መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየሳምንቱ ጉራማይሌ ስሜቶች

የሳምንቱ ጉራማይሌ ስሜቶች

ይህ ሳምንት ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የደስታም የሐዘንም፣ የእልልታም የእሪታም ስሜቶች የተፈራረቁበት ሆኖ አልፏል። ፈንጠዝያው ከስምንት ዓመታት በኋላ ‹ዋሊያዎቹ› ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን ካሜሮን ላይ ለሚካሄደው ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ሲሆን ድብታው ደግሞ በምዕራብ ወለጋ እና በመተከል ዞን በርካታ ንጹሃን ዜጎች የመገደላቸው መርዶ መነገር ነው።

ማክሰኞ፣ መጋቢት 21 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኮትዲቩዋር አቻው ጋር ባደረገው የመጨረሻ የማጣሪያ ውድድር ምንም እንኳን በሰፊ የጎል ልዩነት ሦስት ለአንድ ቢሸነፍም ለማለፍ መቻሉ፥ ሕዝቡን ከዳር እስከዳር በደስታ ባህር ውስጥ አስምጦ፣ በፈነቀለ ስሜት ወደ አደባባይ እንዲተም አድርጎታል። በርግጥ ጨዋታው በ83ኛው ደቂቃ ላይ በተከሰተው የመሀል ዳኛው ድንገተኛ መታመም ቢቋረጥም፥ የኢትዮጵያን ማለፍ የሚወስን በተመሳሳይ ሰዓት በኒጀር እና በማዳጋስካር ብሔራዊ ቡድኖች መካከል እየተደረገ የነበረውን የጨዋታ ውጤት መጠበቅ ግድ ይል ነበር። አስጨናቂ ደቂቃዎች!

በተለይ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያስጨነቀው በኒጀር እና በኮትዲቩዋር መካከል እየተካሄደ በነበረው ጨዋታ መደበኛ ዘጠና ደቂቃ ያለ ምንም ጎል ቢጠናቀቅም፤ የባከነ ሰዓት ለማካካስ የተጨመረው አንድ ደቂቃ፥ የአንድ ሰዓት ያክል ርዝመት ነበረው። ማዳጋስካር በኒጀር ላይ አንዲት ግብ ብታስቆጥር ነገሮች ሁሉ ይለወጣሉ፤ ኢትዮጵያንም ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊነት ትሰናበታለች። የምጥ ያክል አስጨናቂ ደቂቃ!

ኒጀር በቀሪውም ደቂቃ ጎሏን አላስደፈረችም። ተደጋጋሚ የማዳጋስካር ሙከራዎችን የኒጀር ተከላካዮች አላስደፍርም በማለታቸው ማደጋስካር አንዲት የኢትዮጵያውያንን ህልም ልታጨነግፍ የምትችል ግብ ማግባት አቃታት፤ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ። በሽንፈት ውስጥ አስደሳች ድል! ዋሊያዎቹ ሦስት ለአንድ ቢሸነፉም፥ ቀደም ብለው በሰበሰቡት ነጥብ ወደ አህጉሪቱ ትልቅ የእግር ኳስ መድረክ ከስምንት ዓመታት በኋላ ተመለሱ።

በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ወደር የሌለው ደስታ ተስተጋባ፤ ከተሞች በሆታና እልልታ፣ በመኪና ጥሩምባ ደመቁ። የቴዲ አፍሮ ‹ዋሊያ› እና ‹ኢትዮጵያ› የተሰኙ እንዲሁም ሌሎች ወኔ ቀስቃሽ አገራዊ ዘፈኖች አየሩን ሞሉት፤ የሕዝቡን ስሜት አናሩት። ብሔር፣ ሃይማኖት የሚባሉት ሕዝብ ከፋፋይ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያዎች ልዩነቶች ተረሱ። ከጫፍ እስከጫፍ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት አስደሰተ፣ አስፈነጠዘ። ኢትዮጵያ ተደሰተች!

የብሔራዊው ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የደስታ መግለጫ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ነን። ግዳጃችንን በሚገባ ተወጥተን ለአገራችን ከፍታ በሙያችን በአንድነት የቆምን።. . . ይህ ሕዝብ ከዚህም በላይ ደስታ ይገባዋል›› ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ ደስታ ተሰምቶኛል። ከተሠራ የማይመጣ ውጤት የለም።›› ሲሉ ከታወቂ ሰዎች መካከል ቴዲ አፍሮ በተመሳሳይ ብሔራዊ ስሜታችን ሊጠናከር በሚገባበት በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተቀዳጀው ድል የተሰማኝን ደስታ እገልጻለሁ ብሎ በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፎ ደስታውን አጋርቷል።

ይህንን የደስታ ስሜት በደንብ ለማጣጣም ሳይቻል በነጋታው ረቡዕ፣ መጋቢት 22 ቀን የሐዘን መዶ ተሰማ። በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦሌ ቀበሌ ማክሰኞ ምሽት ላይ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በኦነግ ሸኔ አባለት መገደላቸው እንዲሁም በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን አካባቢ ልብ የሚሰብር፣ አንገት የሚያስደፋ አሳዘኝ ዜና ተሰማ። በብዛት የተገደሉት ደግሞ የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸው ታውቋል። ግድያው በተፈጸመበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አስክሬኖች በየመንገዱ ተጥለው ማየታቸውን ምስክርነትም ሰጥተዋል።

ድርጊቱን በማውገዝ ብዙዎች ብዙ ነገር ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ የተሰማቸውን ሐዘን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ገልጸው፥ ‹‹ኢትዮጵያ በመስዋዕትነት የቆመች፤ በመስዋዕትነት የምትቀጥል ሀገር ናት። በትብብር እና በአንድነት መንፈስ የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግመው እንዳይነሱ ማጥፋት አለብን። ›› የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

የቀድሞው የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዘዳነት፣ አሁን የገቢዎች ሚኒስትር የሆኑት ላቀ አያሌው በበኩላቸው ግድያውን ተከትሎ ‹‹እኔን ጨምሮ ለወንጀለኞች የተለያየ የዳቦ ሥም እያወጣንና በመግለጫ ጋጋታ እያጀብን ዜጎቻችን በየቀኑ ሕይወታቸው እየተቀጠፈ፤ እኛም ተላምደነው በመቀጠላችን እንጂ ከኢትዮጵያዊያን አቅም በላይ ሆኖ አይደለም የሚል አስተሳሰብ አለኝ።›› ብለዋል። ላቀ ወንጀለኞችም የሰው ሕይወትን እንደ ቅጠል መቁረጣቸውን ተያይዘውታል። ይህ ድርጊት በአስቸኳይ ይቆም ዘንድ ወንጀለኞቹና ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ተቋማትና ኀላፊዎች ወደ ፍርድ አደባባይ መቅረብ አለባቸው ሲሉ ጠንካራ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ሰሞኑን ጉራማይሌ ስሜቶችን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ፥ አንዳንዶች የኅልውና አደጋ ተጋርጦባታል ሲሉ በድፍረት ይናገራሉ። መንግሥት በመግለጫ ጋጋታ ምንም አያመጣም፤ መሰረታዊ ከሆኑት መብቶች መካከል የዜጎችን የመኖር መብት ሊያስጠብቅ አልቻለም ሲሉ ሞትን እንድንለማመደው አድርጓል ብለዋል። ሁኔታዎች በዚህ መልክ የሚቀጥሉ ከሆነ፥ ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠዋ ነገር ዋስትና የለውም ሲሉ በርካቶች ስጋታቸውን አልደበቁም።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች