ሰኞ የካቲት 8/2013 በይፋ የተጀመረው የምርጫ ቅስቀሳ ባሳለፍነው ሳምንትም ቀጥሎ ፓርቲዎች ከአባላት እና ደጋፊዎቻቸው ጋር በዛ ባለ ቁጥር የተገናኙበት ነበር። ምርጫ ቅስቀሳ በምርጫ ሂደት ወሳኝ ከሚባሉ ሂደቶች አንዱ ነው። ስለሆነም ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መሠረታቸውን አድርገው፣ የምርጫ ሕጎችን በሚገባ ተገንዝበው፣ ለራሳቸው ሕገ ደንብ ጭምር በመገዛት እንዲያከናውኑ ይጠበቃል። መጪው ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት መሠረት የሚጥል እንዲሆን ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ፣ ከወዲሁ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄድና በቀጣይም ምን መልክ መያዝ ይኖርበታል የሚለውን በሚመለከት የአዲስ ማለዳው ጥሩነህ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ አጀንዳ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ የወራት እድሜ ብቻ በሚቀራት በዚህ ወቅት የምርጫ ዋነኛ ተዋናይ ለሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻው ውድ ጊዜ ነው። ምክንያቱም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር ከሚያደርጉበት አጀንዳዎች መካከል የመጀመሪያው የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ በመሆኑ ነው።
ስድስተኛው የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ መደረግ የነበረበት በ2012 ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ አልችልም የሚል ሐሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረቡ፣ ምክር ቤቱ ምርጫውን በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ወደ 2013 እንዲሸጋገር ወሰነ። ያንን ተከትሎ ምርጫው የፊታችን ግንቦት 28/2013 እንዲካሄድ የመጨረሻ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።
ምርጫ በኢትዮጵያ የሚሰጠው ዋጋ ከዚህ ቀደም የነበሩትን እንደማሳያነት ብናነሳ በርካታ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ፍትሐዊና እውነተኛ ምርጫ ተካሂዷል ለማለት የሚያስችል አንዳልሆነ ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ አገራዊ ምርጫዎች ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ‹ምርጫ ተካሂዷል› የሚለውን መስፈርት ለማሟላት እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ የሚኖርበት የምርጫ ሜዳ እንዳልነበረው በማንሳት ይወቀሳል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ኢሕአዴግን አክስሞ በመሪነት ላይ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ከኢሕአዴግ መክሰም በተጨማሪ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸውንና ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች ባለማሟላታቸው 26 ፓርቲዎችን መሰረዙ የሚታወስ ነው። ይህም በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁጥር ወደ 54 ዝቅ አድርጎታል።
እነዚህ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተሰጣቸው 54 ፓርቲዎች የፊታችን ግንቦት 28/2013 ለሚደረገው ምርጫ ተፎካክሮ ለማሽነፍ የሚያስችላቸውን የሐሳብና የፖሊስ አማራጭ የሚያቀርቡበት ሜዳ የሚፈቀደው ከየካቲት 8/2013 እስከ ግንቦት 23/2013 ባሉት ቀናት ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰርት ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳን መጀመር በሚቻልበት እለት፣ ማለትም ባሳለፍነው የካቲት 8 ቀን 2013 ጀምረውታል።
የ1997 ምርጫ ቅስቀሳን በምልሰት
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የ1997 ምርጫ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንደ ትልቅ ምዕራፍ የታየበት የምርጫ ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። በወቅቱ በነበሩ የጦፉ ውይይቶችና መድረኮች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረው በአንድ ግንባር መምጣትና በምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደነበር ብዙዎች የሚያስታውሱት ነው።
ገዥው ፓርቲ በወቅቱ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በከፈተው ነፃነት ተፎካካሪዎች በሚዲያዎች ላይ የፈለጉትን ሐሳብ ያቀረቡበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ በማዋጣት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉት የፌዴራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ምርጫ 1997 ከተደረጉት አምስት ምርጫዎች በመጠኑም ቢሆን የተሻለ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ በማድረሳቸው በምርጫ ውጤቱ ላይ ከቀደሙት ምርጫዎች መሻሻል ማሳየቱን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚያነሱት ሲሳይ፣ በወቅቱ ይደረጉ የነበሩ የምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ ግን በይዘታቸው ደረጃ ክፍተት እንደነበረባቸው አስታውሰዋል። እንደ ክፍተት ብለው ከጠቀሱት ጉዳይ መካከል፤ ጫፍ የረገጠ የብሔር ክፍፍልን የሚያባብስ ነበር ይላሉ፤ ሲሳይ ምርጫ 1997ን ሲስታውሱ።
የምርጫ ቅስቀሳ ጅማሮ
የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻ በይፋ የተጀመረው ባሳለፍነው የካቲት 8/2013 ነው። በእለቱ ምርጫ ቅስቀሳ ከጀመሩ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ኢዜማ በእለቱ ቅስቀሳውን የጀመረው በመዲናይቱ አዲስ አባባ ሲሆን የቅስቀሳ ስልቱም ለከተማው ማኅበረሰብ ነፃ የትራንስፖርት አገልገሎት በመስጠት ነበር።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (አዜማ) ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የጠቀመጠለትን የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢ የሚገኙ የምርጫ ወረዳ መዋቅሮች የምረጡኝ ቅስቀሳውን ጀምሯል። ኢዜማ ያደረገውን የምርጫ ቅስቀሳ በተመለከተ የነበረውን ሁኔታ አዲስ ማለዳ የኢዜማ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ጋር ቆይታ አድርጋለች።
በአዲስ አበባ የኢዜማ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ነፃ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ተሳፋሪዎች ኢዜማን በተመለከተ ያላቸውን ማንኛውንም ጥያቄ እንዲጠይቁ እና ከአመራሮቹ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ቅስቀሳው እንደጀመረ ያስታወሱት ዘላለም፤ በቅስቀሳው ከሕዝቡ የተገኙት ምላሾች መልካም እንደነበሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ቅስቀሳ ሊደረግባቸው ከታሰቡ ቦታዎች አንዱ በሆነው ሽሮሜዳ አካባቢ «የምርጫ ቅስቀሳ ስለመጀመሩ አናውቅም» ባሉ የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ቅስቀሳው ሳይደረግ መስተጓጎሉን አንስተዋል። ይህም መንግሥት በሁሉም ቦታ ሙሉ ዝግጅት እንደሌለው አመላካች ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ ስልቱን በሦስት መደቦች ከፍሎ መጀመሩን ዘላለም ገልጸዋል። የመጀመሪያው በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሆን ኹለተኛው በክልል እና በወረዳ ደረጃ መሆኑን ነው ዘላለም የጠቆሙት። በሦስቱም ክፍሎች ባሳለፍነው የካቲት 8/2013 ፓርቲው ቅስቀሳ መጀመሩን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ወደፊትም ፓርቲው በዚሁ የምርጫ ቅስቀሳ ክፍል እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
ሌላኛው የምርጫ ቅስቀሳውን በእለቱ የምርጫ መወዳደሪያና ማኒፌስቶውን ይፋ በማድረግ የተቀላቀለው ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ነው። የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ ላይ በርካታ ሐሳቦች አንስተዋል። ካነሷቸው ሐሳቦች መካከልም በፓርቲዎች እና በሌሎችም ዘንድ ትችት ያስከተለ ንግግር ይገኝበታል። ይህም የብልጽግናን ፖሊሲ በማወደስ የሌሎቹን በማጣጣል የተነሳ ቅስቀሳ ነው የሚሉት አልጠፉም።
‹‹ሰነድ ድርሰት አይደለም፣ ማኒፌስቶ ድርሰት መሆን አይችልም። ከአንድ ዓመት በላይ ዝርዝር መረጃ ሲሰበሰብ ከምሁራን፣ ከወጣቶች ከተለያዩ የኅብረሰተብ ክፍሎች ጋር ስንወያይበት ቆይተን ለአምስት ዓመት የምንገባው ቃል ኪዳንና ለዐስር ዓመት የሚኖረን የብልጽግና ፍኖታችን ተናበውና ተመሳክረው ይህችን አገር ካለችበት ሁኔታ ወደሚቀጥለው ማሸጋገር የሚችሉ ትላልቅ ሐሳቦች በውስጡ የያዘ ነው።›› ሲሉ ነበር በእለቱ የተናገሩት።
አክለውም ‹‹ከአንድ ወር በኋላ እኔም የትምህርት ፖሊሲ አለኝ፣ እኔም የጤና ፖሊሲ አለኝ የሚል ኃይል ቢኖር ያ ድርሰት እንጂ ፖሊሲ መሆን አይችልም። ፖሊሲ በሰፊ የመረጃ ማሰባሰብ፣ በመተንተን፣ የባለፈውን ችግር በመመርመር መገምገም ከዚያም መማርና ነገን በብሩህ ተስፋ መሰነቅና መንደፍ የሚጠይቅ ስለሆነ እኛ ያዘጋጀናቸው ፖሊሲዎች በብልጽግና የውድድር የተቀመጡ ማኒፌስቶ ሐሳቦች በእያንዳንዱ ዕቅዳችን ውስጥ ያሉ፣ መላው አባላችን የሚያውቃቸው፣ ከሕዝባችን ጋር እንደ አስፈላጊነቱ የተወያየንበት፣ ወደፊትም በዚሁ አግባብ እየተወያየን የምናሰፋውና የምናሳድገው እንዲሁም የምንተገብረው ሰነድ ነው›› ብለዋል።
በዚህ ንግግራቸው መካከል ‹‹ከአንድ ወር በኋላ እኔም የትምህርት ፖሊሲ አለኝ፣ እኔም የጤና ፖሊሲ አለኝ የሚል ኃይል ቢኖር ያ ድርሰት እንጂ ፖሊሲ መሆን አይችልም።›› የሚለው ንግግር ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።
በዚህ ንግግር ቅር ከተሰኙ ፓርቲዎች መካከል ኢዜማ አንዱ መሆኑን የኢዜማው ዘላለም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ዘላለም ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ የምርጫ ቅስቀሳ የተሳሳተ አካሄድ በገዥው ፓርቲ የተጀመረ ነው ብለዋል። ይህን የሚሉትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹ድርሰት› የሚል ሥያሜ ገና ከወዲሁ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ፖሊሲዎች ሥም መለጠፋቸው ነው።
ዘላለም እንደሚሉት የምርጫ ፉክክሩ ገና በቅጡ ሳይጀመር የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር የሌሎችን ፓርቲዎች ሥም በማጥፋት መጀመሩ ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለፖለቲካ አካሄድ ስለማይጠቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትምህርት መውሰድ አለባቸው ሲሉ ነው ዘላለም የተናገሩት።
የፌዴራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) የምርጫ ቅስቀሳ ጅማሮ መልካም የሚባል መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ሲሳይ እንደተናገሩት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ድርሰት› በሚለው ንግግር የተከፉ ፓርቲዎች ካሉ አትንካኝ አይነት አካሄድ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ንግግር የሌሎች ፓርቲዎች ፖሊስ በጥናትና በተግባር ያልተፈተሸ እንዲሁም የሕዝቡን ችግር የማይፈታ ነው የሚል ሐሳብ የያዘ ንግግር መሆኑን ያስታወሱት ሲሳይ፣ ‹‹አንዱ የዴሞክራሲ ጸጋው ሐሳብን በነፃ መግለጽ ስለሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመከፋት ይልቅ ፖሊሲያቸው በጥናት ላይ የተመሠረተና የአገሪቱን ችግር የሚፈታ መሆኑን በማሳየት ለሕዝብ ማቅረብ የተሻለ ነው›› ሲሉ ጠቁመዋል።
እንዳትነካኝ አይነት አካሄድ የዴሞክራሲ መገለጫ ሊሆን እንደማይችል የጠቆሙት ሲሳይ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዙ ጊዜ በገዥ ፓርቲ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲነገሩ የመደንገጥ ሁኔታዎች እንደሚኖር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ፓርቲዎች የሌላውን ፓርቲ ፖሊስ ‹አይረባም ወይም ውዳቂ ነው› በማለት መተቸት ይችላሉ ብለዋል። ይሁን እንጂ ፓርቲዎች በቅስቀሳ ጊዜ በሥነ ምግባር ደንብ መሠረት መመራት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
ቀጣዩ የቅስቀሳ አቅጣጫ
የምርጫ ቅስቀሳ ገና በጅምር ላይ ሳለ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ስልት ምን መምሰል አለበት የሚለው ጉዳይ ለምርጫ አጠቃላይ ሂደት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ እውን ነው። ይህን ጉዳይ የሚያጠናክር ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በሚቀጥለው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የብልጽግና ማኒፌስቶና እሳቤ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም ዋናው ዓላማ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ እንዲሆን ማስቻል ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ማለት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉም በነጻነት የሚሳተፍበት፣ በሐሳብ ልዕልና የሚመረጥ ወይንም የሚወድቅበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው ያሳሰቡት።
አክለውም የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ከወዲሁ ምርጫ ማሸነፍ ተስፋ የለውም፣ ከምርጫ መውጣት ይሻላል ብለው የሚያስቡ ካሉ በምርጫ መወዳደርና ሐሳባቸውን መሸጥ እንደሚሻል መክረዋል። ‹‹ዛሬ ለ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ በእጩነት ስትመዘገቡ ወይም እንደ ፓርቲ እጩዎቻችሁን ስታስመዘግቡ ከፊታችን ያለው መንገድ ከፊል ተስፋ፣ ከፊል ስጋትን አዝሎ እንደሚጠብቀን ለሁሉም ግልፅ ነገር ይመስለኛል።›› ብለዋልም።
የኢዜማው ዘላለም በበኩላቸው ኢዜማ ዘመናዊና የሠለጠነ የምርጫ ቅስቀሳ ለሌሎሌ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር ማሳያ የሚሆን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ስልት እንዳስጀመረ በማስታወስ ወደፊትም በሠለጠነ መንገድ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘላለም አክለውም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ በሐሳብ አሸናፊነት ላይ የተመሠረተ እና አማራጭ ፖሊሲ በማቅረብ ላይ ያተኮረ ሆኖ መጠናቀቅ እንዳለበት ጠቁመዋል። ሐሳብን ሸጦ የሕዝብ ልብ መግዛት ብቸኛው የዴሞክራሲ ስልት ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የእጩዎች ምዝገባ በይፋ መጀመሩን በማስመልከት በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ቀጣዩን ምርጫ ከሂደቱ ጀምሮ በጋራ በማሳለጥ ውጤቱን እውን ለማድረግ ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰብሳቢዋ በመልዕክታቸው ፓርቲዎች በአገራችን የተለያየ አካባቢ እጩዎችን በማስመዝገብ፣ በእጩነት በመመዝገብ የምርጫ ዘመቻውን ምዕራፍ ሲጀምሩ ለሂደቱ የሚጠቅም በጎ እሴት ለመጨመር፣ በችግር ፈቺነት በጋራ ለመሥራት፣ የፖለቲካ ጥቃትን አሮጌ ባህል እለት እለት ከመድገም እንዲቆጠቡ መክረዋል።
‹‹ለዘመናዊ እና ሥልጡን ውድድር ራሳችንን ለማደስ፣ ከምንም በላይ የዜጎችን ባለሥልጣንነት በማክበር እንዲሆን እያሳሰበኩ፤ በዚህ አስፈላጊ እና ትልቅ ትርጉም ባለው ሥራ የሁላችንንም አብሮነት እና የእያንዳንዳችንን ድርሻ ሳንረሳ በበጎ መንፈስ የምርጫ ውድድሩን እንጀምር።›› ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሲሳይ በበኩላቸው፣ ቀጣዩ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ከመወነጃጀል ይልቅ የዴሞክራሲ መንገድን የተከተለ ፖሊሲ ለመራጩ በማቅረብ ሕዝብ ያመነበትን እንዲመርጥ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፖርቲዎች በመሠረታዊነት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው ቅስቀሳ ማድረግ አለባቸው ብለዋል። እነሱም የመጀመሪያው የጨዋታ ሕጉን ማክበር ሲሆን ፓርቲዎች የምርጫ ሕጎችን በሚገባ ተገንዝበው ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ኹለተኛ ፓርቲዎች ለራሳቸው ሕገ ደንብ መገዛት ሲሆን የፓርቲ አመራሮች ለሕገ ደንቦቻቸው ተገዥ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል። ሦስተኛው ለዴሞክራሲ ወይም ለሐሳብ የበላይነት ተገዥ መሆን መሆኑን የጠቆሙት ሲሳይ ግጭት፣ ጥላቻና ሥም ማጥፋት ላይ ያተኮረ የምርጫ ቅስቀሳ እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን በበኩላቸው ፓርቲዎች ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብን ማክበረ ሁኔታ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። የቅስቀሳ መሠረቱ ፓርቲዎች ለሕዝቡ ፖሊሲያቸውን ማሳየት መሆን እንዳለበት ሰብሳቢዋ የጠቆሙ ሲሆን፣ በቅስቀሳ ወቅት የፓርቲዎችን ሥም ማጥፋት፣ ግጭት ቀስቃሽ ተግባር ማድረግና የፓርቲዎችን ክብር መንካት እንደማይቻል ገልጸዋል።
የተጠቀሱትን መርሆዎች ተላልፎ የተገኘ ፓርቲ ላይ ቦርዱ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ሰብሳቢዋ አሳሰበዋል። እርምጃው እጩ እስከመሰረዝ እንደሚደርስ ተመላክቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013



