ዳውላውን ሳይሆን አህያውን!

0
798

በየዓመቱ የካቲት 29 ቀንን ጠብቆ የሚከበረው የሴቶች ቀን በዓለማችን በተለያዩ አገራት የተለያየ መልክ አለው። ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ግን አሁንም የሴቶች የእኩልነትና መብት ጥያቄዎች በቂ እንዲሁም ተገቢ መልስ ያገኙ አለመሆናቸው ነው። ለዚህ መልስ ለማግኘት ወንዶችንና አባታዊ አስተዳደርን በጥላቻ መመልከትና መውቀስ ይስተዋላል። በአንጻሩ ያሉትም በተቃራኒ ሆነው የሴቶችን መብትና እኩልነት ጥያቄ እንደቅንጦትና ወንዶችን በመጥላት የመጣ አድርገው ይቆጥሩታል። መቅደስ ቹቹ ይህን በማንሳት አህያውን ትቶ ዳውላውን እንደሚባለው እንዳይሆን፣ አህያ የተባለውን አገልጋዩ ስርዓት ላይ እናተኩር በሚል ይህን ሐሳብ አጋርተዋል።

የሴቶች ቀን የካቲት 29ን ጠብቆ በየዓመቱ ይታሰባል። እለቱ የሴቶች ቀን ተብሎ መከበሩ ለምን ነው ብለን በበይነ መረብ የሚገኙ መረጃዎችን ስናስስ ከምናገኛቸው መልሶች መካከል አንደኛው የሴቶችን ስኬት ለማክበር ነው ይላል። ይህም በየመስኩ በአስቸጋሪ ሁኔታና ለሴቶች ምቹ ባልሆነ ስርዓት ውስጥ አልፈው ውጤታማ መሆን የቻሉ ሴቶችን ለመዘከርና ለእነርሱ ለመዘመር የሚል ሐሳብ ያለው ነው።

በተያያዘም የሴቶች ቀን የሥርኣተ ጾታ እኩልነትን በሚመለከት ቅስቀሳ ለማድረግና እንቅስቃሴው የደረሰበትን ደረጃ ለመቃኘት የሚል ምላሽ ይገኛል። በዚህም ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸውን ተቋማት ‹ምን ሠራችሁ?›፣ ሊመሰገኑ የሚገባቸውን ‹በርቱ!› ለማለት ይህን ቀን የሚጠቀሙበት አሉ።

ከዚህ ውጪ በሆነ መልኩ ደግሞ ከጠቃሚ ምክክሮችና ‹የት ደረጃ ላይ ነው ያለነው?› ከሚለው ግምገማ ውጪ ያሉ ረብ የለሽ ድግስና ሆሆታዎች እንዳሉም ልብ ይሏል! እንደውም አንዳንድ ወንድሞች ሲቀልዱ፣ ‹እንደው በቀናችሁ እንኳ እኛ ሽር ጉድ ብንልላችሁ ምን አለ!› ይላሉ፤ የሴቶች ቀን ድግስን ለማሳመር ደፋ ቀና የሚሉ የመሥሪያ ቤት ባልደረቦቻቸውን።

ከዚህ ሁሉ በተቃራኒ ደግሞ በሴቶች ቀን መከበር ጭራሹን የማይስማሙ አሉ። ‹የወንዶች ቀን መች ይከበርና ነው!› በሚል ንጽጽራዊ ዕይታ የሚቃወሙት ሲኖሩ፣ ለሴቶች አንድ ቀን ብቻ ሰጥቶ መዘመር ዋጋ የለውም ብለው በጽኑ ያምናሉ።
ያም ሆነ ይህ፣ የሴቶች ቀን ወይም የሴቶች ወር በሚል በሚጠራው ሰሞን የሴቶች ጉዳይ አጀንዳ ይሆናልና የተለያዩ ሐሳቦችና እይታዎች በተለያየ አቅጣጫ የሚፈሱበት ወቅት ነው። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ታድያ በበኩሌ ተከታዮን ሐሳብ ላነሳ ወደድኩ።
እንደሚታወቀው የሴቶች መብት ተሟጋቾች ከድጋፍ ይልቅ ወቀስ የሚደርስባቸው ጊዜ ብዙ ነው። በተለይም ‹ፌሚኒዝም› የሚለው ቃል ገና ሲጠራ ፊታቸውን ጭፍግግ የሚያደርጉ ያጋጥማሉ። አንዳንዴም የሴቶች የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ከውጪ የመጣ አጉል ባህል የሚያደርጉትም አሉ። ‹‹ደኅና ያገለግሉና አንገት ይደፉ የነበሩ ሴቶቻችንን አጉል ‹መብት፣ እኩልነት› እያላችሁ አበላሻችሁብን!› የሚሉም አልጠፉም።

በአገራችንም በሴቶች ሥምና ጉዳይ ተደራጅተው የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ፣ የበጎ አድራጎት ወይም የሲቪክ ማኅበር የሆኑ ድርጅቶች፣ ማኅበራትም ሳይቀሩ ሲናገሩ የምንሰማው ያንን ነው። ‹አቃቂር የሚያወጣብን፣ እንቅፋት የሚሆንብን ብዙ ነው።› ይላሉ። ‹በሴቶች ሥም መታገል ምን ያስፈልጋል!› የሚሉ ወንዶችም ጥቂት አይደሉም።

የሕግ ጉዳይን በሚመለከት እንድተነትን የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ባይኖረኝም፣ የሴቶች መብት ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አውቃለሁ ወይም የሴቶችን መብት እንደ ሰብአዊ መብት ነው የምረዳው። ሴቶች የመኖር መብታቸውን የተገፈፉበት፣ በባህልና በክብር ሥም መስዋዕት የሚሆኑበት ሳይቀር አካባቢና ባህል ጥቂት አይደለምና፣ የሴቶች መብት ሰብአዊ መብት ነው። አሁን ላይ በብዙ መልኩ ፖለቲከኞች፣ የብሔር አቀንቃኞች እንዲሁም ‹አክቲቪስቶች› የሚጮኹለት ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ኹነት ሴቶችን በሚመለከት ይከሰታል። ግን እንዲያም ሆኖ ገና ‹ሴቶች…› ብለን መናገር ስንጀምር ‹ደግሞ ጀመሩ!› ባዩ ብዙ ነው።

ለምን? ለምን የሴቶች መብትን ከሰብአዊ መብት ጋር እኩል እንደሆነ አስቦና አምኖ ቢያንስ ትግሉን ባይቀላቀል እንኳ በዝምታ የሚመለከትና የማይነቅፍ ሰው ጠፋ? ሴቶች በባህል ሥም ሲገደሉ፣ በለጋ እድሜያቸው የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ዙሪያቸውን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ ሲሆኑ እናያለን፤ እንሰማለን። ከዚህ የበለጠ የሰው ልጅ ላይ የሚደርስ ጉዳት የት አለና ነው ‹የሴቶች መብት› ሲባል ሰዉ ሰልችቶ መስማትን የሚጠላው?

በአንጻሩ ፖለቲካ ሲነካካው ግን ጉዳዩ አጀንዳ ሲሆን እንመለከታለን። ሴቶች ይጠለፋሉ፣ ከብሔር ጋር በተገናኘ ሲሆን ግን ጩኸቱ ይበረክታል። ሴቶች ይደገፈራሉ፣ ፖለቲካ ቀመስ ጉዳይ ከነካካው ግን የሁሉንም ትኩረት ይስባሉ። በአዘቦቱ የሚሆኑው የየእለት የሴቶች ጥቃት፣ በየፍርድ ቤቱ በገንዘብ የተዘጋው፣ በር ተዘግቶበት አደባባይ ያልወጣው በደል ግን ሰሚ የለውም። ሰሚ ስላጣው የሴቶች መብት ሲነገርም፤ ‹ደግሞ ጀመራችሁ!› ነው መልሱ። ለምን?

በአገራችን ፖለቲካ እንመልከት። የአንድ ብሔር ጩኸትና መብት እየተሰማና እየተከበረ አይደለም ከተባለ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? በእኛ አገር ሁኔታ ምክንያቱ ትግሉ ከስርዓት ጋር ሳይሆን ከሌላ ብሔር ጋር ስለሆነ ነው ብንል ያስሄዳል። ‹ሀ› የተባለ ብሔር መብቱ የሚከበረው ‹ለ› የተባለ ብሔርን በመጫን ይመስለዋል፤ ወይም ጥቅሙን የሚያስከብረው ‹ሐ› የሚባለውን ብሔር በማሳነስ አድርጎ ይቆጥረዋል። ሁሉም አህያውን ትቶ ዳውላውን የሚመታ፣ የተሸከመውን ስርኣት ረስቶ በላዩ ላይ በተዘረጋለት መስመር የሚሄደውን አካል እንደመደብደብ ነው።

የሴቶች ትግልም ከዛ የሚርቅ ነው ብሎ ማመን ይከብዳል። ‹ወንዶች እንዲህ አሉ! ወንዶቹኮ እንዲህ ያስባሉ! ወንዶች እንዲህ ለምን አይሆኑም!› የሚለውን አነጋገር ብዙ ጊዜ እንጠቀማለን። የሚገርመው ግን ችግር ያለው ወንዶቹ ጋር ብቻ አይደለም። የባሰው ችግር ሴቶች ጋርም አለ። ለምሳሌ ብዙ ጊዜ የሚነሳውን ተጠቂን መልሶ መኮነን/መውቀስ (Victim Blaming) የሚለውን ጉዳይ ብናነሳ፣ ይህን ሲያደርጉ የሚታዩት ሴቶች ናቸው።

በእርግጥ ይህ ጥናት የሚፈልግና እንደው በግምትና ስለመሰለን የምንለው ሊሆን አይገባም፤ ግን በማኅበራዊ ሚድያ ጨምሮ በአካባቢያችን የምናየው እውነት ይህ ነው። ስለዚህ ችግሩ ወንዶችም ሴቶችም አይደሉም ማለት ነው። አንድ ስርዓት አለ። ሴት ልጅን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አሳንሰን እንድናይ የሚያደርግ፤ ሴት ከፍ ስትል ብርቅ እንዲሆን እንዲሰማን ያደረገ።

ሃይማኖትን እንመልከት። የእምነት ተቋማት አስተምህሮን በተለያየ ትንተና ልንቃወም ወይም ላንስማማበት እንችላለን። ግን አንድም ቦታ ላይ ሴት ከወንድ ታንሳለች የሚል ከቅዱስ መጽሐፍም ሆነ ከቁርዓን ላይ የጠቀሰ የሃይማኖት ሰው አናውቅም። ኹለቱም ጾታዎች የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ግን ያስቀምጣሉ።

ዋናው ነጥብ እዚህ ጋር ነው። ሰዉ በተሰጠው ድርሻ ከፍና ዝቅ ሊደረግ አይገባም! ቢጎድል ያጎድላል። ሁሉም እያንዳንዱ በየድርሻው የሚገባው ከፍታ አለው።
በአንጻሩ ግን የምናውቀው ስርዓት ድርሻን ከፍና ዝቅ ያደርጋል። ስለዚህ ትግላችን ‹ሚስቴ የቤት እመቤት ናት! ሥራ የላትም› የሚል ባል ወይም ‹አንቺ ምን አለብሽ ቤትሽ እየዋልሽ› የምትል ጓደኛን ሳይሆን መቃወም ያለብን፣ አስቀድሞ ድርሻ ከፍና ዝቅ አያደርግምና፣ ይህን ስርዓት መለወጥ ያስፈልጋል።

ስርዓትን ሰው ይሠራል፣ ከዛ ሰው በስርዓት መሠረት ይመራል። እርግጥ ነው ስርዓቱን ከማሻሻል ጎን ለጎን የሰዎች አስተሳሰብ ላይ መሥራት ያሻል። ምክንያቱም የምንኖርበት ስርዓት የተጻፈ ሕግ አይደለም፤ በልምድ የመጣ ነው። ልምድ ደግሞ እንኳን እንደ ማኅበረሰብ እንደ ግለሰብም ለመተው ከባድ ነው። ይህን የኖረና የተጣባንን የልምድ ስርዓት መቀየር የምንችለው ከታች ጀምሮ በመሥራት ነው።

አንድም ሴቶችን በሚመለከት የሚሠሩ ማኅበራትና ድርጅቶች የሚታሙበት አንድ ጉዳይ ይህ ይመስለኛል። በአገራችን ሴቶች የሚገጥማቸውን ፈተናና ችግር እየታወቀና ምን ዓይነት አኗኗር እንዳለ እየታወቀ፣ አህያውንም ዳውላውንም ትተው ዱላቸውን የሚያሳርፉት መሬቱ ላይ ነው። እንደውም አሁን አሁን በሴቶች ሥም መደራጀት በራሱ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ፣ የውጪ ድጋፍ ሰጪዎችን የሚስብ ዘርፍ ሆኗል።

በእርግጥ ጽንፍ የረገጠ የሴቶች መብት ተሟጋችነትም ይታያል። በዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም አንዳንዶች ‹ፌሚኒዝም› ሲባል በጥላቻና በቁጣ ምላሽ የሚሰጡት። ይህም ጽንፍ የያዘ ሙግት ወንዶች ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻ ሲገለጽ ሊታይ ይችላል። ይህም ቀስ እያለ ወዴት እንደሚያመራ ግልጽ ነው።

በጊዜ ተገቢው መልስ ካልተሰጠ እርግጥም አፈንጋጭና ጽንፍ የያዘ ጾተኝነት በብዛት የማይታይበት ምክንያት አይታየኝም። አሁን ላይ ያለውን የኢትጵያን አገራዊ መልክ ተመልክተው ‹ላለፉት 30 ዓመታት የተተከለው ነው የበቀለው፣ የተዘራው ነው የታጨደው፣ የተቀበረው ነው የፈነዳው› እንደሚሉት፣ የሴቶች የእኩልነትና የመብት ጥያቄም ከወዲሁ ምላሽና ተገቢ ውጤት ማምጣት ካልቻለ የማንፈልገውን ማሳጨዱ፣ የማንሻውን ማብቀሉና ማፈንዳቱ አይቀርም።

አሁንም ላይ ሙግቶች በዳውላው ይልቅ ዳውላውን የያዘው አህያ ያልነው ስርዓት ላይ አተኩረው ያንን መቀየር ስለሚቻልበት ማኅበራዊና ሳይንሳዊ መንገድ ላይ ቢሆኑ እላለሁ። ምክክርና ንግግር ለውጥ ለማምጣት ትልቁ መግቢያ ነው።
ስለዚህም በዚህ ላይ ከተማ ላይ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭና ጆሮ ገብ ምክክሮችን በኢትዮጵያ ሴቶች በብዛት በሚገኙባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ማድረግ ያሻል። የሴቶች እኩልነትና መብት ትግል ገጠር ላለችው ሴት እንዲሰማት ከሆነ፣ እንደ ውርድወቷ ቃቄ ያሉ ሴቶች እንደውም መነሻው ከገጠራማዋ የኢትዮጵያ ክፍል ነው። ለዚህ ሁሉ ግን እርስ በእርስ ዱላ በማንሳትና በመነቃቀፍ ሳይሆን፣ ሁላችን የተሳፈርንበትን ስርዓት በመተቸትና በማሻሻል ለሴቶች የተሻለች አገርን እናቆይ። ሰላም!


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here