ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ የወራት እድሜ ብቻ በሚቀራት በዚህ ወቅት የምርጫ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲ በቅድመ መርጫ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በማንሳት ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።
ስድስተኛው የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ መደረግ የነበረበት በ2012 ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሐየራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ አልችልም የሚል ሐሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረቡ፣ ምክር ቤቱ ምርጫውን በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ወደ 2013 እንዲሸጋገር ወሰነ። ያንን ተከትሎ ምርጫው የፊታችን ግንቦት 28/2013 እንዲካሄድ የመጨረሻ ቀነ ቀጠሮ ተቆርጦለታል።
ምርጫ በኢትዮጵያ የሚሰጠው ዋጋ ከዚህ ቀደም የነበሩትን እንደማሳያነት ብናነሳ በርካታ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ፍትሐዊና እውነተኛ ምርጫ ተካሂዷል ለማለት የሚያስችል አንዳልሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ አገራዊ ምርጫዎች ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ‹ምርጫ ተካሂዷል› የሚለውን መስፈርት ለማሟላት እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ የሚኖርበት የምርጫ ሜዳ እንዳልነበረው በማንሳት ይወቀሳል። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት ከሚነሱት ነገር መካከል የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነት አንዱ ነው።
የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ በብዙዎች ዘንድ ጥሩ የሚባል ተስፋ የተጣለበትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጻነት ይወክለኛል ያለውን ፓርቲ እንደሚመርጥ ይጠበቃል። ይሁን እንጅ በምርጫ ሂደቱ ላይ ገና ከወዲሁ ቅሬታ የሚነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልጠፉም።
በመርጫ ሂደቱ ላይ ቅሬታ ከሚነሱት አንዳንድ ፓርቲዎች መካከል እንደ ኦሮሚያ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ይገኙበታል። ፓርቲዎቹ የሚነሱት ቅሬታ በአመዛኙ በምርጫ አስፈጻሚው አካል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት የሦስቱንም ፓርቲ አመራሮች አነጋግራ በምርጫ ቦርድ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳላቸው ሰምታለች።
ፓርቲዎቹ ለቦርዱ የሚቀርቧቸው በርካታ ቅሬታዎች ናቸው። ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እራሱ ከፓርቲዎች የሚመጡ ቅሬታዎች አጅግ በዝተውብኛል ማለቱ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጅ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የሚተነተኑት ፓርቲዎች እያቀረቡ ያሉት የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነትና ብቃት፣ እንዲሁም ፓርቲዎች በእንዚህ ጉዳዩች ዙሪያ በቅድመ ምርጫ ሁደቱ ላይ ያላቸውን ስጋት ነው።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነት ላይ ቅሬታ ካቀረቡት ፓርቲዎች መካከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አንዱ ነው። ፓርቲው የሚቀርባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እያገኙ አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ባልደራስ በምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነት ላይ ያለውን ቀሬታ ለምርጫ ቦርድ በጽሑፍ ማሳወቁን ገልጿል። ይሁን እንጅ ባልደራስ አንደሚለው በተለይ በአዲስ አበባ ምርጫ አሰፈጻሚዎች ገለልተኛነት እና ምርጫ የማስፈጸም ብቃት ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች ቢቀርቡም ምላሽ እንዳልተሰጠው አስታውቋል።
ፓርቲው ባሳለፍነው መጋቢት 2/2013 “የመንግሠት ሽፋን የተሰጠው የዘር ማጥፋት ወንጀል እና የምርጫ ቦርድ አሻጥር” በሚል ለጋዜጠኞች በሰጠው መገለጫ ላይ እንዳለው ምርጫ ቦርድ በራሱ ገለልተኛ ነው ብሎ እንደማያምን ጠቁሟል። ባልደራስ ይህን ያለበት ምክንያት ቦርዱ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በገለልተኛነት አለማቅረቡ፣ ለሚቀርቡለት ቅሬታዎች ተገቢ ምላሽ አለመስጠትና የመወሰን ስልጣን በሌለው ጉዳዮች ላይ መወሰኑን መነሻ በማድረግ ነው ብሏል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ(ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች አስተማማኝና አስማሚ መሆን ካልቻሉ በምርጫው ላይ ቅሬታ መፍጠራቸው አይቀርም ባይ ናቸው።
በቃሉ አክለውም የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሂደት በላይ በምርጫ ፍትሓዊነት ላይ የበለጠ እንድንጠራጠር አድርጎናል ይላሉ። የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነት አስተማማኝ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ምርጫው ዋጋ አለው ብለው የማያምኑት በቃሉ፣ እስካሁን በነበሩት የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ምርጫ ቦርድ በራሱ ገለልተኛ ነው ብለን እንዳናምን አድርጎናል ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጥርጣሬውን ያቀረበው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) ነው። ኦፌኮ በምርጫ ቦርድ ላይ ያለው ቅሬታ እንደ የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነትና የማስፈጸም ብቃት ብቻ አይደለም።
“በገለልተኝነት ምርጫውን ያስፈፅማሉ የተባሉት የምርጫ አስፈፃሚዎችም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የተሞሉና ቀሪዎች ደግሞ ሕግ የማውጣት ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቀውን የሕዝብ ተወካዮች ምርጫን የማስፈጸም ልምድና ቁመና ላይ እንዳልሆኑ እና በኹለቱም በኩል ፍትሓዊ ምርጫ ያስፈጽማሉ የሚል እምነት እንደሌለንም ለምርጫ ቦርድ ደጋግመን አሳውቀናል።”ሲሉ የኦፌኮ ሊቀመንበሩ መረራ ጉዲና(ፕ/ር) ገልጸዋል።
መራራ አክለውም የባልደተራስን አቋም በመጋራት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራዉን ምርጫ ቦርድላይ ጭምር ያላቸውን እምነት ገለልተኛ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
“እንደ ኦፌኮ፣የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ለመሾም ጠቅላይ ሚንስትሩ አስተያየት ሲጠይቁን ያለንን ሪዘርቬሽን ሁሉ ለጠቅላይ ሚንስትሩ በግልጽ ተናግረናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አክለውም ኦፌኮ በሰላምና በነጻነት ቅስቀሳዎችን ያደርግ ነበር፤ ሆኖም እንደ ጃዋር ያሉትን አመራሮች ወህኒ ቤት በማስገባት፤ የኦፌኮ ሕዝባዊ ስብሰባዎች የጥላቻ ንግግርቾ ሲነገሩት የነበረው። ዲቃላዎች፣ ነፍጠኞች እያሉ የተወሰኑ ማኅበረሰባት ላይ አፍራሽ ቅስቀሳዎች ሲያደርጉም ነበር ብለዋል።
ኦፌኮ በምርጫ ሂደቱ ላይ ገና ከጅመሩ ሲቃወም የቆየ ፓርቲ አንደሆነ የሚታወቅ ነው። ፓርቲው እስካሁን ድረስ በምርጫ ሂደቱ በርካታ ቅሬታዎች እንዳሉት እየገለጸ ነው። ቅሬታዎቹ ካልተፈቱለት በምርጫ ለመሳተፍ እንደማይፈልግም ገልጿል። እንደ መራራ ገለጻ ፓርቲው ቅሬታዎቹ ካልተመለሱለት በምርጫው የማይወዳደረው ከሂደቱ እስከ ፍጻሜው ምርጫው ፍትሓዊና ገለልተኛ ነው ብሎ ስለማያምን መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው ቅሬታውን በተደጋጋሚ ለምርጫ ቦርድ የሚስገባው ፓርቲ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ነው። ኦነግ ከዚሀ በፊት በተደጋጋሚ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ከሆነ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኝነት እንደሌለው ነው።
የኦነግ ቅሬታ በዋናነት የፓርቲው አመራሮች መከፋፈል ላይ ቁርጥ ውሳኔ አለማግኘቱ ቢሆንም፣ በምርጫ ቦርድ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ገለልተኛነት ላይ ቅሬታ እንዳለው ነው።
አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ያነጋገረቻቸው ኢነግ እና ኦፌኮ ገዥው ፓርቲ በምርጫ እንዳንሳተፍ የሚደርገው ተንኮል በምርጫው ገለልተኛነት ላይ እንድንጠራጠር አድርጎናል ባይ ናቸው። የእነ ዳውዲ ኢብሳው ኦነግ ቡድን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊበንቴ ኡርጌሳ እንደሚሉት ከሆነ ገዥው ፓርቲ በሸረበው ሴራ ኢነግ በምርጫው ተፈኳካሪ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖበታል ይላሉ።
በንቴ አክለውም ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ነው ሊስብሉትን ተግባራት እየከወነ አይደለም የሚል እምነት አላቸው። ለዚህም እንደ መሳያነት የሚነሱት ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው የሚቀርቡለተን ቅሬታዎች ተመልክቶ ምላሽ አለመስጠት እና ኦነግ ያቀረበለትን እንደ ቃለ ጉባኤ የመሰሉ ማስረጃዎችን አልደረሱኝም በሚል ለሚዲያዎች የሚሰጠው የውሰጥ መልስ መሳያ ናቸው ብለዋል።
የኢዮጵያ ብሐየራዊ ምርጫ ቦርድ በቅድመ ምርጫ ሂደቶች ከሚፈጽማቸው ተግባሮች አንዱ የምርጫ ተአማኒነት ያላቸው ምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመልና ማሰልጠን ነው። ቦርዱ እንደሚለው እስካሁን በከወናቸው ቅድመ ምርጫ ሥራዎች ገለልተኛ ተአማኒ እንደሆነ ነው።
ይሁን እንጅ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ የመለመላቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ፣ ተአማኒና ብቁ አይደሉም ሲሉ ይተቻሉ።
ፓርቲዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነትና ብቃት ከሚተቹበት ምክንያት ያስቀምጣሉ። ባልደራስ የምርጫ አስፈጻሚዎን ገለልተኛነትና ብቃትን የሚተቸው ገና ከምልመላ መስፈርቱ ነው። እንደ ባልደራስ አቋም ከሆነ በተለይም በአዲስ አበባ የተመለመሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ብቃትና ገለልተኛነታቸው ላይ ከማነጻጸር ይልቅ ሥራ የሌላቸው መሆናቸው ላይ ያተኮረ መሆኑን መታዘቡን አስታውቋል።
በሎሎች ፓርቲዎች በኩል ይህን መሰል ሀሳቦች ይነሳሉ። ምርጫ ቦርድ የሚመለምላቸው ምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነት ጥያቄ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩላ ካለ ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል። የተመለመሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ አለመሆናቸወን በውል የሚረጋግጥ ማስረጃ ከቀረበለት ቦርዱ ቅሬታውን እንደሚስተናግድ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 2/2013 የምርጫ ሂደት ላይ እየተሳተፋሁ ለሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች ባደረገው ጥሪ የመራጮች ምዝገባ ከሚጀመርበት ቀን አስቀድሞ፣ ማለትም እስከ መጋቢት 15/2013 ድረስ ፓርቲዎች አስተያየታቸውን ለቦርዱ እንድታቀርቡ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫን የተሻለ ግልጽነት እና ተአማኒነት አንዲኖረው ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን ቦርዱ አያይዞ ገልጿል። ከዚህም መካከል ለፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር በመስጠት የገለልተኝነት ማጣራት እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያሳወቁ ማድረጉን አንስቷል።
ቦርዱ ከዚህ በፊት በተለያዩ ዙሮች የመለመላቸውን የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳቀረበ ጠቁሟል። በዚሁ መሰረት በአሁኑ ወቅት ቦርዱ በተለያየ መልኩ የመለመላቸው እና ለመራጮች ምዝገባ ተግባር ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ አስፈጻሚዎች ዝርዝርን አዘጋጅቻለሁ ብሏል። በመሆኑም ፓርቲዎች ከቦርዱ የተሰጣቸውን ፍላሽ ይዘው በመቅረብ ከቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሥራ ክፍል መውሰድ የሚችሉ መሆኑን አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013


