ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእነ እስክንድር እጩ ሆኖ መቅረብ ላይ የወሰነው ክልከላ ከሕግ ውጭ ነው ሲል ከሰሰ።
ባልደራስ እስክንድር ነጋን በፓርቲው ስም እጩ አድርጎ በየካ ምርጫ ወረዳ አቅርቧቸው የነበረ ቢሆንም በእጩነት መቅረብ እንደማይችሉ ምርጫ ቦርድ አሳውቆኛል፣በዚህም ቅረወ ተሰኝቻለሁ ብሏል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር” አ/ቁ. 1162/11 አንቀጽ 31(1)(ሠ) “ማንኛውም ሰው በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ” እንደሆነ በእጩነት መቅረብ እንደሚችል በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ መኖሩን ይህም ሕግ መጣሱን ባልደራስ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነ አቶ እስክንድር ነጋ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ በባልደራስ ፓርቲ ስም እጩ ሆነው እንዳይቀርቡ የሰጠው ውሳኔ አመራሮቻችንን ከገዢዎች ጋር ተደርቦ እንደማጥቃት አድርገን ቆጥረነዋል ብሏል።በተጨማሪ የቦርዱ ውሳኔ፣ የ6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ገለልተኛነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዳስቀምጠው አድርጎኛል ብሏል።
በሕግ ጥላ ያሉ ዜጎችን የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ያለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ መግፈፍ፣ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ ያጨነግፈዋል ያለው ባዳልደራስ፣ለእስክንድር ነጋ የተመዘዘ የክልከላ ካርድ ነገ በማናቸውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ጥርጣሬ የለኝም ሲል ገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲያችን እየተፈጸመ ያለውን በደል ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ባሻገር፣ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ለተቋቋሙት ልዩ የምርጫ ችሎቶች በገለልተኛነት ፍርድ እንደሚሰጡ ወይም በገዢው ፓርቲ ረጅም እጅ የተጠለፉ መሆናቸውን እፈትሻሁ ብሏል።
በምርጫ ቦርድ ያለውን ሂደት በሙሉ ጠብቄ ጨርሻለሁ ያለው ባልደራስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው እና የፍትህ ተቋሙን ገለልተኝነት ከወዲሁ ለመፈተሽ መወሰኑን አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013



