ምርጫ 2013-የመረጃ ምንጫችሁ የትኛው ነው?

0
1151

ምርጫ 2013 ቅድመ ዝግጅቱ በደንብ ገፍቷል። ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ እረፍት አጥተዋል። ከእነዚህ መካከል መገናኛ ብዙኀን ተጠቃሽ ናቸው። ጋዜጦች፣ ራድዮንና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዲሁም ማኀበራዊ ሚድያዎች ምርጫን ከዘገባቸው መካከል ያካትታሉ። ሕዝቡም መረጃዎችን ጆሮ ሰጥቶ፣ ዐይኑን ከፍቶ
በጉጉት ይጠብቃል። ታድያ ምን አዲስ ነገር አለ ሲባል፣ ቀድሞ ራድዮን ይከፍታል? ቴሌቭዥን ጣቢያ ይቀያይራል? ጋዜጣና መጽሔቶች ያገላብጣል? ወይስ ማኅበራዊ ሚድያ ይገባል? ምርጫው ምንም ሆነ ምን መገናኛ ብዙኀን ከወዲሁ ሊሠሩ የሚገባቸው የቤት ሥራ መኖሩ ግን ግልጽ ነው።
የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት ድምጽ በመሰብሰብ፣ ባለሞያዎችን በማናገርና ጥናቶችን በማገላበጥ ተከታዩን የአዲስ ማለዳ ሐተታ አዘጋጅታለች።

500ው ሰዎች?
አዲስ ማለዳ ልክ ከኹለት ሳምንት በፊት (የካቲት 19/2013) በተለያዩ የማኅበራዊ ሚድያ ገጾቿ ላይ ‹የ2013 ምርጫን በሚመለከት የዜና እና የመረጃ ምንጭ ተመራጭ አማራጭዎ የትኛው ነው?› የሚል ጥያቄ በማስቀደም አማራጮችን አስቀመጠች። እነዘህም ማኅበራዊ ሚድያ፣ የመንግሥት ወይም የግል ሚድያ የሚሉ ሲሆኑ በአራተኛነት የቀረበው አማራጭ መረጃዎችን ከሰዎች እሰማለሁ የሚል ነው።

በትዊተር፣ ፌስቡክ እንዲሁም ቴሌግራም የአዲስ ማለዳ ገጾች ላይ ለሰፈረው ለዚህ መጠይቅ 500 ሰዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ 464 በቀጥታ ከተቀመጡት አማራጮች መካከል መርጠዋል። በዚህ መሠረት ምርጫቸውን ካስቀመጡ 464 ሰዎች መካከል 197 ሰዎች (42.46%) ማኅበራዊ ሚድያን፣ 146 ሰዎች (31.46%) የግል ሚድያዎችን፣ 76 ሰዎች (16.38%) የመንግሥት እንዲሁም 45 ሰዎች (9.7%) ከሌሎች ሰዎች እሰማለሁ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 30 ለሚጠጉ ሰዎች መደበኛ እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የትኛውን ሚድያ ይመርጡ እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ 13 ሰዎች ማኅበራዊ ሚድያን እንደሚመርጡ ሲገልጹ፣ 8 ሰዎች የመንግሥት፣ ኹለት ደግሞ የግል ሚድያ ምርጫን በሚመለከት የሚወጡ ዘገባዎችን የሚከታተሉባቸው አውዶች እንደሆኑ ተናግረዋል።

የተቀሩት 10 ሰዎች በጥያቄው ከተጠቀሱት ምርጫዎች በተለየ ‹‹ሚድያ አንከታተልም››፣ ‹‹ማንንም አናምንም›› (የምርጫውን ውጤት ብቻ ሲደርስ ማየት ነው በሚል) እንዲሁም ‹‹ሁሉንም ሚድያዎች በወፍ በረር እንቃኛለን›› ያሉ ናቸው።
በተመሳሳይ በአዲስ ማለዳ ማኅበራዊ ገጾች ላይም በቀረበው ጥያቄ ስር በአስተያየት ማስቀመጫ ሳጥን ላይ ዕይታቸውን ያሰፈሩ አሉ። አስተያየቶቹም ‹‹ሁሉም [ሚድያዎች] አይመጥኑም››፣ ‹‹ምርጫ ቦርድን አምናለሁና ማኅበራዊ ሚድያ ሲባል የምርጫ ቦርድ የሚያወጣውን ብቻ እከታተላለሁ››፣ ‹‹መልስ የለም የሚል ይጨመር››፣ ‹‹ውስጥ አዋቂ ምንጭ›› እንዲሁም ‹‹የምርጫ ቦርድን ብቻ›› የሚሉ ተገኝተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አዲስ ማለዳ ይህንን ጥያቄ ለተለያዩ ጋዜጠኞችም አቅርባለች። በመንግሥት እንዲሁም በግል ሚድያ ከእያንዳንዳቸው ኹለት መገናኛ ብዙኀን የሚሠሩ ጥያቄው የቀረበላቸው ባለሞያዎችም፣ ሕዝብ ተመራጭ የሚያደገውና ጫና ሊፈጥር የሚችለው ማኅበራዊ ሚድያው ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ከዛም በተጨማሪ በማኅበራዊ መገናኛዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ የግል መገናኛ ብዙኀንም ተዓማኒነትን ጨምረው ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ ብለዋል።
በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን የሚሠሩ አስተያየት የሰጡ ጋዜጠኞችም ከሚሠሩበት ተቋም ይልቅ ማኅበራዊ ሚድያው እንዲሁም የግል መገናኛ ብዙኀን በሕዝብ ተመራጭ እንደሚሆኑ ጥርጥር ያላቸው አይመስልም። ‹‹ሰዎች የመንግሥት መገናኛ ብዙኀንን የሚከታተሉት ከግልና ማኅበራዊ ሚድያዎች የሰሙትንና ያመኑትን ለማረጋገጥ ብቻ ይመስለኛል።›› የሚል አስተያየት የሰጡ አሉ።

በጥቅሉ ጥያቄው ገና ሲቀርብ ጀምሮ ‹ምን ጥርጥር አለው!?› በሚያሰኝ ሁኔታ ብዙዎች የማኅበራዊ ሚድያን ተጽእኖ የመፍጠር አቅም አምነዋል። ይህ ታድያ ለምርጫ 2013 እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ነው? ማኅበራዊ ሚድያዎች ለሐሰተኛ ዜና ተጋላጭ እንደመሆናቸው መጠን፣ ከወዲሁ ምን ማድረግ ይገባል? የግልም ሆነ የመንግሥት መደበኛ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ዘገባውን የሚያዘጋጁ ጋዜጠኞችስ ምን ይጠበቅባቸዋል? አዲስ ማለዳ እነዚህን ጥያቄዎች አቅርባለች።

ምርጫና መገናኛ ብዙኀን – ምልሰትና እውነት
ምርጫ በቂ የፖለቲካ እውቀትና መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔን የሚፈልግ ሂደት እንደሆነ እሙን ነው። ይህን መረጃ በማቀበልና በቂ እውቀትና መረጃ ያለውን ዜጋ በመፍጠር በኩል ደግሞ የመገናኛ ብዙኀን ሚና እጅግ ወሳኝ መሆኑ አያጠራጥርም። በተለይም ሙያዊ ሥነምግባርን ጠብቆ የፖለቲካ ፉክክርን ሙሉ ምስል የማሳየትን ድርሻ ይወስዳሉ። የክርክርና የውይይት መድረኮችን መፍጠር፣ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ ማስቻል ዘገባዎችን ከማቅረብ ጎን ለጎን ሊወጧቸው የሚገቡ ተግባራት ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው ካደረጋቸው ቅድመ ዝግጅቶች መካከል አንደኛው የመገናኛ ብዙኀን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባርና አሠራር መመሪያን ማውጣት ነው። በመመሪው መግቢያ ላይም ቦርዱ መገናኛ ብዙኀን ወይም ጋዜጠኞች በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው በሚዘግቡበት ወቅት የሚኖራቸው መብት፣ የሥነምግባር ኃላፊነት እና ግዴታዎችን መደንገግ ለምርጫ ሂደት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ያወጣው መመሪያ መሆኑን አስፍሯል።
ይህ ወሳኝ የመገናኛ ብዙኀን የምርጫ ሂደት ላይ የሚኖራቸው ሚና ታድያ በቀደሙ ጊዜያት ውስን መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ላይ ብቻ የተጣለ ነበር። አሁን ላይ ግን መደበኛ መገናኛ ብዙኀን እጅግ በርካታ ከመሆናቸው ባለፈ የማኅበራዊ ሚድያው ተገዳዳሪና የላቀ አቅም ያለው መሆኑ ፈታኝ እንደሚሆን ይታመናል።

በምልሰት ወደኋላ ዓመታትን ተሻግረን የ1997 ምርጫ ኹነቶችን ማስታወሳችን ግድ ነው። በወቅቱ ከምልዐት የቀረበ የቅድመ ምርጫ ሂደትና ንቁ የመደበኛ መገናኛ ብዙኀን (በተለይም ሕትመት) እንቅስቃሴ ይታይ የነበረበት ወቅት ነው።
‹‹በ1997 ምርጫ አንድ ብሎገር ብቻ ነበር።›› በማለት የነበረው ሁኔታ በማስታወስ የሚጀምሩት የመብቶችና ዴሞክራሲ እድገት ማእከል (ካርድ) የጋራ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ ናቸው። በጊዜው የኢንተርኔት ተደራሽነት ምንም የለም የሚባል ደረጃን የተጠጋና ለኮምፕዩተር ቴክኖሎጂ ያለው ግንዛቤ እንኳ ገና በሚገባ ማኅበረሰቡን ዘልቆ የገባ እንዳልነበር ያወሳሉ።

በጊዜው ይልቁንም የግል ጋዜጦች እንደ አሸን ፈልተው ነበር። ፖለቲካውን የመሩት፣ አጀንዳ ሲሰጡና ሲነሱ የነበሩትም እነዚሁ ጋዜጦች እንደነበሩ በፍቃዱ አንስተዋል። በጊዜው ጋዜጦች የነበራቸው አቅምና ጉልበት ከዛሬው የማኅበራዊ ሚድያ አቅም ጋር በየራሱ አውድ ተስተካክሎ ሊታይ የሚችል እንደሆነም ነው የጠቀሱት።

ማኅበራዊ ሚድያና የሚፈጥረው ስጋት?
ብዙዎች የማኅበራዊ ሚድያን ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ አድርገው መውሰዳቸው ለምን አጀንዳ ሊሆን እንደቻለ መገመት ቀላል ነው። እውነቱ በኢትዮጵያ ከኹለት ዓመታት ወዲህ ብንመለከት እንኳ፣ የተከሰቱና ተዘርዝረው የማያልቁ ግጭቶች የተፋፋሙትና የተቀጣጠሉት በማኅበራዊ ሚድያዎች መሆኑ ግልጽ ነው።

ባለፈው ዓመት የመብቶችና የዴሞክራሲ እድገት ማእከል (ካርድ) ባወጣው ዘገባ፣ ከመቶ በላይ የሐሰት ዘገባና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ አካላትና ቡድኖች መኖራቸውን በጥናት አረጋግጫለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው። ማኅበራዊ ሚድያ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ መሆኑን የምንቀበለው እውነት እየሆነ ቢመጣም፣ ከሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት አንጻር ስጋት መደቀኑ አይቀርም።

በፍቃዱ ይህን በሚመለከት ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ማኅበራዊ ሚድያው በኹለት ዓይነት መንገድ ስጋት እንደሚፈጥር ተናግረዋል። አንደኛ ግጭት የማስከሰት አደጋ ማምጣት ሲሆን በሌላ በኩል ውሳኔ ሰጪነት ላይ ተጽእኖ ማድረግ ነው።
በማኅበራዊ ሚድያዎች የሚቀርቡ የተዛቡና ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች፣ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚመለከት በቂ መረጃ እንዳያገኙ ወይም የተሳሳተ መረጃ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ይህም በምርጫ ካርዳቸው የሚሰጡት ድምጽ ላይ ተጽእኖ ያደርጋል። በትክክል መረጃ ቢኖራቸው ኖሮ የማይመርጡትን፣ በተዛባ መረጃ ምክንያት ይመርጣሉ። ይህም ትልቅ ኪሳራ መሆኑ አያጠራጥርም።

በተመሳሳይ ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣ የምርጫ ሂደትም ይሁን ውጤትን በተመለከተ የሚሰራጩ የተሳሳቱና የተዛቡ መረጃዎች ሊሰራጩ መቻላቸው ነው። እነዚህም ቁጣና ግጭት ይፈጥራሉ። በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሚድያዎች፣ በፖለቲከኞች፣ በተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ሥም የተከፈቱ ‹ሐሰተኛ› ወይም ‹አስመሳይ ገጾች› እነዚህን ሐሰተኛ ዜናዎች የሚያሰራጩ ናቸው፤ እንደ በፍቃዱ ገለጻ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት መምህርት ሰብለ በቀለ ስጋታቸውን በመግለጽ ጀመሩ። ስጋታቸው ሁሉም ሰው በየሐሳቡ፣ በየአመለካከቱና በየብሔሩ ጥግና ጽንፍ ይዞ ባለበትና ከዛ ወጥቶ እየተመለከተ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ፣ እንኳንና ማኅበራዊ ሚድያ መደበኛውም ቢሆን በትክክለኛው መንገድ ዘገባዎችን ላያደርስ ይችላል የሚል ነው።

እርሳቸው ትኩረታቸውን ያደረጉት ማኅበራዊ ሚድያውን የሚፈጥረውን ችግር ከማንሳት ይልቅ ተዓማኒና ለሕዝብ ጥቅም የሚሠሩ መደበኛ መገናኛ ብዙኀንን እና ጋዜጠኞች አስፈላጊነት ላይ ነው። በበኩላቸው የምርጫ ዘገባን ከማንሳት በፊት ጋዜጠኞች መጀመሪያ ራሳቸውን እንዲሁም የሚሠሩበትን ተቋም መፈተሽና መመልከት አለባቸው ብለዋል።

የማኅበራዊ ሚድያውን ተጽእኖ ጥልቀት ሲያስረዱ፣ መደበኛዎቹ መገናኛ ብዙኀን ማኅበራዊ ሚድያዎችን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም ላይ መድረሳቸውን ይጠቁማሉ። ለአጠቃቀም ምቹነት፣ በሚያቀርበው የሐሳብ ብዝኀነትና የዕይታ ስፋት፣ ፍጥነትና መረጃዎችን ለማሰራጨት ካለው ቅለት አንጻር ማኅበራዊ ሚድያ ተመራጭ መሆኑ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከዛ መተካከል ባይችሉ እንኳ መደበኛዎቹ ሊሠሯቸው የሚችሉና ስጋቱን መቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደነበሩ አስረድተዋል። ምንም እንኳ አስቀድሞ መጀመር የነበረባቸው ሥራዎች ቢሆኑም።

መደበኛዎቹ ለምን ቀዳሚ ተመራጭ አልሆኑም?
የአዲስ ማለዳ ጥያቄ ምርጫችሁ የትኛው ነው የሚል እንጂ የትኛውን ታምናላችሁ የሚል አይደለም። ምንአልባት ጥያቄው የተዓማኒነት ጉዳይ ቢሆን ምላሹ ይቀየር ይሆናል ወይም ላይቀየር ይችላል፤ መገመት አይቻልም። እንዲያም ሆኖ ግን ከተመራጭነት አንጻር እንኳ ቢሆን መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ተመራጭነትን ያገኙ አይመስልም።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ማኅበር ምሥረታውን ካጸና አንድ ዓመትን ተሻግሮ በዛም ላይ ወራት ጨምሯል። የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል ደመቀ ከበደ በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ፣ ማኅበራዊ/ዲጂታል ሚድያዎች በፍጥነታቸው እንዲሁም በምስል፣ በጽሑፍና በቪድዩ፤ በሦስቱም መንገዶች መረጃዎችን ለማቅረብ ምቹ መሆናቸውና መሰል ምክንያቶች የተነሳ ተመራጭ ሆነዋል።

‹‹መጀመሪያ ተግባቦት በአንድ ወገን ብቻ ነበር። አድማጭ፣ ተመልካች ወይም አንባቢ ዘገባዎችና መረጃዎች ላይ አስተያየት ለመስጠት የሚጠቀመው መንገድ ጽሑፍ [ደብዳቤ] ነበር። ቀጥሎ ስልክ ሲመጣ በፍጥነት ደውሎ አስተያየት ለመስጠት ተቻለ። በማኅበራዊ ሚድያ ደግሞ ይህ በፍጥነት ተቀየር። የመረጃ ተጠቃሚና የሚድያዎች ግንኙነት ቀጥታና ፈጣን ሆነ።›› ሲሉ ሂደቱን ያስረዳሉ። ማኅበራዊ ሚድያው እንዲህ ያሉ ብዙ ጥቅሞች ያሉት መሆኑ መደበኛዎቹን ፈተና ውስጥ አስገብቷቸዋል።
ያም ብቻ አይደለም። መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚኖርባቸው ጫና እንዳለ ሆኖ፣ ጋዜጠኝነት ቅቡልነቱና ማኅበራዊ መሠረቱ እየተናጋ መሆኑን እናምናለን፤ ደመቀ ያሉት ነው። ጋዜጠኝነት ብቻ ሳይሆን የመገናኛ ብዙኀን ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ወቅትንና ሁኔታን ባገናዘበና በሚመጥን መልኩ እየቀረቡ አይደለም ብለዋል።

የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህርት ሰብለ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ጋዜጠኞች ያለወገንተኝነትና በተዓማኒነት ሲዘግቡ አይስተዋልም። ይህ የምርጫና የፖለቲካ ዘገባ ሆነ እንጂ በአዘቦቱም የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ዘገባዎች ማዘጋጀት ላይ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰዋል።

‹‹በዜና ውስጥ እውነቶችና የግል ዕይታዎች አንድ ላይ እየቀረቡ ሳለ፣ እንዴት ወደፊት እንጓዛለን!?›› ሲሉ ይጠይቃሉ። ከሙያተኝነት አቅም በመነሳት ያለውን ክፍተት ያነሱት ሰብለ፣ በአንድ በኩል በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶና እንደ ዘርፍ በጉዳዩ ሙያተኛ ሆኖ የመዘገብ አሠራር አለመኖር የፈጠረው ክፍተት ነውም ብለዋል።

የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ደግሞ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በየራሳቸው ወገንተኛነት ይታይባቸዋል ባይ ናቸው። ‹‹ሐሰተኛ መረጃ ከማሰራጨት ነጻ አይደሉም [መደበኛ መገናኛ ብዙኀን]። ብቃት ወይም ቁርጠኝት፤ ከኹለቱ አንዱ ይጎድላቸዋል።››
በፍቃዱ አክለው ከሰጡት ሐሳብ ይህን ቃል በቃል እንጥቀስ፤ ‹‹በአገራችን አሁን ያለው የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዛባት ገጥሞታል። የመረጃ ልውውጥ ምህዳሩ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነው ያለው። ይህ ቀውስ እያንዳንዱን ሰው ውዥንብር ውስጥ ይከታል። እየተከናወኑ ስላሉ ነገሮች ብዙዎቻችን ትክክለኛ መረጃና ግንዛቤ ያለን ይመስለናል፣ ግን አብዛኞቻችን በብዙ የተሳሳቱ መረጃዎች የተነዳ ግንዛቤ ነው ያለን።››

በቅርቡ በትግራይ ክልል እየሆኑ ያሉ ክስተቶችና ያለውን የመረጃ ክፍተት ያወሱት በፍቃዱ፣ አያይዘው በምርጫ 2013 ከዚህ የተለየ የመረጃ ተደራሽነት ይኖራል ብለው አያስቡም። ‹‹በምርጫውም ጊዜ የተለየ ነገር አይኖርም። የተለያዩ ኃላፊነት የማይሰማቸው የፍላጎት ቡድኖች አሉ። እነዚህ ቡድኖች የራሳቸውን የፖለቲካ ትርክት ይቀልቡናል።››

80 በመቶው ሕዝብስ?
እነዚህን እውነታዎች ለአፍታ እንመልከት። የኢትዮጵያ ሕዝብ 114 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ከሥነ ሕዝብ ጋር በተገናኘ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቅሳሉ። ከዚህ ውስጥ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 23.5 ሚሊዮን እንደሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ከኹለት ወራት በፊት ባወጣው የግማሽ ዓመት ዘገባ አስታውቋል።

ይህ ማለት ከተጠቀሰው የሕዝብ ብዛት አንጻር ሲሰላ ኢንተርኔት ተጠቃሚው 20.61 በመቶ ብቻ ነው። ከዚህ ሁሉ የቀረው 80 በመቶ ሕዝብስ?
‹ስታትካውንተር› የተሰኘ የአገራትን የማኅበራዊ ሚድያ አጠቃቀም አሃዝ የሚያስቀምጥ ድረገጽ፣ የካቲት ወር መጀመሪያ ባወጣው የአሃዝ መረጃ፣ ከኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መካከል 39.94% የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ናቸው። 36.71% ትዊተር፣ 10.9% ዩትዩብ እና 1.31 ደግሞ ኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ናቸው ይላል።

ኢትዮ ቴሌኮም በተለያየ ጊዜ የዋጋ ማስካከያዎችና ቅናሾ በማድረግ፣ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን መጠን ለመጨመርም ስልኮችን በዱቤ ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ሥልቶችን እየተጠቀመ ይገኛል። ያም ሆኖ ዘመናዊውን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ሕዝብ የጠቅላላውን ግማሽ እንኳ አልሆነም።

ዴሞክራሲ፣ የፖለቲካ ነጻነት እና ሰብአዊ መብትን በተመለከተ በየጊዜው ዘገባዎችን የሚያወጣ ‹ፍሪደም ሃውስ› የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፤ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አጠቃቀም ዙሪያ ባስነበበው መረጃ፣ በገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍል የቴሌኮም መሠረተ ልማት የለም ማለት ይቻላል ይላል።

ትንንሽ በሚባሉ ከተሞችም ኢንተርኔት ለማግኘት መንቀሳቀስ ወይም ከፍ ወዳለ ተራራማ ቦታ መውጣትን የሚጠይቅ እንደሆነ ያክላል። ያውም የፖለቲካ አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ በተፈጠረ ቁጥር ኢንተርኔት ይዘጋል፤ ይቋረጣል።
ገጠራማ አካባቢዎች ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሌለ ያለው የመረጃ ምንጭ አማራጭ ራድዩን አልያም ቴሌቭዥን እንደሚሆን ግልጽ ነው። ይህም ማኅበራዊ ሚድያው ኖረም አልኖረ፣ መደበኛው መገናኛ ብዙኀን በተገቢው የሙያ ሥነምግባር መሠረት የምርጫ ዘገባዎችን ለሕዝብ የማድረስ ኃላፊነትን በሚገባ ይወስዳል።

መደበኛው ሚድያ ምን ያሰጋዋል?
‹‹መደበኛው ሚድያ ብዙ ርቀት መጓዝ፤ ሐሳብና አመለካከትም መቀበል አለበት። ይህም ቀድሞ ነበር መታሰብ የነበረበት። ብዝኀነትን የሚያስተናግድ ሚድያ ያስፈልጋል። ያ ስላልነበረ ነው እዚህ ወቅት ላይ ደርሰን የተጨነቅነው።›› ያሉት የጋዜጠኝነት መምህርት ሰብለ ናቸው።

ማኅበራዊ ሚድያው ምንም እንኳ ተመራጭ ይሁን እንጂ ሰዎች የመረጃዎችን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ከመደበኛ መገናኛ ብዙኀን ቃል መጠበቃቸው የማይቀር እውነት ነው። ሆኖም ከፍጥነትና ሐሰተኛ ዜናንም ከማክሸፍ አንጻር፣ ለሕዝቡም ትክክለኛውን መረጃ ለማድረስ ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ነው ሰብለ ያሳሰቡት።

ከዚህ በተጓዳኝ ታድያ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ከምርጫ 2013 ጋር በተገናኘ ኃላፊነታቸውን በአግባብ እንዳይወጡ ሊፈትናቸው የሚችልና የሚያሰጋቸው ነገር ይኖር ከሆነ አዲስ ማለዳ ጠይቃለች።
የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል ደመቀ እንዳሉት፣ ከምርጫ ዘገባ ጋር በተገናኘ እንደ ማኅበር ከስጋት የተያዘው አንዱ የመረጃ እጥረት ይኖራል የሚል ነው። መረጃዎች በተፈለገው ፍጥነትና ለሁሉም አካላት በፍጥትና በትክክል የማድረስ ችግር ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አለን ብለዋል።

ሌላው ደግሞ ጋዜጠኞች በነጻነት እንዳይዘግቡ የሚያደርጉ ቢሮክራሲያዊ ማሸማቀቆች ሊኖሩ የሚል ነው። ይህ በሚፈጥረው የመረጃ ክፍተት የተነሳ፣ እንዲሁም ከጋዜጠኞች የሙያተኝነት አቅም ማነስ፣ አንድን አካል መወገን፣ ትክክለኛ የሆነ መረጃን አለማግኘት ምክንያት በራሳቸው ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት በማኅበሩ በኩል እንዳለም ጨምረው ጠቅሰዋል።

ማኅበሩ ‹የካቲት ወር እንዴት አለፈ?› በሚል ባወጣውና የ2013 ምርጫን በሚመለከት ባስነበበው መግለጫ፣ በተጀመረው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ የነበሩ የዘገባ ሽፋኖችን እንደ ማሳያ አንስቷል። መግለጫው እንዲህ ይላል፤
‹‹የዘገባ ሽፋናቸው ምጣኔ በግርድፉ ሲታይ ውግንና የሚስተዋልበት ነበር ማለት ይቻላል። በተለምዶ የ‹መንግሥት› የሚባሉትና ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያላቨው ለገዢው ፓርቲ ሰፋ ያለ ሽፋን ሲሰጡ፣ በተመሳሳይ የግል የሚባሉት ደግሞ ለተፎካካሪዎች ሰፋ ያለ ሽፋን ሰጥተዋል። ይህ በብዙኀን መገናኛዎቹ የተስተዋለው የ‹ፓርቲ ውግንና ዝንባሌ› በሚቀጥሉት ጊዜያት በሚኖረው ነጻና ፍትሃዊ የምርጫ አዘጋገብና የመረጃ ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይኖረው ስጋት አለን።›› ብሏል፤ ማኅበሩ።

ምክረ ሐሳብ
‹‹ሁሉም ከራሱ መጀመር አለበት፣ ጋዜጠኛውም ጭምር።›› ያሉት ሰብለ ናቸው። በተለይም ለሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት ቅድሚያ መስጠትን ሁሉም ባለሞያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለው በአጽንዖት ተናግረዋል። ባለሞያዎች ራሳቸውን ከአድልዎ ነጻ ማድረግ ከቻሉ፣ ቀጥሎ ተቋማቸውን መመልከትና ኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን መከለስ ይገባቸዋልም ብለዋል።

እንዲሁም የመረጃ ምንጭ ብዝኀነት ወሳኝ መሆኑንና በቀላል ሊገኙ ከሚችሉ ምንጮች ባለፈ ድምጻቸው መታከል ያለበትንም ሰዎችና ባለሞያዎች ድምጽ ለማካተት ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል። በስሜትና በሆሆታ ሳይሆን በመረዳትና በጥንቃቄ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የካርድ የጋራ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ በበኩላቸው፣ የጋዜጠኞችን አቅም በፋክት ቼኪንግ እና ግጭት አገናዛቢ የሆነ አዘጋገቦች በመገንባት በርካታ ርብርቦች እየተደረጉ መሆኑን አውስተዋል። ግን በቂ አይደለም አሉ። መገናኛ ብዙኀን ኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውም መከለስ አለባቸው ሲሉ አመላክተዋል።

የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል ደመቀ፤ ሐሰተኛ መረጃ ከምርጫ ጋር ሲገናኝ በአገር ላይ ሊያሳድር የሚችለውን መጥፎ ጠባሳ ለመከላከል ይረዳሉ ያሏቸውን መንገዶችን ጠቁመዋል። መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ያለአድልዎ በሚዛናዊነት መዘገብ አንዱ ነው። የጋዜጠኞችን አቅም በቶሎ መገንባት ያስፈልጋልም ብለዋል።

አገር ዐቀፍ የሆነ ሁሉን ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የሚድያ ክትትልና ማማከር ላይ የሚሠራ፣ ሚድያ የተመለከቱ ማኅበራት በጋራ የሚሳተፉበት ጊዜያዊ ኮሚቴ ማቋቋም እንደሚጠቅም ጠቁመዋል። እንዲያ ሲሆን ሐሰተኛ መረጃን በፍጥነት ማረምና እርስ በእርስ መተራረም ይቻላል ባይ ናቸው።

ከዛም በተጓዳኝ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በማኅበራዊ ገጾች ተሳትፎአቸውን በማጠናከር መረጃዎችን በጥራትና በፍጥነት ማድረስ ላይ እንዲተጉ መክረዋል። የጋዜጠኝነት ሙያ ሥነምግባና ምርጫ ቦርድ ያወጣው መመሪያ ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here