ከተሞችን አስቦ መወጠን

0
1007

የኢትዮጵያን የከተሞች ዕቅድ እና ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችን በማመሳከር፣ ከተሞችን ለነገ አቅዶ ስለመቀየስ አስፈላጊነት የጻፉት ሙሉጌታ ገዛኸኝ፥ ዕቅዶቹ ታሪክ፣ ባሕል፣ ነባር የኪነ ሕንጻ ትውፊቶችን እና ሌሎችንም ከግንዛቤ ያስገባ መሆን እንደሚኖርባቸው ያስታውሳሉ።

 

 

የከተማ ዕቅድ እና ቅየሳ አመጣጥና ዕድገት በአንድ ውስን የዓለማችን አካባቢ ብቻ ተጀመረ ለማለት የሚያስቸግር ቢሆንም ከሰው ልጅ ጥንታዊ ሥልጣኔ መፍለቂያዎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ባላቸው ልዩ ልዩ ሥፍራዎች መጠንሰሱን መዛግብት ያስረዳሉ።
የከተማ ፕላን ወይም ዕቅድ ዓለም ዐቀፍ ፅንሰ ሐሳብ ከጥንት እስከ አሁን ዘመን ያለፈባቸውን የታሪክ ቅደም ተከተል ለመቃኘት ስንሞክር በርካታ ጥናቶች ተካሒደዋል። በአህጉራችን አፍሪካ በአብዛኛው የምዕራባውያን ከተማ አቀያየስ ዘይቤ መከተልና ተግባራዊ ማድረግ የተለመደ ሲሆን፥ እንደአካባቢው የሕዝብ አኗኗር፣ ባሕል፣ የተፈጥሮና የባሕር ነፋስ ጠባይ ታሳቢ ያደረገ የከተማ ልማት አቀያየስ በራስ አቅምና ዕውቀት መሥራትን ማዳበር አስፈላጊነቱም ጉልህ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ጠቃሚ ቴክኖሎጂዎችንና ልምዶችን በጥንቃቄ ቀስሞ በአገራችን በሥራ ላይ ማዋልም ተገቢ ይሆናል።
የራስን ጥሎ፣ የሌላውን አንጠልጥሎ?
በአገራችን በከተማ ቅየሳ ረገድ በዋናነት የባሕል ብዝኀነት፣ ታሪካዊ የገበያ ሥፍራዎች፣ ቅርሶች፣ ነባር ሰፈሮች፣ ቀደምት የኅብረተሰብ መሰባሰቢያ ቦታዎች፣ አድባራትና መስጊዶች፣ የከተማው ልዩ መለያ ትውፊቶች ወዘተርፈ በጥናት ተለይተው በከተማው ዕቅድ ውስጥ እንዲካተቱና በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የታሪክ ጥናት የላቀ ድርሻ አለው። በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባቸውን ከተሞች በመቀየስ ረገድ ከፍተኛ ሙያዊ ትኩረት ካልተሰጠ አላስፈላጊ ውድመት ሊደርስባቸው ይችላልና ዕቅዳቸው በጥንቃቄ እንዲዘጋጅ ያስፈልጋል። የከተማውን የወደፊት ዕድገት ከቀደምቱ ጋር በማስተሳሰር ሕይወት እንዲኖረው በማድረግ ከታሪካዊ የስህተት ድግግሞሽ ይታደጋል።
ይህንን ሐሳብ ለማጠናከር ስኮትላንዳዊው የንድፈ ሕንጻ ታሪክ ጸሐፊ ሚልስ ግሌንዲንግ የጻፈውን መጥቀስ ቢያስፈልግ “ለውጥ በታሪክ ሒደት ቋሚና ራሱን በቻለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ገባ አተያይና አረዳድ ፋይዳው የላቀ ነው።” የአንድ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዕቅድ ላይ በሚሸነሸኑ የከተማው ቦታዎች አብዛኛውን ለኅብረተሰብ የጋራ መገልገያ አጠቃቀም ታሳቢ ያደርጋል። የታቀደው ቦታ በሚዘጋጅበት ወቅት በቅየሳው ሒደት የተጠኑ ታሪካዊ የከተማ ክፍሎች፣ ሰፈሮች እና የሚዳሰሱ ቅርሶቻቸው ጉዳት እንዳይደርስባቸውና በአግባቡ እንዲጠበቁ በሙያዊ ጥናትና በጣልቃ ገባዊ አሠራር ተመርኩዞ በየከተሞቹ ከንቲባዎች መደገፍ ይኖርባቸዋል።
በጥንታዊት ኢትዮጵያ የአገራችን ሥልጣኔ በአሻራነታቸው የሚጠቀሱ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሐረር፣ ጎንደር የመሳሰሉ ከተሞች ያለጥርጥር አስደናቂ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ማበቡን ማሳያ ምስክሮች ናቸው። እነዚህ ከተሞች ባሕላዊውን የአኗኗር ዘይቤ ሳያፋልስ አገርኛ የሣርና የጭቃ፣ የድንጋይ ጥርብ ቤቶች አቀያየስ ስልት ማስኬድ የተለመደ እንደነበርም ያሳያሉ። አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 1876 ጀምሮ ይህንኑ ገጽታ ተላብሳ ብትቀጥልም በተፈጠረው የውጭ ግንኙነት ሳቢያ የአውሮፓውያን የዘመናዊ ኪነ ሕንጻ ቅርፅ ተፅዕኖ ማሳረፉ አልቀረም። ሆኖም የከተማዋ ቅየሳ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች እንደተቀየሰች ከአሻራዎቿ ለመገንዘብ ይቻላል።
ከሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ እስከ ኢጣሊያ ወረራ ማግስት የነበሩ ልዩ ልዩ የከተማ ዕቅድ ጅማሮዎች ቢኖሩም፥ ከተሞቹ በተቆረቆሩበት አምባ እንዲሁም አባጣ ጎርባጣ መልክዓ ምድር ባሕርይ፣ በሕዝብ አሰባሰብና አሰፋፈር አሉታዊ ተፅዕኖዎች መኖሩ አይቀርም።
በፋሽስት ወረራ ወቅት በ1929 ዘመናዊ የቤቶች አሠራር ኪነ ሕንጻ በሰፊው መታየት የጀመረበት ነበር። ሆኖም ከነጻነት መመለስ በኋላ (1933) የመጀመሪውን ዘመናዊ ‘ማስተር ፕላን’ ለአዲስ አበባ ከተማ ለዐሥር ዓመት አገልግሎት እንዲሰጥ ተዘጋጀ። የከተማዋ ፕላን እንደገና እንዲከለስ በ1956 የተደረገ ሲሆን በሌሎችም የጠቅላይ ግዛቶች ዋና ዋና ከተሞች ማዘጋጃ ቤት እንዲቋቋምና ‘ማስተር ፕላን’ እንዲኖራቸው ታወጀ። የካርታና ቶፖግራፊ ክፍል ጉላቲ (ፕሮፌሰር) በሚባል ሕንዳዊ ይመራ ነበር። እንዲሁም የአዲስ አበባ ዕቅድ ክፍል በኢትዮጵያውያን የመልክዓ ምድር ባለሙያዎች ይካሔድ የነበረ ሲሆን፥ ‘የካዳስተር’ ክፍል የባለይዞታዎችን መሬት የቦታ ስፋትና በካሬ ሜትር ዋጋ ይመዘገብ ነበር። ከዘውዳዊው ሥርዓት ለውጥ (1966) በኋላ ራሱን የቻለ የብሔራዊ ከተሞች ዕቅድ ተቋም እንዲቋቋም በመደረጉ ከተሞች ዕቅድ እየተዘጋጀላቸው እንዲተገብሩት መደረጉ ጠቃሚ ልምድ አስገኝቷል። ከደርግ ‘የኮሚኒስት’ ሥርዓት ማክተም ወዲህ (1983) ‘የፌደራል ፕላን ኢንስቲትዩት’ በሚል ይታወቅ የነበረ ሲሆን፥ ከተሞች በፌደራል ደረጃ የክትትልና ድጋፍ አማካኝነት ክልሎች የዕቅድ ተቋማትን በማደራጀት በራሳቸው አቅም እንዲያዘጋጁ ጥረት መደረጉ ይገለጻል። በአሁኑ ወቅት የዘመናዊ ቅየሳ መሣሪዎች ‘ቲዎዶላይትስ’፣ ‘ቶታልስቴሽን’፣ ‘ዲፈረንሻል ጂፒኤስ’ የመሳሰሉት ለከተማ ቅየሳ በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ ቢሆንም በሠለጠነ ባለሙያ ባለመደገፉ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የተቻለ አይመስልም።
በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የከተማ ዕቅድ ቅየሳ ደግሞ በልዩ ሁናቴ እየዘመነ የመጣበት ዓይነተኛ ምክንያት የኢንዱስትሪ መስፋፋት በመሆኑ የሕንጻ ግንባታ ቁሳቁስ፣ ፍጥነት እና ዘዴ ከግል ባለሀብቶች ፍላጎት አኳያ ትኩረትን ለመሳብ ችሏል። ሆኖም የሥልጡን ከተሞች አስቀያሚ የድኽነት ሕይወት ከተሜነት ገጽታ በእጅጉ መንሰራፋት መንግሥታቱን ይከተሉት ከነበረው የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ለውጥ እንዲያመጡ አስገድዷል። በተለይም ‘ቪክቶሪያን’ እየተባለ በሚጠራው ዘመን የኒዮሊበራሊዝም (አዲሱ ሊበራሊዝም ማሰላሰያ) ጎልቶ መውጣቱና በድኽነት ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕይወት ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ መምጣቱ አልቀረም። እ.ኤ.አ ከ1900 ወዲህ ተንታኞች አዲስ የከተማ ልማት ዕቅድ ምስለ ማሳያዎችን ማስተዋወቅ የጀመሩበት አጋጣሚ በመሆኑ የኢንዱስትሪ ዘመን ተፅዕኖዎች በከተሞች ማለትም በፋብሪካ ላባደሮች ጤንነት እና አካባቢያዊ ጤንነት አጠቃላይ ኅልውና መንፀባረቅ ጀመረ። በቀድሞ ሰፊው የጀርመን ግዛት መጠሪያ ፕረሽያ በከተሞች ልዩ ልዩ ሠፈሮች ዘመነኛ የመሬት አጠቃቀም አገልግሎቶች በከተማ ዕቅድ ቀያሾች ሕጋዊ አሠራር መከተል እየተለመደ የመጣ ቢሆንም ቀስ በቀስ ወደ እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ስካንዲኒቪያ አገሮች ተስፋፍቷል። የዚህ የከተማ ዕቅድ ዋነኛ የአስተሳሰብ ትኩረት መነሻው በከተሞች የተደራጀ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‘ጋርደን ሲቲስ’ ወይም ‘የአረንጓዴ ልምላሜ ውብ ከተሞች’ ፅንሰ ሐሳብ ተቀባይነት እያገኘ መምጣት ጀምሯል።
የአረንጓዴ ውብ ከተሞች ዕሳቤ
የአረንጓዴ ከተሞች ዕሳቤ እየዳበረ ሊመጣ የቻለው እ.ኤ.አ ከ1898 ጀምሮ አቤኔዘር ሃዋርድ በተባለ የከተማ ዕቅድ ቀያሽ ነበር። የመጀመሪያው ንድፈ ሐሳብ ፈር ቀዳጅ ተብሎም ይጠራል። በልምላሜ የታጀበ ውብ ከተማን የመፍጠር አስተሳሰብ ብቅ ማለት የጀመረው ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ዘመን ምግባረ ሰናይ ግለሰቦች በገጠራማ አካባቢዎች በዕቅድ በተመሠረቱ የፋብሪካ መስፋፊያ መንደሮች የሚኖር ማኅበረሰብ መፍጠርን ዓላማው ባደረገበት ወቅት ነው።
የሥነ ምጣኔ ተንታኝ ባለሙያ የሆነው አልፍሬድ ማርሻል እ.ኤ.አ በ1889 ባሳተመው መጽሐፍ “ዘ ጋርደን ሲቲስ ኦፍ ቱሞሮ” ስለ ከተማ ቅየሳ ዕቅድ ጠቃሚ ማጣቀሻ ነው። አልፍሬድ እንደሚገልጸው የኢንዱስትሪ መስፋፋት በታላላቅ ከተሞች ርካሽ የሰው ጉልበት ፍለጋ የተነሳ ጤናማ ያልሆነ የኑሮ ሁኔታን በወዛደሮች ላይ ስለሚስከትል ሞራላቸውን ማጎልበት ብሎም ለእነሱ ሕይወት መሻሻል ትኩረት ማግኘት እንዳለበት ያብራራል። እንደ ኤ.አ.አ 1945 የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን መገባድድ ተከትሎ የእንግሊዝ መንግሥት ጦርነቱ ያዳሸቃትን አገር “የተሻለች እንግሊዝ” ለቀጣዩ ትውልድ በሚል መርሕ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች በዋና ከተማዋ ሎንዶን አዲስ ዕቅድ ይፋ ሆነ። እንግሊዞች አዳዲስ ከተሞችን መቀየስ፣ ነባር የገጠር ከተሞችን ማደስ የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ተጠምደዋል። በልዕለ ኃያሏ አሜሪካም የተቀናጀ የመልሶ ግንባታ፣ የደቀቁና የዳሸቁ የመኖሪያ ሠፈሮች ማፍረስና ማደስ፣ የቤቶችን ጥራትና ቁጥር መጨመር፣ የመንገዶች ግንባታ እንዲሁም አጠቃላይ የከተማ እደሳ ፕሮጀክቶች ሰፊ ዘመቻ ተስተውሏል።
የዚሁ ዕሳቤ ጠንሳሽ ሃዋርድ “ምናባዊ” እየተባለ ይተች የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን ተቀባይነት እያገኘ ለመምጣት በመብቃቱ ተግባራዊነቱ እውን ለመሆን ቻለ። በሌላ በኩል አልፍሬድ ባቀደው የአረንጓዴ ከተማ ፕላን ለአብነት፦ ዕቅዱ 2,428 ሔክታር መሬት ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን ክፍት ቦታዎችን፣ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮችን እንዲሁም ስድስት ዙሪያ ዋና ዋና ‘ቦሌቫርድ’ (ሰፋፊ ውብ የእግረኛ መንገዶች) የያዘ ነበር። የአረንጓዴ ከተሞች ይዘት ጥናቱ እንደሚጠቁመው የመዝናኛ ፓርኮች፣ የተመጣጠነ የመኖሪያ ሰፈሮች፣ ኢንዱስትሪ ቦታዎች፣ የከተማ እርሻን (ግብርናን) ያካትታል።
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ የሞደርኒዝም (ዘመናዊ አስተሳሰብ) በከተማ ቅየሳ መሠረቱን እየጣለ መምጣት የጀመረበት ጊዜ ሲሆን የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች እንደ አርክቴክት ሊ ኮርበዚየር የመሳሰሉ ባለሙያዎች ቢያንስ ለ3 ሚሊዮን ነዋሪዎች የሚዘጋጅ ዘመናዊ ከተማ በልዩ የከተማ ፕላን አቀያየስ ስልት ይዞ ብቅ ያለበት ዘመን ነው። የኮሚኒስቱ ዓለም ከምዕራባውያን የአዘማመን ስልት በመውረስ በተመሳሳይ ሁኔታ የከተማ ቅየሳ አሠራርን በተለይም ለአስተዳደራዊ ቢሮዎች ግንባታ ፕላንን መከተል እንደቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኋለኛው የዘመናዊ አስተሳሰብ ዘመን ማለትም እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ወዲህ በርካታ የከተማ ቀያሾች የክላሲካል ዘመናዊ አስተሳሰብ ያስከተለውን የከተሜነት ቀውስ በሰዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መካከል ልዩነት እያሰፋ መምጣቱን አጥብቀው ይኮንኑ ጀመር። በዚህ ረገድ በከተሞች የአደገኛ ወንጀሎች መስፋፋት እና ተያያዥ የማኅበራዊ ችግሮች አይቀሬነት አበክረው አሳስበዋል። የነባር ይዞታዎችን በማፍረስ የዘመናዊ ከተማ ቤቶች አሠራር ቅየሳ እሳቤ ራስ ወዳድነትን የሀብታም እና ድኻ ስብጥራዊ አኗኗር ማሳያ ሰፈሮች በእንግሊዝና ፓሪስ በመሳሰሉ የአውሮፓ ከተሞች እየተቀዛቀዘ ለመምጣት አስገደዳቸው።
በዚህ ወቅት ጎልተው ከወጡ አመለካከቶች ከሰው ልጅ የሥነ ልቦና ባሕርያት አጥኝዎች በከተማ አቀያየስ ላይ የራሱን ተፅዕኖ ለማሳረፍ የቻለበት ነበር። በተለይም ወንጀሎችን ከመከላከል አንፃር የመኖሪያ አካባቢያዊ ንድፈ ሐሳብ እንዲጎለብት አድርጓል።

ሙሉጌታ ገዛኸኝ የታሪክና ቅርስ ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው gezahegn.mulu@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here