መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊው ክሽፈት

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊው ክሽፈት

የፌደራል መንግሥቱ በሕወሓት ላይ ወሰድኩት ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በሦስት ሳምንታት ውስጥ አጠናቅቂያለሁ ቢልም በዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ ረገድ ግን ከባድ ሽንፈት እንዳጋጠመው የብዙዎች እምንት ነው፤ ሰሞነኛ መነጋገሪያም ሆኗል። የሰሞኑ ከምዕራባውያን እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት አካባቢ የሚሰሙት መግለጫዎች ይህንን ሐሳብ ያጠናክራሉ።

ኀሙስ፣ የካቲት 26 የተባበሩት መንግታት ድርጅት በትግራይ ግጭት ከባድ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽመዋል ሲል በድርጅቱ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚሼል ባሽሌት ማስታወቃቸው የመገናኛ ብዙኀን በሰፊው ዘግበውታል። ኮሚሽነሯ በግጭቱ የተሳተፉ አካላት የጦር ወንጅል እና በሰብኣዊነት ላይ ከባድ ጥፋቶች እንደተፈጸሙ ከትግራይ የሚወጡ ያልተቋረጡ እና ተዓማኒ ሪፖርቶች ያመለክታሉ ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል። ተሳታፊ ናቸው ያሏቸው አካላት ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ሕወሓት፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ክልል ኀይሎች እና ሚሊሻዎች በጦር ወንጀልነት እና በሰብኣዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ሊጠየቁ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚሼል ባሽሌት ጠንካራ አቋም በተንጸባረቀበት ዕለት፥ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በተጠራው በዝግ ስብሰባም ላይ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየቱ ታውቋል። በሰብሰባው ላይ ሩሲያ፣ ቻይና እና ሕንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግባት አይቻልም ማለታቸውን ተከትሎ ስብሰባው ያለስምምነት መበተኑ ከሰዓታት በኋላ ታውቋል።

ከምክር ቤቱ ሰብሰባ በኋላ የሩሲያ መንግሥት የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ‹‹በአንዲት ሉዓላዊት መንግሥት የውስጥ ጉዳይ መግባት ሉዓላዊነትን መዳፈር ነው›› የሚል መግለጫ ማውጣቱ መዘገቡ በጸጥታው ምክር ቤት ያለ ውጤት መበተን ያረጋግጣል። ቻይና እና ሕንድም ‹‹ኢትዮጵያ የራሷን ችግር ራሷ መፍታት ትችላለች›› ሲሉ አቋማቸውን መግለጻቸው፥ ከስብሰባው ውጤት ብዙ ይጠብቁ የነበሩትን የሕወሓትን ደጋፊዎች እንደላስደሰተ መረዳትም ተችሏል።

ሌላው፥ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ዲፕሎማሳዊ ጫና ከአዲሱ የባይደን አስተዳደር እየተደረገ ሲሆን የኹለቱ አገራት ፍጥጫ በማኅበራዊም ሆነ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በሰፊው ትኩረት ስቧል። በዚህ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በግላቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያደርሱ የነበረው ጫና ተጠናክሮ፥ በ‹ዋይት ሃውስ› እና ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ማስወጣት ደረጃ መድረሱ ነው።

የ‹ዋይት ሃውስ› መግለጫ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከኬኒያው አቻቸው ኡኹሩ ኬኒያታ ጋር በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ በሥልክ መወያየታቸውን ሲያስታውቅ፤ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ደግሞ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ የኤርትራ ሠራዊትን እና የአማራ ልዩ ኀይልን ከትግራይ ማስወጣት እንዳለበት አሳስቧል።

በርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ለተሰሙት መግለጫዎች ጠንከር ምላሽ ሰጥቷል። ስለኤርትራ ሠራዊት ያለው ነገር ባይኖርም፥ ሉዓላዊነቴን የተዳፈረ ነው ሲል አስታውቋል። በትግራይ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከጸጥታ ማስከበርም ሆነ ከሰብኣዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ የአቅሙን ያክል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል።

የሆነው ሆኖ የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕወሓት ላይ የተቀናጀውን ድል በዲፕሎማሲው መስክ ሊደግመው እንዳልቻለ ነው። መቻል አለመቻል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ሽንፈቱን አምኖ መቀበል አለበት ሲሉ ጠንካራ ትችትም ያሰሙ አሉ። ብዙዎች በትግራይ ጦርነት እንደመካሄዱ ብዙ ንጹሃን ዜጎች ለከፋ ሰብኣዊ ጥሰቶች እንዲሁም ቀውሶች ሊዳረጉ እንደሚችሉ ቢገልጹም፥ ከሕወሓት ዲጅታል ሠራዊት እና ዳያስፖራ ደጋፊዎች በሚቀርቡ ጠንካራ ክሶች ምክንያት ተፈጸሙ የተባሉ ወንጀሎችን ለማመን ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

የዲፕሎማሲውን የኢትዮጵያ ሽንፈት በተመለከተ፥ ብዙዎች ከዲፕሎማቶቹ ብቃት ጋር የሚያያይዙት ሲኖሩ የአገሪቱ ዲፕሎማሲ መመራት ያለበት በፖለቲካ ሹመኞች ሳይሆን ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መሆን አለበት ሲሉም መከራከሪያ ሐሳባቸውን ያቀረቡም አሉ። መፍትሔም መንግሥት በትግራይ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የታላቁን ሕዳሴ ግድብን ጭምር በተመለከተ በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባዋል፤ ከዘርፈ ብዙ ሙያዎች የተወጣጡ ሰዎችን (‹ተንክ ታንክ›) በማቋቋም አጠቃላይ ዲፕሎማሲውን ማሻሻል ይገባል ሲሉም ምክረ ሐሳብ ያቀረቡም ይገኙበታል። የተበላሸውን የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ ገጽታ ለመለወጥ ዲፕሎማሲው ላይ መሥራት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አንዳንዶች አበክረው መክረዋል፤ ሰሚ ጆሮ ካለ!


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች