መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብኪን/ጥበብደራሲ፣ አርታኢ እና ተርጓሚ አማረ ማሞ

ደራሲ፣ አርታኢ እና ተርጓሚ አማረ ማሞ

በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ዘታሪክ በደራሲነት፣ ተርጓሚነት፣ ሐያሲነትና አርታኢነት ሥራዎቻቸው በቀዳሚነት ስማቸው ከሚነሱት መሀከል አንዱ የኾኑት አንጋፋው ደራሲ፣ ተርጓሚና ሐያሲ አማረ ማሞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል።
በአሁኑ የደቡብ ክልል ፍስሃ ገነት በተባለ መንደር በ1931 ዓ.ም የተወለዱት ደራሲው ዕድሜአቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት ያዋሉ ናቸው። በዚህም አማረ ማሞ ከ27 በላይ መጻሕፍትን ለአንባብያን አበርክተዋል።

በአርትኦትና በሃያሲነት ጭምር አበርክቷቸው የሚጠቀስላቸው አቶ አማረ ማሞ፣ የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅትን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩም ናቸው። ደራሲው ለአንባብያን ካቀረቧቸው መጻሕፍት መካከል፣ እሪ በል አገሬ፣ አሳረኛው፣ ቁርበኛውና ሱዳን፣ የዴዜዴራታ ምክር፣ አግብቼሻለሁ እና ሳቅና ቁም ነገር 110 የኤዞፕ ተረቶች የሚሉተ የሚጠቀሱ ናቸው።

ደራሲ አማረ ማሞ የቀለም ጠብታ በሚል የኢ-ልብወለድ አጻጻፍ መሠረታዊ መመሪያ መጽሐፍ እንዲሁም የልብወለድ ድርሰት አጻጻፍ የሚሉ ተያያዥነት ያላቸው የድርሰት መማሪያ መጻሕፍትንም ለስነ ጽሑፍ ተማሪዎች አጋዥ ይሆኑ ዘንድ ደርሰዋል።
ከ6 በላይ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ደራሲ፣ አርታኢ እና ተርጓሚ አማረ ማሞ “አሳረኛው” በማለት ወደ አማርኛ የመለሱትን የግብጹን ዝነኛ ደራሲ ነጂብ ማህፉዝን ድርሰት እና ሌሎች ታላላቅ የትርጉም ስራዎችን ለአንባቢ አበርክተዋል።
በአርታዒነትም የበዓሉ ግርማ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ፣ የሙሉጌታ ጉደታን እና የሌሎች በርካታ ደራሲያን ሥራዎች አርትኦት በመሥራት ሥራዎቻቸው ይበልጥ ተነባቢ እና ተወዳጅ እንዲሆኑ አስችለዋል።

ደራሲ አማረ ማሞ ካበረከቷቸው ሥራዎች መካከል የልጆች ወጥ የድርሰትና የትርጉም ሥራዎችም የሚጠቀሱ ናቸው።ከነዚህም በዋናነት፣
የጆናታን ስውፊት …….የጋሊቨር ጉዞዎች
የዳንኤል ዶፍ ………………ሮቢንሰን ክሩሶ
የሚካዔል ሰርቫንቴስ …….ዶን ኪሆቴ
የኤዞፕ ……..ሳቅና ቁም ነገር 110 የኤዞፕ ተረቶች እና
የፍራንሲስ ጆሴፍ …ልዑል ዓለማየሁ
የአለን ፔተን……እሪ በይ አገሬ
የነጂብ ማህፉዝ …….አሳራኛው፣ ይጠቀሳሉ። በነገራችን ላይ፣ የነጂብ ማህፉዝ መጸሐፍ እንግሊዘኛውን ቅጂ (the searcher} ከካይሮ ይዞ መጥቶ በስጦታ ያበረከተላቸው ሐያሲ አብደላ እዝራ እንደነበር ይገለጻል።
መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ትርጉም ሥራዎቻቸው
የካታኩምቡ ሰማዕት
የዋልተር ትሮቢሽ …አግብቼሻለሁ እና አንዲት ወጣት ወድጄ
ማርቲን ሉተር (የፕሮቴስታን መስራቹ) ጥቂቶቹ ሲሆኑ ፣ ወደ ሲውዲሽ ቋንቋ የተመለሰላቸው የእውነት ብልጭታዎች የተሰኘ የአጫጭር ልቦለድ ሥብስብ ሥራም አላቸው፡

ከትርጉም ስራዎቻቸው መካከል በተለይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በላቲን ቋንቋ ተጽፎ በእርሳቸው ወደ አማርኛ የተመለሰው “ዴዚ ዴራታ” ዘመን አይሽሬ ሆኖ ተመዝግቧል።ደራሲ፣ አርታኢ እና ተርጓሚ አማረ ማሞ በኢትዮጵያ መፃሕፍት ድርጅት በዋና ስራ አስኪያጅነት፣ በሻማ አታሚዎች ደግሞ በተርጓሚነት እና በአርታኢነት አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የእድሜ ልክ የክብር አባል የነበሩት ደራሲ፣ አርታኢ እና ተርጓሚ አማረ ማሞ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ባለፈው እሮብ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ቤተሰብና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት የቀብር ሥርዓታቸው ተፈጽሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች