ሲቪል ማኅበራት በኢትዮጵያ – ታሪካዊ ዳራ፣ የሕግ መሠረት፣ እና በፓርላማ የሕግ ማውጣጥ ሥራ ውስጥ የሚኖራቸው ሚና

0
1180

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም ላያንጸባርቅ ይችላል።

በሚኪያስ በቀለ (አምቦ ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1. የሲቪል ማኅበራት ምንነት
ሁሉን የሚያስማማ የሲቪል ማኅበራት ትርጉም ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። ከቦታ ቦታ እና ከጊዜ ጊዜ፣ ብሎም ከተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች አንጻር የተለያዩ ትርጎሞች ሲሰጡት ቆይቷል – የሲቪል ማኅበር። ነገር ግን የሲቪል ማኅበር እንደ ተደራጀ ተቋምነቱ ካለው ቦታ እና ዓላማ አንጻር ለመረዳት ይቻላል። የሲቪል ማኅበር ከመንግሥት ብሎም ለትርፍ ከተቋቋሙ የንግድ ተቋማት የተለየ ነው። የሚቋቁምበት ዓላማ የአባላቱን ወይም የተለዩ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ወይም የአጠቃላይ ማኅበረሰቡን ፍላጎት እና/ወይም እሴት ለማረጋገጥ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት የሲቪል ማኅበራት ማኅበረሰቡን በአንድ በኩል እና መንግሥትን እና የንግዱ ዘርፍ በሌላ በኩል የሚያገናኝ ድልድይ ተብሎ ይወሰዳሉ።

2. የሲቪል ማኅበራት የሕግ መሠረት
የሲቪል ማኅበራት ሕልውናቸውን የሚያገኙት “የመደራጀት መብት” ከሚባል የሰብኣዊ መብት ነው። ይህ የሰብኣዊ መብት መሠረታዊ የሰው እሴት ተደርጎ የዓለም ዐቀፍ እውቅና የተቸረ፣ እና በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ብሎም በሀገራት ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የተካተተ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የዓለም ሃገራት አባል የሆኑበት የዓለም ዐቀፍ የፖለቲካ እና የሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 22 ላይ ማናቸውም የስምምነቱ አባል ሃገራት ዜጎች በሠራተኛ ማኅበራት የመታቀፍን ጨምሮ ለሕጋዊ ዓላማ የመደራጀት መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ዜጎች ሕጋዊ ዓላማ ላለው ማናቸውም ዓይነት ጥቅም መደራጀት እንደሚችሉ መብት ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራትን በዝርዝር የሚያስተዳድር ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሀገሪቷን የሕግ ስርዓት ለማዘመን ስድስት ጥራዝ ሕጎችን ወደ ሃገሪቷ ባስገቡበት ጊዜ ነበር። ከስድቱ ጥራዝ ሕጎች አንዱ የሆነው እና በ1952 የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ በርእስ 3 ክፍል 2 ላይ የሲቪል ማኅበራት የሚያስተዳድሩ ድንጋጌዎች አካትቷል። በመቀጠልም የሲቪል ማኅበራት ስለሚመዘገቡበት አካሔድ በ1958 ዓ.ም ደንብ ወጥቶ ነበር።

ከዚህ በኋላ የሲቪል ማኅበራትን ለማስተዳደር የወጣው ሕግ በ2001 (አዋጅ ቁጥር 621) ሲሆን የሲቪል ድርጅቶች ለመመዝገብ እና ለማስተዳደር እራሱን የቻለ የኤጀንሲ መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ ሲሠራ ነበር። ይህ አዋጅ ለዓመታት ዘርፉን ለማቀጨጭ ጥቅም ላይ መዋሉ ሲነገርለት ቆይቷል። የሲቪል ማኅበራት የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዜግነት ያላቸው በሚል የሚከፍለው ይህ አዋጅ፤ የሀገር ዐቀፍ የሲቪል ማኅበራት ከውጪ ለጋሾች የሚያገኙት ገንዘብ ከአጠቃላይ በጀታቸው 10 በመቶ እንዳይበልጥ የተጣለው ገደብ አንዱ ዘርፉን አፋኝ ለመሆኑ የሚያሳይ ነጥብ ተደርጎ ይነሳ ነበር። ሌላው የሚነሳው ነጥብ የውጪ ዜግነት ያላቸው የሲቪል ማኅበራት በልማት ላይ እንጂ በፖለቲካዊ አራማጅነት ሥራዎች ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚጥለው ገደብ ነበር። መንግሥት ለዚህ ያነሳ የነበረው ክርክር ፖለቲካ ለዜጎች ብቻ የሚተው ጉዳይ መሆኑን እና የውጪ ዜግነት ያላቸው የሲቪል ማኅበራት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ያሉ ሥራዎች ላይ ሊሳተፉ አይገባም የሚል ነበር። የሲቪል ማኅበራት አስተዳደርያዊ ወጪ ከአጠቃላይ በጀታቸው 30 በመቶ መብለጥ እንዳይኖርበት የተቀመጠው ክልከላም በሲቪል ማኅበራቱ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ነበር። የሲቪል ማኅበራትን የሚመዘግበው እና የሚቆጣጠረው የመንግሥት የኤጀንሲ መስሪያ ቤት ስለ ምዝገባ እና ፍቃድ ስረዛ የነበረው የተለጠጠ ሥልጣን እና ውሳኔውም በፍርድ ቤት የማይከለስ መሆኑም ሌላው የሕጉን ጨቋኝነት ለማሳየት የሚነሳ ጉዳይ ነበር።

ለዓመታት የዘለቁ ሰላማዊ ብሉም በኀይል የታጀቡ ሕዝባዊ ተቃውሞችን ተከትሎ በኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገው የሥልጣን ሽግሽግ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ድርጅቱ ሊቀ መንበርነት፣ ቀጥሎም ወደ ሃገሪቷ መሪነት ብቅ አሉ። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የሀገሪቱን ፖለቲካ ለመክፈት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ከወሰዷቸው ግንባር ቀደም ሥራዎች ውስጥ አንደኛው ጨቋኝ የተባሉ ሕጎችን ማሻሻል ነበር። ለዚህም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር በነጻነት እና ሙያዊ ሥነ ምግባር ተመስርቶ የሚሠራ “የሕግ አማካሪዎች ጉባኤ” እንዲቋቋም ተደረገ። ይህ የሕግ ባላሙያዎች ስብስብ የመንግሥት ፖሊሲዎን ወደ ሕግ ከመቀየር ባሻገር የሚሻሻሉ ሕግጋትን ቅደም ተከተል የማወሰን ሥራም ይከውናል። ጉባኤው ካረቀቃቸው ሕጎች ውስጥ በቀደምትነት የሚቀመጠው ይህ አፋኝ የተባለው የሲቪል ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621 የሚሽር አዋጅ ነው። አሁን ላይ በተሻለ ለሲቪል ማኅበራት ነጻነት የሚሰጥ አዲስ አዋጅ (ቁጥር 1113) በ2011 ተረቅቆ እና ጸድቆ ተፈጻሚ ሆኗል።

3. የሲቪል ማኅበራት በኢትዮጵያ – ታሪካዊ ዳራ
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ብሎም ማኅበራዊ መዋቅሮች የረዥም ዘመናት ታሪክ አላቸው። በዚህም ምክንያት ኢ-መደበኛ የሆኑ የሲቪል ማኅበራት በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ለረዥም ዘመናት ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበር። በሀዘን ጊዜ ማኅበረሰቡ የሚረዳዳበት “እድር”፣ በገንዘብ የሚተጋገዙበት “እቁብ”፣ አለመግባባቶች የሚፈቱበት “ሸንጎ”፣ የሥራ ክፍፍልና መረዳዳት የሚደረግብት “ደቦ” እና የመሳሰሉ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ጉዳዩች የሚስተናገዱባቸው ኢ-መደበኛ የሲቪል ማኅበራት ለረዥም ዓመታት ነበሩ። እንቁ ይመር የተባሉ ተመራማሪ ከኢሕአዴግ በኋላ ለሚኖር ሽግግር ሊሳተፉ ስለሚችሉ ባለድርሻ አካላት ባጠኑት ጥናታቸው ላይ የአቅም ግንባታ ሚንስትርን በመጥቀስ በ2004 ዓ.ም 39 ሚሊዮን የእድር አባላት እና 21 ሚሊዮን የእቁብ አባላት እንደነበሩ ይገልጻሉ።

መደበኛ የሆኑና በመንግሥት የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበራት ማበብ የጀመሩት በ1930ዎቹ አካባቢ የከተማዎችን ማቆጥቆጥ እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ እድገቶችን ተከትሎ በንጉስ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን ጄፈሬ ክላርክ የተባሉ በዘርፉ ላይ ብዙ ያጠኑ ባለሙያ ሲቪል ማኅበራት በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ስላላቸው ድርሻ ባጠኑበት ጥናታቸው ላይ ይገልጻሉ። በ1966 ዓ.ም የተፈጠረውን ድርቅ እና ርሃብ በእርዳታ አቅርቦት ላይ የተመሰረቱ የሲቪል ማኅበራት እንዲያብቡ ምክንያት ሆኖ ነበር። ተቋማቱን መደበኛ ሆነውና ተመዝግበው መሥራት የጀመሩት የ1952 ዓ.ም የፍትሃ ብሔር ሕግ መውጣጥ ተከትሎ ነበር። እንደ ክላርክ ጥናት እንደ ንግድ ምክር ቤት እና የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ያሉ የባለሙያ ማኅበራት በተሻለ ነጻነት በንጉሱ ጊዜ ሲሰሩ የነበሩ ቢሆንም፣ በደርግ ዘመን ግን ነጻነታቸውን አጥተው የመንግሥት መጠቀሚያ በመሆን ታምኝነታቸውን፣ የሙያ ስብዕናቸውን ብሎም ቅቡልነታቸው አጥተዋል።

4. የሲቪል ማኅበራት በሕግ የማውጣጥ የፓርላማ ሥራ ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለው ሚና እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ
ሀ) በረቂቅ ሕጎች የሚወክሉት ማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎት እንዲካተት የሚደረግ ውትወታ
የሲቪል ማኅበራት እንወክለዋለን የሚሉት የማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎት አለ። ስለዚህ የሚወጡ ሕጎች ይህንን የማኅበረሰብ ፍላጎት የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ሊሰሩ ይችላሉ – የሲቪል ማኅበራት። ይህም ማለት የሲቪል ማኅበራቱ እንደ ባለድርሻ አካል በረቂቅ ሕጎች ውስጥ የሚወክሏቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ፍላጎት እንዲካተተ ውትወታ ሊያደርጉ ይችላሉ። ለዚህ ሁለት አይነት አካሄዶች አሉ።

የመጀመሪያው ረቂቅ ሕጎች ወደ ምክር ቤት ከተላኩ በኋላ የሲቪል ማኅበራት ሕጎቹ ላይ በሚወያዩ እና በማጽደቅ ውስጥ የሚሳተፉ የፓርላማ አባላት ላይ ጫና የማድረግ፣ የመደለል ሥራ ነው። የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እንዳስረዱት ቋሚ ኮሚቴዎቹ ከሲቪል ማኅበራት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ተቋማዊ ግንኙነት የላቸውም። ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀረቡት የተለያዩ ጫናዎችን እና ማባበሎችን ለማስወገድ ነው። እንደ ምክር ቤቱ አባል እና የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ከሆነ የሲቪል ማኅበራት ኢ-መደበኛ ባልሆነ አካሄድ አባላቱ በተለያዩ ረቂቅ ሕጎች ላይ አቋም እንዲይዙ በሚል የሚደረግ የማባበል አካሔዶች የሉም። በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ለምክር ቤት አባላት ተጽህኖ የሚያደርጉበት አጋጣሚ አይታይም። ከምክር ቤቶቹ ይልቅ ኢ-መደበኛ የሆኑ ውትወታዎች የሚታዮት በምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያዎች ላይ ነው። የምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ ለዚህ ጸሁፍ አቅራቢ ሲያስረዱ በረቂቅ ሕጎች ላይ በቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ረቂቁን ባመነጨው አካል መካከል ስምምነት ባልተፈጠረባቸው ነጥቦች ላይ ወደ መደበኛ ጉባኤው በሚመለሰው የውሳኔ ሃሳብ ላይ መስተካከል እንዲደረግ ሕጉን ካመነጨው አካል በባለሙያዎች ላይ ውትወታዎች ይኖራል።

በኹለተኛ ደረጃ የሲቪል ማኅበራት በቋሚ ኮሚቴ በሚዘጋጁ ሕዝባዊ ውይይቶች (Public Hearing) የሚወክሏቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ፍላጎቶች በመወከል ቀርበው አስያየታቸውን ሊያቀርቡ ይችላሉ። አስተያየታቸውን የሚያቀርቡበት ዓላማ አንድም ሃሳባቸው በረቂቅ ሕጎች ውስጥ እንዲካተት ብሎም በቦታው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት (የተለየ ቋሚ ኮሚቴ አባላት) እና ረቂቁን ካቀረበው አስፈጻሚ አካል የመጡ አስረጂዎችን አስተያየቶች ለመቅረጽ ሊሆን ይችላል። የቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ምርመራ ከተላከላቸው በኋላ ከሚሰሯቸው ሥራዎች አንዱ እና ዋነኛው ሕዝባዊ ወይይቶች ማሰናዳት እና መጥራት ነው። የቋሚ ኮሚቴዎች ለተሳትፎ የሚያደርጉት ጥሪ በሚዲያ (ለአጠቃላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ የማኅበረሰብ ክፍሎች) ወይም በቀጥታ (የቋሚ ኮሜቴዎች ባለድርሻ ናቸው ብለው ለሚያስቧቸው ግለሰቦች እና ማኅበራት) ነው። ስለዚህ የሲቪል ማኅበራት ተከታትለው በሚዲያም ሆነ በቀጥታ ጥሪ ሲቀርብላቸው ቀርብው የሚወክሉት የማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎት በረቂቅ ሕጎች ውስጥ እንዲንጸባረቅ ጫና ማድረግ ይችላሉ። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የተለያዩ የሲቪል ማኅበራትን ኃላፊዎች እና የቋሚ ኮሚቴ ሊቃነ-መንበራት ከማነጋገር እንደተገነዘበው የቋሚ ኮሚቴዎች የተለዩ ረቂቅ ሕጎችን አስፈጻሚዎች እና ከመንግሥት ጋር ንክኪ ያላቸውን ማኅበራት በብዛት እንደ ባለድርሻ አካላት ቆጥረው እንደሚጠሩ፣ ብሎም የሲቪል ማኅበራት ሕዝባዊ ውይይቶችን ችላ የማለት አካሄድ አለ።

ለ) ሙያዊ ምክር
የምክር ቤት አባላት በሁሉም ሕግ ይዘት ላይ የተለየ እውቀት ሊኖራቸው አይችልም። በተቃራኒው የሲቪል ማኅበራት ደግሞ በየዘርፋቸው የተለየ እውቀት ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ የሲቪል ማኅበራት የሚወክሉት ማኅበረሰብ ፍላጎት ከማንጸባረቅ በዘለለ በረቂቅ ሕጎች ላይ የባለሙያ እይታም ሊያቀርቡ ይችላሉ። ይህ የሙያ ትንታኔ የሚቀርበው ለቋሚ ኮሚቴዎች ሊሆን ይችላል። በዚህም የምክር ቤት አባላት ስለ ረቂቅ አዋጆች በተሻለ እንዲያውቁ እና በውይይቶች ላይ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ እንዲያደረጉ ብሎም ድምጽ ለሚሰጡበት አቋምም አቅጣጫ ሊያሲዙ ይችላሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የሙያ ድጋፍ የሚያገኙት በራሳቸው ወይም በጽ/ቤቱ ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች ነው። የራሳቸው ባለሙያ ያላቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ውስን መሆናቸውን የምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ ይናገራሉ። ቋሚ ኮሜቴዎች ረቂቅ ሕግ ከተመራላቸው በኋላ ረቂቁን ካሰናዳው የሚንስትር መስሪያ ቤት ከሚመጡ አስረጂዎች ጋር ውይይት ከማድረጋቸው በፊት በጽ/ቤቱ ከሚገኙ ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚጠይቁ እና ለአስረጂ የሚቀርቡ ጥያቄዎችም እንዲሰናዱ እንደሚደረግ የጽ/ቤቱ የሕግ ባለሙያ ያስረዳሉ። የጽ/ቤቱ ሕግ ባለሙያ የቋሚ ኮሚቴዎች በተለየ ረቂቅ ሕግ ላይ የባለሙያ ምክር ለማግኘት በሚል የሲቪል ማኅበራት በቀጥታ የጠሩበትን አጋጣሚ አያስታውሱም። የአንድ ቋሚ ሊቀመንበር፣ ለሙያዊ ምክር ለሲቪል ማኅበራት ጥሪ እንደማያደርጉ ሳይሸሽጉ፤ የሲቪል ማኅበራት የራሳቸው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሙያዊ ግንዛቤ አለን በሚሏቸው ጉዳዩች ላይ ሕዝባዊ ውይይት በሚደረግበት ጊዜ የመምጣጥ ተነሳሽነቱ የላቸውም በሚል ባለሙያዎችን እና የሲቪል ማኅበራትን ይተቻሉ።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here