የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኹለት ቀናት ማለትም የካቲት 26/2013 እና የካቲት 29/2013 ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ማመልከቻ ላስገቡ እና በመጀመሪያ ዙር ላለፉ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥልጠና ሰጠ።
በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ የተከፈተው መድረክ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ በቦርዱ የፕሮግራም ባለሙያ-የውጭ ግንኙነት ክፍል፣ በቦርዱ የሥርዓተ -ፆታ እና አካታችነት ክፍል እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሙያ ቀርቧል። ሥልጠናውን ለምን መስጠት እንዳስፈለገ የተናገሩት የቦርድ አመራሯ ብዙወርቅ ከተተ፤ የተወሠኑት ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ያስገቡት ሠነድ ላይ የዕቅድ አወጣጥና ዘዴ ክፍተት በመታየቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለምን ምርጫ መታዘብ ያስፈልጋል፣ የምርጫ መታዘብ ዕሴቶችና ጥቅሞች፣ በምርጫ መታዘብ ወቅት የሚጠበቁ የሥነ-ምግባር ደንቦችና ኃላፊነቶች፣ አካታችነትን ያማከለ የምርጫ መታዘብ ሂደት፣ የምርጫ መታዘብ አቀራረብ ዘዴ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎች፤ ማለትም የምርጫ መታዘብ ስልት፣ ሪፖርቶችን ማደራጀት፣ የአካታችነት መርሆችን ተግባራዊ ማድረግ ከሥልጠናው ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ ሲሆኑ፤ የቀረበውን ሥልጠና የተመለከተ ውይይት ከተሣታፊዎች ጋር ተደርጎ የፕሮግራሙ ማብቂያ ሆኗል ተብሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013


