መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየኢትዮ - ኤርትራውያን ጥምረት

የኢትዮ – ኤርትራውያን ጥምረት

ሰሞነኛ መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ አንዳንድ ከተሞች በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራዊያን በጋራ የተካኬዱት ደማቅ የድጋፍ ሰልፎች ይገኙበታል።
ረቡዕ፣ መጋቢት 1 በዋሽንግተን ዲሲ እና በካናዳ፣ ቶሮንቶ እና ከአቅራቢያቸው ከተሞች የተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ትዕይነተ ሕዝብ አካሂደዋል። እንዲሁም ኀሙስ በቤልጄም፣ ብራስልስ ተመሳሳይ ደማቅ ሰልፍ ተካሂዷል፤ በኒዎርክ የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት እና በካናዳ ካሊጋሪ ተመሳሳይ ሰልፎች መካሄዳቸውም ታውቋል።

ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠሩት የዲሲ ሰልፈኞች፥ በኮከብ አልባው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማዎች በማውለብለብ እንዲሁም በብዛት በእንግሊዝኛ የተጻፉ መፈክሮችንም ይዘው ታይተዋል። የሰልፎቹ ዋና ዓላማ ለአገራችን ድምጽ ለመሆን ሲሆን፥ በተለይ ኢትዮጵያ ለአሜሪካም ሆነ ለምዕራቡ ዓለም አጋር እንጂ ጠላት አልደለችም ሲሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር እያደረጉ ያለውን ጥረት አውግዘዋል። በሰላም ማስከበር ዙሪያ ኢትዮጵያ ያበረከተችውን አስተዋጽዖ በተመለከተ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ለምታደርገው ያላሰለሰ ሰላም የማስፈን ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሊያግዛት ሲገባ ተገቢ ያልሆነ ጫና ሊያሳድር መሞከሩን አውግዘዋል። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ እንጂ የውጪ ኀይል ፈጽሞ ሊሆን አይችልም ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓት ለፈጸመው ወንጀል በዓለም ዐቀፍ ሕግ ሊጠየቅ ይገባል ሲሉም ሰልፈኞቹ ተደምጠዋል። ሕወሓት በአማራ፣ ኦሮሞ፣ በሲዳማ፣ በአኝዋክ እና በሌሎች ብሔሮች ላይ የዘር ማጥፋት ግድያ ፈጽሟል ሲሉ ተቃውሟቸውን በከፍተኛ ድምጽ አሰምተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ደብዳቤም አስገብተዋል። በደብዳቤው ላይ ሕወሓት ኢትዮጵያ ካካሄደችው ለውጥ በኋላ የፈጸማቸውን ወንጀሎች ዘርዝረዋል፤ የፌደራል መንግሥቱም በተደጋጋሚ ላቀረበው የሰላም ጥሪ ሕወሓት ምላሽ መንፈጉንም አስታውሰዋል። በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ወንጅልንም በዝርዝር አብራርቷል።

በቀጠናው ሰላም ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና እንደምትጫው የሚያትተው ደብዳቤ፥ ለአብነትም ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱማሊያን ጠቅሷል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ላይ አሜሪካንን ጨምሮ ጫና ውስጥ ለመክተት የሚደረገው ሙከራ ቀጠናውን ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑን በመጠቆም ጉዳዩ ሊጤን ይገባወል ይላል፤ ደብዳቤው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ‹‹በዋሽንግቶን ዲሲ ~ አሜሪካ የምትኖሩ ወገኖቻችን በጠንካራ የሃገር ፍቅር ስሜት፤ የኢትዮጵያን ትክክለኛ እና ወቅታዊ ገፅታ አስመልክቶ፤ ለሰፊው ዓለም እውነታውን ያስተጋባችሁበት ታሪካዊ ሰልፍ በእጅጉ የሚደነቅ ሲሆን ለፈፀማችሁት አኩሪ ተግባር ከልብ እናመሰግናለን፤ ደግሞም ኮርተንባችኋል።›› ሲሉ ሰልፈኞችን ሲያመሰግኑ የቀደማቸው አልነበረምል። በተመሳሳይም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑት አዳነች አበቤ ‹‹ታላቅ ምስጋናችን እና አክብሮታችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ›› በማለት በአገር ሉዓላዊነት ሲነካ እኛ ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይንት የፖለቲካ አቋም ልዩነት ቢኖረንም በጋራ እንቆለን ሲሉ አድናቆት የተሞላበትን ምስጋና ለሰልፈኞቹ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ሰልፉ በተካሄደበት በተመሳሳይ ቀን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አንቶኒ ብሊንከን ለአሜሪካ ምክር ቤት በትግራይ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል። ወንጀሉ ከማውገዝ ባሻገር፥ ብሊንከን ብሊንከን በትግራይ ውስጥ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች ታዓማኒ መረጃዎች መኖራቸውንም ለምክር ቤቱ በመግለጽ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ሊያስቆም ይገባል ብለዋል። ብሊንከን በትግራይ ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም የጎረቤት ክልል የአማራ የሚሊሻ ከትግራይ መውጣ አለባቸው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ያደረጉት አዲሱ የአሜሪካ የባይደን አስተዳደር፥ በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ፖሊሲ ማራመዱ በጣም አስገርሟቸዋል። ሌሎች ግን የሚጠበቅ ነው ሲሉ ኢትዮጵያዋውያን በኅብረት አቋማቸውን በማስተባበር ግፊት በማድረግ ሊወሰዱ የታቀዱ እርምጃዎችን ማኮላሸት እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ሁሉ የተለዩት ደግሞ ሕወሓት’ን ከመቃብር አውጥቶ ነፍስ ዘርቶ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ሰማይን እንደመንካት ይቆጠራል ሲሉም እየተደረጉያሉ ዘመቻዎች የትም አይደርሱም ሲሉ አጣጥለውታል።
በተመሳሳይ በሌሎች ክፍለ ዓለማት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መንግሥትን የሚደግፉ፤ ሕወሓትን የሚያወግዙ እና ኀያላን አገራት እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የሚያሳስቡ ሰልፎች እንደሚካሄዱ በሰፊው ማኅበራዊ ትስስር መረቦች ላይ እየተጋሩ እንደሚገኙም ታውቋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች