውን ማንኛውንም ጥያቄ እንዲጠይቁ እና ከአመራሮቹ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ የምርጫ ቅስቀሳ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ሆኖም ቅስቀሳው ሊደረግባቸው ከታሰቡ ቦታዎች አንደኛው በሆነው ሽሮ ሜዳ አካባቢ «የምርጫ ቅስቃሳ ስለመጀመሩ አናውቅም» ባሉ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ቅስቀሳው ተስተጓግሏል።

የሆነው ሆኖ የእጩዎች ምዝገባም ሆነ የምረጡኝ ቅስቀሳው መጀመር ብዙዎችን አሳስቧል፣ አስጨንቋል፣ ስጋት ላይም ጥሏል። በየዕለቱ ብዙ ምርጫ ነክ ውርክቦች፣ ዘገባዎች፣ ጫጫታዎች፣ ጩኸቶች እንደሚሰሙ ግን ከወዲሁ ብዙኀን ያምናሉ። ትልቁ ጥያቄ ምርጫው ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወይም ጨርሶውኑ ወደ እንጦሮጦስ ይወስዳት ይሆን የሚለውን ጊዜ መልስ የሚሰጥበት ይሆናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች