መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛበትግራይ ‹‹የግድያዎቹ አንድምታ››

በትግራይ ‹‹የግድያዎቹ አንድምታ››

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቀናት በትግራይ የተከሰቱት ኹለት የተለያዩ ግድያዎች ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተዋል።
የመጀመሪያው ግድያ የተፈጸመው ኀሙስ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሰማዕታት ቀን ታስቦ በሚውልበት የካቲት 12 ሲሆን በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩና በትግራይ ማዕከላዊ መንግሥት የሕግ ማስከበር እርምጃ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አሪድ ግቢ ውስጥ ተከታትለው እንዲያጠናቅቁ የተደረጉ ወደ ኹለት ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎች ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ተለያዩ ከተሞች ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ በተደረገበት ወቅት ነው። በዚህ በመመለስ ሒደት ውስጥ በአንደኛው አውቶብስ ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ኹለት ሴት እና አራት ወንድ ተማሪዎችን ጨምሮ የመኪናው ረዳት እንዲሁም ኹለት የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ከዘገበው በኋላ በመደበኛም መገናኛ ብዙኀንም ሆነ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ትኩረት ስቧል። ጥቃት የተሰነዘረበት አውቶብስ በመቃጠሉም ምክንያት የሰለባዎቹ ቤተሰቦቻቸው አስክሬን ማግኘት ባለመቻላቸው መርዶው ብቻ እንደተነገራቸውም ተሰምቷል። ድርጊቱም ልብ ሰባሪ ሆኖ አልፏል።

ከጥቃቱ የተረፉ ተማሪዎችን እንዲሁም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዘዳንት የሆነውን አብርሃሌ አረፋይኔ’ን ዋቢ ያደረገው ዘገባው ጥቃቱ በደረሰ ዕለት መንግሥት በተለይ የከፍተኛ ትምህርት እና ሳይንስ ሚኒስትር እንዲያውቁት መደረጉ ታውቋል። በዚህም መሰረት ተማሪዎቹ ተጨማሪ ድጋፍ እንያገኙም ተደርጎ ከሌሎች መሰል ጥቃቶች እንዲታደጉ ተደርገዋል ተብሏል።

ጥቃት ያደረሱት የአርሶ አደር ልብስ እና የትግራይ ሚሊሻ የደንብ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን ከጥቃቱ የተረፉት በተማሪዎች ጨምረው መግለጻቸውን ዋናው የመረጃ ምንጭ ጠቁሟል።
ኹለተኛው ግድያ ደግሞ የተፈጸመው ተማሪዎቹ ላይ ጥቃት ከደረሰ ከአንድ ቀን በኋላ ቅዳሜ፣ የካቲት 20 ከመቐለ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ሐወኒ በምትባል ትንሽ ከተማ ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመበት የማነ ንጉሥ ላይ ነው። የማነ የሚታወቀው ሕወሓት’ን በሕዝባዊ እምቢተኝነት ለማስወገድ ወጣቶችን በማስተባበር ግምባር ቀደም ሚና በመጫወቱ ሲሆን ፈንቅል የተባለውን የወጣቶች ንቅናቄ በጊዜያዊ በሊቀመንበርነትም መምራቱ ይታወቃል።

ብዙዎችን እንዲገረሙም እንዲታዘቡም ያደረጋቸው ጉዳይ፥ ኹለቱም ግድያዎች ከመንግሥት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አለሰማቱ ሲሆን በዚህም ምክንያት ግድያዎቹ ለብዙ መላምቶች ተጋልጠዋል፤ የብዙኀን መነጋገሪያ አርዕትም ሆነው ሰንብተዋል።
የተማሪዎቹን ግድያ በተመለከተ ሐዘንን ከመግለጽ ባሻገር ስለ ገዳዮቹ ብዙም ብዥታ ሐሳቦች አልተንጸባረቁም። መንግሥትን ለማሳጣት እና በሕዝበ ዘንድ ያለውን ተቀባይነትም ሆነ ትምምን ሆን ብሎ ለመሸርሸር የታቀደ ከሕዝብ የመነጠል ሥራ ሲሆን ፈጻሚዎቹም የሕወሓት ‹ርዝራዦች› ናቸው በሚል ከሞላ ጎደል አንድ ዓይነት ድምጽ ተሰምቷል። የየማነ’ን ግድያ በተመለከተ ግን ብዙ መላምቶች ተንጸባርቀዋል፤ የፖለቲካዊ አንድምታም ተሰጥቶት በሰፊው መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።

ጉዳዩን በደንብ እናውቃለን የሚሉ አንዳንዶች፥ የማነ ሐወኒ ከተማ የተገኘው ለወገኖቹ የምግብ እርዳታ ለማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የማነ በርግጥ ከሕወሓት ውድቀት ለማትረፍ የግል ዝናና ክብር ለማግኘት ሲሯሯጥ እንደሆነ ተከራክረዋል። ከኹለቱ የተለየ አቋም የሚያንጸባርቁት በበኩላቸው መንግሥት ለሴራ ፖለቲካ ሲል አስገድሎታል ሲሉ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፤ ምንም እንኳን ድምጻቸው ጎልቶ ባይሰማም። ምክንያቱ ደግሞ የማነ የተገደለው ብቻውን ሳይሆን ከኹለት ጥበቃ ሲያደርጉለት ከነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር መሆኑ ከመንግሥት ይልቅ የሕወሓት ታጣቂዎች ግድያውን ፈጽመዋል ወደሚል መላምት እንዲያደላ አድርጎታል።

የሆነው ሆኖ፤ የእነዚህ ግድያዎች አንድምታ ምንድን ነው ምላሽ የሚያስፈልገው ወሳኝ ጥያቄ አስነስተዋል። ምንም እንኳን መንግሥት የሕግ ማስከበር ተልዕኮዬን ፈጽሚያለሁ ቢልም፥ አሁንም ትግራይ ሰላምና መረጋጋት እንደራቃት ያሳያል። ይህ ደግሞ በዚህ መልኩ ከቀጠለ የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል የበለጠ ክልሉን ወደ አለመረጋጋት እንዲሁም ኢትዮጵያንም ወደ ተራዘመ የርስበርስ ግጭት ይመራታል የሚሉት ስጋታቸውን አልደበቁም፤ መንግሥት የኅብረተሰብን ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ ምኑን መንግሥት ሆነ በማለት ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ሐሳባቸውን ያጋሩ እንዲሁ። ከግድያዎቹ ጋር በተያያዘም አንዳንዶች በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የተለማመድነውን የሰዎች መሞትን በትግራይም እንድንለምደው ሊደረግ ይሆን ሲሉ ስላቅ አዘል ስጋታቸውን በሰፊው በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ አጋርተዋል።
የብዙኀኑ ስጋት ግን ‹‹እስከመቼ ኢትዮጵያ ባለመረጋጋት ውስጥ ትቀጥላለች፤ ልክ እንደ የመን እና ሶሪያስ ላለመፈራረሷ ምን ዋስትና አለን?›› በሚሉ ምላሽ አልባ ጥያቄዎች መብሰልሰላቸውን ቀጥለዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች