በጋምቤላ ክልል ባለፉት ኹለት ሳምንታት ከ450 ሺሕ ለሚበልጡ የዳልጋ ከብቶች የበሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መሰጠቱን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ጋልዋክ ዎል በክልሉ ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሀብት ጤና በማሻሻልና የአረባብ ዘይቤውን በማዘመን የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ለመለወጥ እየተሠራ ነው ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል። በተለይም ክልሉ ጠረፋማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታ ለመከላከል በሁሉም ወረዳዎች ለቀንድ ከብቶች ክትባቶች መሰጠታቸውን ተናግረዋል። አርብቶ አደሩን ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግም በየቀበሌው የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ተመድበው በቅርበት ሙያዊ ድጋፍ እንዲሰጡ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የቢሮው የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዳይሬክተር ዶክተር አካሉ ከበደ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የክልሉን የዳልጋ ከብቶች ጤና ለመጠበቅ በኹለት ዙር የጉርብርብ፣ ጉሮርሳ፣ አባጎርባና ሳባ ምች መከላከያ ክትባት መሰጠቱን አስረድተዋል። ክትባቱ የተሰጠው በሽታዎቹ የክረምቱን መውጫና መግቢያ ተከትሎ ሊከሰቱ ይችላሉ በሚል ስጋት እንደሆነና በክልሉ ከ450 ሺሕ የሚበልጡ የዳልጋ ከብቶች መከተባቸውን አስታውቀዋል።
በክልሉ ላሬ ወረዳ የንብንብ ቀበሌ ነዋሪ ኡቻን ኖድ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ በኹለት ዙር ክትባት በመሰጠቱ የቀንድ ከብቶቻቸው ጤንነት መጠበቁን ገልጸዋል። ባለፈው ክረምት ተከሰቶ ከነበረው ጎርፍ ጋር ተያይዞ ከብቶቻቸው በተለያዩ በሽታዎች እንዳይጠቁ በቂ ክትባት በመቅረቡ ከስጋት መላቀቃቸውን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ፖል ጆክ ናችው።
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



