ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የዓለም ዐቀፍ የቴሌኮሙኔኬሽን ልማት ጉባኤ ዝግጅት አኅጉራዊ ስብሰባዎችን እንድትመራ መመረጧን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለጉባኤው ስኬት ኢትዮጵያ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገች ሲሆን የጉባኤውን አኅጉራዊ ስብሰባዎች በሊቀመንበርነት እንድትመራም ተመርጣለች።
ስብሰባውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አህመዲን መሀመድ ለጉባኤው መሳካት ውጤታማ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
በአኅጉራት መከካል የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ፣ ፍሬያማና ቀልጣፋ የዝግጅት ሥራዎች እንዲከናወኑ ኢትዮጵያ ትሠራለች ያሉት ሊቀመንበሩ፣ በኮቪድ ተፅዕኖ ውስጥ ስኬታማ ሥራ ይሠራልም ተብሏል፡፡
የጉባኤው አስተናጋጅ አገር አኅጉራዊ ስብሰባዎችን እንድትመራ መደረጓ ለኮንፈረንሱ የሚደረጉ ዝግጅቶች በፍጥነት እንዲከናወኑ እድል ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል።
ኢትዮጵያ 2021ንዱን የዓለም ዐቀፍ የቴሌኮም ልማት ጉባኤ የምታስተናግድ ሲሆን ከተሳታፊ አገራት የቀረቡ ኮቪድ የደቀናቸው ስጋቶችን የተመለከቱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማቅረቧንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከተለያዩ የዓለም አገራት የተወጣጡ 250 ሰዎች የተሳተፉበት ስብሰባ በበይነ መረብ እንደተካሄደና፤ በኮቪድ 19 ምክንያት ጉባኤው በአካል ይካሄድ ወይንም በበይነ መረብ የሚሉት አማራጮች ላይ አገራት የተለያዩ ሐሳቦችን እያንፀባረቁ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013


