መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛከ‹ቴዲ ቡናማው› ግድያ ጀርባ

ከ‹ቴዲ ቡናማው› ግድያ ጀርባ

በሳምንቱ የሥራ ቀን መጀመሪያ ሰኞ፣ መጋቢት 6 በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤተል አዲስ ተስፋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ወጣት ቴዎድሮስ አበባው (በሚታወቅበት ቅጽል ሥም ‹ቴዲ ቡናማው›) ባልታወቁ ሰዎች በተፈፀመበት ወንጀል በግል የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥባት መኪና ውስጥ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል። ድርጊቱ ብዙዎችን ያስቆጣ፣ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ያጨናነቀ ሰሞነኛ መነጋገሪያም ሆኗል።

ስለ ‹ቴዲ ቡናማው› ብዙዎች የሚያውቁት ምስክርነት ሲሰጡ፥ ደግ፣ መልካም፣ አቅመ ደካሞችን እና ድሆችን የሚረዳ ነበር ይሉታል። ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለሰባት ዓመታት ያክል የወደቁ ወገኖችን አንስቷል፤ የተቸገሩትን ረድቷል። የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎም አለርት አካባቢ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብስቦ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ መጠለያ አሰርቶ ገላቸውን እያጠበ ይመግብ እንደነበረ ጓደኞቹ እንባ እየተናነቃቸው ምስክርነታቸውን አሰምተዋል። አንዳንዶች የቴዲ በሰው እጅ መገደል፥ ‹‹ደግንት ምን ያደርጋል?›› ብለው እንዲጠይቁም ሰበብ ሆኗቸዋል።

‹ቴዲ ቡናማው› ሌላው የሚታወቅበት እንዲሁም ለሥሙ ቅጽል ያሰጠው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ቡድን ቀንደኛ ደጋፊ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሚታማባቸው ነገሮች አንዱ፥ የታዋቂዎቹን የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የሌሎች ቡድኖች ደጋፊዎች ከባድ የሥነ ምግባር ማፈንገጥ እና ጠብ አጫሪ መስተጋብር እንዲቀር ‹ቴዲ ቡናማው› ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በብረቱ ሰርቷል፤ ውጤትም አስመዝግቧል። በቀብር ሥነ ስርዓቱም ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሌሎች ክለብ ደጋፊዎች መታደማቸው ምስክር ሆኖ አልፏል።
ከታወቂ ሰዎች መካከል የ‹ቴዲ ቡናማው›ን ኅልፈት በተመለከተ ድምጻዊ ያሬድ ነጉ በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹‹ቴዲ ቡናማውን ሳውቀው ጀምሮ በቅንነቱ እና ትሁት በሆነው አንደበቱ ስለሌሎች መልካም ነገርን በማውራት እና ለተቸገሩ በመደርስ ነው። የኅልፈተ ሕይወቱን ዜና በመስማቴ የተሰማኝ ሐዘን እጅግ ጥልቅ ነው። . . . እኔን ጨምሮ ሌሎችንም ወጣቶች በማሰባሰብ እና በማነቃቃት ብዙ መልካም ነገሮችን የፈጸመ ለብዙዎች የቅንነት ጉዞ መሰረት የሆነ ሰው ነው።›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ሌላው ብዙዎች የሚያውቁት ቀደም ብሎ በጄቲቪ ‹‹ጨዋታ ከእንዳልክ ጋር›› አሁን ደግሞ በአፍሪሄልዝ ቲቪ ላይ ዝግጅቱን የሚያቀርበው እንዳልካቸው ዘነበ፥ ስለ‹ቴዲ ቡናማው› በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹‹የተዋወቅነው ብሩህ የምትባል ምስኪን ልጅ እናሳክማት ዘመድ ወገን የላትም ብሎ ደውሎልኝ ነው። ደሃ ሲታመም የቡና ደጋፊን አስተባቡሮ የሚያሳክም፤ . . . . ሙሽራ ነበር፤ ልደቱንም ትናንትና እያከበርንለት ነበር›› ሲል የተሰማውን ጥልቅ ሐዘኑን አሰፍሯል፤ ለጓደኞቹም ‹‹ሐዘናችንን ዋጥ አድርገን ቴዲ የጀመራቸውን በጎ ተግባራት በቡድንም በተናጥልም እናስቀጥል።›› ሲልም ጥሪ አስተላልፏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ማክሰኞ፣ መጋቢት 7 በይፋዊው ኮሚሽኑ የፌስቡክ ገጽ ባሰራጨው መረጃ፥ በተለያዩ ጊዜያት ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ወንጀሎች ተፈፅመው ፖሊስ ባደረገው ክትትል ፈጻሚዎቹን በአጭር ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን አስታውሷል፤ በተለይም የግል ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 8 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። የወጣት ቴዎድሮስ አበባውን ሕይወት ያጠፉ ተጠርጣሪዎችን ለማወቅና ለመያዝም ፖሊስ ኮሚሽ’ኑ ቀን ከሌሊት ክትትል እያደረገ ሲሆን በአጭር ቀናት ውስጥ የደረሰበትን ውጤት ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ ጨምሮ ገልጿል።

ይህንን አሳዛኝ ግድያ በተመለከተ ብዙ መላ ምቶች ተሰምተዋል፤ ከሃይመኖት፣ ከፖለቲካ፣ ከ125ኛው የአድዋ በዐል አከባበር ጋር በነበረው የጎላ ተሳትፎ እንዲሁም በውርስ ከቤተሰቡ ጋር የገባበት ግጭት ጋር በማያያዝ ብዙዎች፣ ብዙ ነገሮችን ብለዋል። የትኛው መላምት ለእውነት የቀረበ ነው የሚለውን ጊዜ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ለእጮኛው ከሣምንታት በፊት የ‹ታገቢኛለሽ ወይ› ቀለበት ያሠረው እና ልደቱን እሁድ ከጓደኞቹ ጋር ያከበረው ‹ቴዲ ቡናማው›፥ ኀሙስ፣ መጋቢት 8 በነቂስ በወጡ ወጣቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታዊ ስርዓት መሰረት ግብዐተ መሬቱ በቀራኒዩ ድብረ ቀራኒዮ ደብረ መድኀኒዓለም ሥር በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።


ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች