‹‹ምርጫ ከአፈሙዝ ይበልጣል›› አብርሃም ሊንከን

የኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ ምርጫ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ዓመት ተገፍቶ 2013 ግንቦት ላይ ሊውል ቀን ተቆርጦለታል። ከወዲሁ ተስፋና ስጋቶችን የያዘው ይህ ምርጫ፣ አሁን በሚገኝበት በቅድመ ምርጫ ሂደት ወቅት ውስጥ ለመራጩ ሕዝብ እንዲሁም ለተራጮች ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ የተለያዩ ማንቂያዎች ሲሰጡ ይስተዋላል። ጁሃር ሳዲቅም መራጮች የምርጫን አስፈላጊነት በመረዳት፣ የድምጻቸውን ዋጋም በማወቅ የሚመርጡትን ፓርቲ በጎሳና ብሔር ወይም በመሳሰለው ጠባብ መነጽር ሳይሆን ለአገር ሊያበረክት ከሚችለው አነጻር እንዲመዝኑ አደራ ብለዋል።

አገራችን ጓዟን ጠቅልላ ወደ ምርጫ ሜዳ ለመግባት ተሰናድታለች፤ ፊሽካው የተነፋ ይመስላል፤ ፓርቲዎችም በውቧ አዱ ገነት እንዲሁም በተለያዩ ክልል ከተሞች ቅስቀሳቸውን ሲያደርጉ ተስተውሏል። እንደኔ ከዘንድሮ ምርጫ ብዙ ነገር ይጠበቃል። አንደኛው አገር የምታሸንፍበት ሲሆን ሌላኛው ዴሞክራሲ የሚያሸንፍበት እንዲሆን ነው። እኔም የስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለማድረግ ወራት የቀሩት በመሆኑ፣ ወቅታዊና አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት፣ መነጋገር ያስፈልጋል ብዬ በማመን የዛሬው ርዕሴ ምርጫና ከምርጫ ጋር ተያይዞ ባሉ ጉዳዮች ላይ ላደርግ ወደድኩ።

ምርጫው የምርጫ መስፈርቶችን ያሟላል አያሟላም የሚለውን ክርክር ለጊዜው እንተወው። ምርጫ መደረጉ አይቀሬ መሆኑ የተወሰነ ከመሆኑ በተጨማሪ የምርጫ ጊዜው ስለደረሰ አሁን ጠቃሚ አጀንዳ እሱ አይደለምና፣ ሕዝቡ በሚጠቅመው ላይ መነጋገር ያሻል።
በመጀመሪያ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በስፋት እንመለከተው ዘንድ ዴሞክራሲና ምርጫ ምን አገናኛቸው? ለምን እንመርጣለን? ሕዝብ መሪውን እንዴት ነው የሚመርጠው? መስፈርት ሊኖረው ይገባል ወይስ አይገባም? በዘንድሮ ምርጫ መስፈርት መሆን ያለበትስ ቀዳሚው ጉዳይ ምንድነው? የሚሉት ጥያቄዎችን አንስቼ በኔ በኩል ያለውን ‹የምርጫ ቅስቀሳ› በይፋ እጀምራለሁ።

ዴሞክራሲና ምርጫ ሰፊ ተያያዥነትና የማይነጣጠል ቁርኝት ያላቸው ናቸው። ሐሳቡ ሰፊ ቢሆንም አሳጥረን እንይ፤ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን ፅንሰ ሐሳቡም ለዜጎች፣ ለአገር ምቹ የሆነውን መንግሥታዊ ስርአት መገንባት በሚቻልባቸው መርሆዎች ዙሪያ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ተንትኖ የሚያስቀምጥ የፖለቲካ ፍልስፍና ነው ማለት ይቻላል።

የዴሞክራሲን ፅንሰ ሐሳብ ብዙ የዓለም መሪዎች ይቀበሉታል። ሆኖም በተለይ የአፍሪካ መሪዎች ተግባሩ ላይ አንቀላፍተው፤ መርሁ ጋር ሲመጣ ግን ነፍስያቸው ታሸንፋቸዋለች። ስተው አምባገነን፤ መጨረሻቸውም በሕዝብ ማእበል ተንጠው መውደቅ ይሆናል።
ሌላው ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሲባል የእያንዳንዱ ዜጋ ይሁንታ የሚገለፅበት እና ዜጎች በጋራ የሚወስኑበት ስርአት ነው። በዚህ መልኩ ዜጎች በጋራም ይሁን በግል ይሁንታ ዴሞክራሲን ለማንበር አንዱ ትልቁ መሣሪያ ምርጫ የተባለው የዴሞክራሲ መርህን መጠቀም ነው።
ለዚህም ነው ዴሞክራሲያዊ ስርአት (ተቋም) ግንባታ/ምሥረታ የዜጎች ድምፅ (ምርጫ) ትልቅ ሚና አለው የሚባለው። በዚህ መልኩ ስናየውም ዴሞክራሲ እና ምርጫ የማይነጣጠሉ ሆነው ይገኛሉ።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት አብረሃም ሊንከን ስለ ዴሞክራሲ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፤ ‹‹ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በሕዝብ የሚመጣ ለሕዝቡ የሚሠራ›› (‹‹Democracy is government by the people for the people››) ማለት ነው። አያይዞም ዴሞክራሲ በብዙኀኑ ድምፅ የተመረጠ ሆኖ የትንሾቹን መብት የሚያከብር መንግሥት የሚመሠረትበት ስርአት ነው ይላል።

እንደዚህ አይነት መንግሥት የሚመረጠው ሕዝብ በሚያካሂደው ምርጫ ነው። ታዲያ በምርጫ ያልተመረጠ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተብሎ አይወሰድም። ምክንያቱም ከሕዝብ ሕጋዊ እውቅና አላገኘምና የሕዝብ መንግሥት ለመባል በሕዝብ መመረጥ አስፈላጊ ይሆናል ።

ላለፉት ሦስት ዓመታት አሁን ያለው ገዥው ብልፅግና ትክክለኛ የሆነ መንግሥት አይደለም የሚሉ ስሞታዎች ሲቀርቡ የነበረውም ከዚህ አኳያ ነው። ስለዚህ ብልግፅናው ገና ለገና ምርጫ በማድረግ ሕጋዊ እውቅና እና ትክክለኛነትን ለማግኘት ሲል ከሆነ ምርጫውን የሚያደርገው ውድቀቱም የከፋ፤ ለአገሪቱም የባሰ ቀውስ ይዞባት የሚመጣ ይሆናልና ጥንቃቄ ያሻል።

ያንንም ለማረጋገጥ ሲል ብቻ እንደ ሕውሃት ተመረጥኩ ቢል/ለማስባል ብቻ ከሆነ ምርጫ የሚያደርገው፣ ምክሬ ይቅርባችሁ ነው። ሕዝብ ባልመረጠው መንግሥት መተዳደር ደስ አይለውም። የሕውሃትን ቀድሞ የነበረውን በዴሞክራሲ መርሆዎች የተጫወተባቸውን ዓመታት ማስታወስ እንዲሁም ሲወገድ ደግሞ የሕዝቡን የዴሞክራሲ ፍላጎት መመለከትና ስርአቱን ሲረግምበት የነበረው ሁኔታ ማስታወስ በቂ ነው።

ስለዚህ በዚህ ምርጫ ብልፅግና ከሕውሃት ውድቀት በርካታ ነገሮች መማር አለበት ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ቀጥሎ ታዲያ ለምን ምርጫ እንመርጣለን የሚለውም እናስከትል።
ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለማንበር በሚደረገው ሂደት ትልቁ ወሳኝ መራጩ ነው። መራጩ የሚመርጠው የሚፈልገውና የሚያምንበት ስርአት እንዲመጣ እኩልነቱና ነፃነቱ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ፣ የአገርና የሕዝብን ደኅንነት ወዘተ ያረጋግጥልኛል የሚለውን ስርአት እንዲመጣ ለመወሰን ነው።

ከምርጫ ጋር ተያይዞ አገራችን ያላት ተሞክሮ ሙሉ ለሙሉ የከሸፈ ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ጎሰኝነት የበላይነትን ይዞ ዴሞክራሲ የተደፈጠጠበት ስለነበር፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቆም አልተቻለም። ለምን ቢባል፣ የሕዝቡ ድምፅ ብዙ ቦታ የተከፋፈለ ስለሆነ። ስለዚህ ዴሞክራሲ የሚመጣው እያንዳንዱ ዜጋ ለራሱ የሚፈልገው ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለሌላውም እንደሚያስፈልገው ሲያምን ነው።
በአሜሪካ ጥቁሮች ለእነርሱና ለሁሉም አሜሪካዊ የሚሆን መንግሥት ለመመሥረት ከታገሉበት ትልቁ ጉዳይ ውስጥ አንዱ የዜጎች የመምረጥ ነፃነት ጉዳይ ነበር ።

ጥቁሮች እያንዳንዱ ጥቁር የመምረጥ መብቱ እስኪከበር ትግል ጀመሩ። ታግለው የመምረጥ ነፃነታቸው ሲታወጅ መንግሥት ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ የጥቁሮች ነፃነት እኩልነት፤ የሥራ እድል፤ ፍትሃዊ የቤት እድል ተጠቃሚነት ወዘተ ፖሊሲዎች ይዘው መጡ። ጥቁሮችም ዴሞክራሲ ሊቸራቸው የሚችለውን አካል ካርዳቸውን በመስጠት ወደ ሥልጣን አምጥተዋል፤ በዚህ ሂደት ነው በአሜሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ፈር እየያዘ የመጣው።

ስለዚህ ዜጎች በመምረጣቸው እንደዚህ አይነት ቀድሞ ተበላሽተው የነበሩ ፖሊሲዎች በዴሞክራሲያዊ ፖሊሲዎች እንዲቀየሩ የራሳቸው አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት ነው፤ የምርጫ ሂደት። ምርጫ መምረጥ በሠለጠኑት አገሮች ትልቅ ተፅእኖ አለው ተብሎ በብዙኀኑ ይታመናል። ለዚህም ነው አብረሃም ሊንከን ‹‹ምርጫ ከአፈሙዝ ይበልጣል›› በማለት የተናገረው። ሌሎች ደግሞ ለአምባገነኖች ‹‹አድብቶ መግደያ›› ነው ይሉታል።
ምርጫ በባህሪው ምስጢራዊ ስለሆነ ሳይናገር አድብቶ አምባገነኖችን በማጥቃት ከሥልጣን ለማውረድ ሁነኛ መሣሪያ መሆኑም ይገለፃል።

ታዲያ ሕዝብ መሪውን እንዴት ባለ ሁኔታ ነው የሚመርጠው ወይም ሊመርጥ የሚችለው? መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው። ምክንያቱም በአብዛኛው የተመረጠው ስለሆነ መንግሥት የሚሆነው። ስለዚህ በመጀመሪያ የትኛውም ግለሰብ ወይም በአገሪቱ የሚገኙ ሕዝቦች፣ ለመምረጥ በተዘጋጀው የምርጫ መርሃግብር ለመሳተፍ ብሎም ይሁንታ የሰጠው ፓርቲ መንግሥት ሆኖ እንዲመጣ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ባወጣው የመራጮች መስፈርት መሠረት መመዝገብ እና የመምረጫ ካርድ መውሰድ ይጠበቅበታል።
ከዛ የተሰጠው ካርድ በአግባቡ ድምፁ እንዳይባክን ከቻለ በመጠየቅ ግንዛቤ መውሰድ ነው። ለአንድ ዜጋ መምረጥ ከፈለገ የምርጫ ካርድ መውሰድ ግዴታው ነው፤ ያለዚያ መምረጥ ስለማይችል።

የምርጫ ካርድ ማነው የሚወስደው ከተባለ ደግሞ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት ከ18 ዓመት በላይ የሆነው የትኛውም ዜጋ የመምረጥ መብቱ የተረጋገጠ ስለሆነ፣ በዛ መሰረት ይሆናል። በዚህ ሂደት ሁሉንም አሟልቶ የተገኘ መራጭ ቀጣይ ሥራው ምንድነው? መሪውን የሚመርጥበት መስፈርት ሊኖረው አይገባም ወይ የሚለው እናነሳለን?

የምናወራው ስለ እውነተኛ ዴሞክራሲና ስለእውነተኛ መራጭ ከሆነ፣ መራጩ ካርዱ ወደ ምርጫ ሳጥኑ ሳያስገባ በፊት ስለሚመርጠው ፓርቲ/ግለሰብ ቆም ብሎ ማየት አለበት። እንደሚታወቀው በእኛ አገር ዴሞክራሲ በሕወሃት የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ምክንያት የሚተረጎመው/የሚታሰበው በዘር፤ በወዳጅነት፤ በግል ጥቅም፤ በቤተሰብ ነበር። እነዚህ አስተሳሰቦች ፀረ ዴሞክራሲ ስለሆኑ የዜጎች እኩልነት ነፃነት ሊያመጡ አይችሉም።
ስለዚህ አሁን ከዛ ወጥቶ ለብዙኀኑ የሚሆን ዴሞክራሲ የሚመጣበት /ሊያመጣ የሚችለውን ለመለየት መራጩ ፓርቲዎችን መገምገም አለበት። ግን ምን ያህሉ ይህንን ይከተላል?
በተለይ አሁን ያለው ወጣት መሸወድ የለበትም ባይ ነኝ። ዝም ብሎ በብሔር አጥርና ሳጥን ታጥሮ እንዲሁም በይሉኝታ ግለሰቦችን ከሚከተል ይልቅ ግለሰቦቹ የተደራጁበት ፓርቲ፣ የፓርቲ ፕሮግራሞች እና ፖሊሲዎች፣ ማኒፌስቶአቸው ምን ይመስላል፣ ምንስ አማራጮች ይዘዋል ወዘተ የሚለውን መገምገም አስፈላጊ ነው።

የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማራጮችን ማየትና መገምገም፣ የመሬት ፖሊሲ ማየት መገምገም፣ የጤና ፖሊሲያቸውን ማየት መገምገም/ማነፃፀር፣ የትምህርት ፖሊሲያቸው ማየት መገምገም፣ የሃይማኖት ፖሊሲያቸው መገምገም ማየት ወዘተ። ሌላው ፓርቲዎች የሚከተሉትን ርዕዮተ ዓለም ማጤንና ከሚሉት ነገር ጋር በማስተያየት ሊበራል ዴሞክራሲ ነው፤ ሶሻሊስት ነው፤ ሶሻል ዴሞክራት ነው፤ ኢምፔሪያሊስት ነው ወዘተ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

እነዚህ ነገሮች የሚያስፈልጉበት ምክንያት ፓርቲዎች ዝም ብሎ ተጨብጭቦላቸው ነገ ሌላ አምባገነን እንዳይሆኑና ሆነው እንዳይመጡ ማስጨነቁ ጥሩ ስለሆነ ነው። የሚከተሉት የመንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ ነው፤ አሃዳዊ ወይስ ኮንፌደሬላዊ ነው? እንዲሁም ስርዓታቸውስ ፓርላሜንታዊ ነው ፕሬዝደንታዊ በሚሉትና በመሳሰሉት ዙሪያ መጠየቅ ያስፈልጋል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ቅስቀሳው በሐሳብ ስለማስጨነቅ እና ይህ ትውልድ ዴሞክራሲ እንጂ ‹እኔ ብቻ!› ስለሚለው የዘር ፖለቲካ ጉዳዩ ሊሆን እንደማይገባ ለማስረገጥ ነው።

መራጩ ማኅበረሰብ የፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ክርክሮችን በደንብ መፈተሸ ይኖርበታል። ለዚህ ነው በአሜሪካ የምርጫ ክርክሮች ሰፊ ቦታ የሚሰጣቸው። ምክንያቱም ከላይ ያልናቸው ሐሳበቦቻቸውን ለመራጩ የሚገልፁበትና የሚሸጡበት አጋጣሚ ነው። እነዚህ የምርጫ ክርክሮች በብዙኀኑ ዘንድም ይጠበቃሉ።

እነዚህን ክርክሮች በአንክሮ መመልከትና ማሰላሰል ከመራጩ የሚጠበቁ መሪውን መምረጫ መስፈርቶች ናቸው። ይህን ካደረገ በኋላ አንድ መራጭ በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ፅንሰ ሐሳብ የሚያምን ከሆነ፣ ለወደፊቷ የጋራ አገር በጋራ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን አረጋግጦ፤ በዴሞክራሲ፣ በእኩልነት፣ በነፃነት ሊያኖረኝ ይችላል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ይወስናል። ከዚያም መስፈርቱን ለሚያሟላው ፓርቲ ድምፁን ይሰጣል።

ከመራጮች ድምፅ ከሰጡ በኋላ ምን ይጠበቃል? ውጤቱ የጠበቁት ባይሆንስ? ከፓርቲዎችስ ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ለቀጣይ አቆይተን፣ በእኛ አገር ዘንድሮ ፓርቲዎች የምንመርጥበት መስፈርት ምን ይሁን? የሚለውን አንስቼ ላሳርግ።
አገራችን ላለፉት 27 ዓመታት ከዛ ቀድሞም የነበሩ ውዝፍ የተጠላለፉ ችግሮች ያሉባት አገር ነች። በተለይ የዘር/የጎሳ ፖለቲካ አስቸጋሪው ነው። ከነዚህ ዝብርቅርቅ ካለ ቀውስ ሊያተርፈን/ሊያስወጣን የሚችል ቃል የሚገባልን፣ ቃሉንም የሚፈፅም ወደፊት የምንጠይቀው ፓርቲ ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ።

በዚህ መሠረት አንድ ፓርቲ የኔን ካርድ ለመውሰድና ለመመረጥ በአጭሩ ሊያሟላቸው የሚገባው ዋና መስፈርቶች ብዬ የማስቀምጠው፣ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ላይ፣ በሕገ መንግሥቱ መቀየር ዙሪያ፣ ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮችን በተለይም ግብርናው እና የኑሮ ውድነቱ ማሻሻልን በተመለከተ፣ በቋንቋና በጎሳ ፌዴራሊዝሙ፤ የመሬት ስሪት እና አከላለል መቀየር ላይ፣ በሀብት እንዲሁም በፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍል፣ የአገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ፣ የውጭ ዲፕሎማሲና ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት፣ ጤናና ትምህርት፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዘመን ጋር በተያያዘ፣ የዜጎች የሃይማኖት፣ የቋንቋ እኩልነት ነፃነት፤ ዜጎች በግልም በቡድንም ስለ ሚኖራቸው ዴሞክረሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች ማሻሻል ላይ እዲሁም ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ዙሪያ የያዛቸው አቋሞች ወዘተ፣ የመሳሰሉትን ነው። በአንጻሩ በእኔ ዕይታ በጎሳ የተደራጀ የትኛውም ፓርቲ ከመስፈርቱ ውጪ ነውና ይታወቅ! ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here