የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም ዐቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ማዳም ጁታ ኡርፒላየን እና ከአውሮፓ ኅብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ጃነዝ ለናርሲስ ጋር ብራስልስ በኢትዮጵያና በኅብረቱ መካከል ባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ሚኒስትሩ መጪውን አገራዊ ምርጫን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦትንና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ እየተደረገ ስላለው ምርመራ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያም ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮ-አውሮፓ ኅብረት የልማት ትብብርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሐሳቦችን የተለዋወጡ ሲሆን፣ በውይይቱ የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ እየወሰደ ላለው እርምጃ እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የኅብረቱ ባለሥልጣናት አክለውም ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያላትን ቁልፍ ሚና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት መጠቆማቸውን በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ጠቁሟል። የአውሮፓ ኅብረት እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



