ኢዜማ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ 200 ሺሕ ቤቶችን እገነባለሁ አለ

0
458

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) በ2013 ጠቅላላ ምርጫ በአዲስ አበባ የማሸነፍ እድል ካገኘ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ 200 ሺሕ ቤቶችን እንደሚገነባ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ለመቀነስ በግንባታ ላይ የሚገኙትን በአስቸኳይ በመጨረስ በጥናት ላይ የተመሰረተ የቤት ግንባታ እንደሚያካሂድ ነው ፓርቲው የገለጸው። ኢዜማ በምርጫ 2013 የአዲስ አበባን ኗሪ ይሁንታ ካገኘሁ በቀጣይ አምስት ዓመታት በከተማዋ እሰራለሁ ያላቸውን ባለ 138 ቁልፍ ሥራዎች መጋቢት 29/2013 ይፋ አድርጓል።

ኢዜማ “ብሩህ ተስፋ ለአዲስ አበባ” በሚል ርዕስ 138 ቁልፍ ግቦች የያዘ ለአዲስ አበባ ያዘጋጀውን የቃል ኪዳን ሰነድ ይፋ ባደረገበት ወቅት ፣ በሰነዱ ላይ በቀጣይ አመስት ዓመታት በአዲስ አበባ የሚገነባቸው 200 ሺሕ ቤቶች ከግሉ ዘርፍ፣ ከገንዘብ ተቋማት እና ከከተማ አስተዳደሩ በሚገኝ መዋዕለ ነዋይ እገነባቸዋለሁ ብሏል።

ኢዜማ በምርጫው አሸናፊ ሆኖ አዲስ አበባን የማስተዳደርደ እድል ካገኘ በአምስት ዓመታት የሚገነባቸውን ቤቶች አነስተኛ ገቢ ላላቸው የከተማዋ ኗሪዎች በሽያጭ ወይም በኪራይ መልክ እንድቀርቡ ምቹ ሁኔታዎችን እፈጥራለሁ ብሏል። ኢዜማ ለአዲስ አበባ ካቀረበው ባለ 138 ነጥብ የቃል ኪዳን ሰነድ መካከል የመኖሪያ ቤቶችን እጥረት ማቃለል አንዱ ነው።

በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ኢዜማ በሚቀጥሉት አመስት ዓመታት እተገብራቸዋለሁ ካላቸው ነጥቦች መካከል፣ በከተማዋ በሚገኙ የቀበሌ ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ ቅድሚ በመስጠት የቤቶቹን ባለቤትነት በኹለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ወደ ነዋሪዎቹ በሽያጭ ለማዘዋወር የሚስችል አሰራር እቀይሳለሁ ብሏል። የቀበሌ ቤቶቹ ለነዋሪዎች የሚተላለፉት በሽያጭ እንደሚሆን አክሏል።

የኮንደሚኒየም ቤት ባለቤቶች ባለ ሙሉ መብት ሆነው፣ ቤታቸውን ያለምንም ገደብ መሸጥና መለወጥ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻቻለሁ ያለው ኢዜማ፣ መንግሥት ዜጎችን ከቀበሌ ቤት አስወጥቶ በኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ የዜጎችን ነፃነት ለመገደብ የሚደረግውን አሰራር አነሳለሁ ብሏል።

አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ ብትሆንም በቅድሚያ ለሚኖሩባት ዜጎች ምቹ ሆና እንድትገኝ ማድረግ እንደሚገባ የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ገልጸዋል። ኢዜማ በአዲስ አበባ ከሕዝቡ ጋር ወርዶ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የነዋሪዎቹ ችግር ሥር የሰደደ መሆኑን እንደለየ የገለጹት መሪው፣ ፓርቲያቸው የአዲስ አበባ ነዋሪን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

አዲስ አበባን የከተማዋ ነዋሪ የሆነ፣ የሕዝቡን ችግር የተረዳና በሕዝብ የተመረጠ ማንኛውም ግለሰብ ማስተዳደር እንደሚችል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል። በቂርቆስ ከፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የኢዜማ ዕጩ ክቡር ገና በመዲናዋ ሥር የሰደደውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በአምስት ዓመት ውስጥ ከሚሰሩት ተግባራት በተጨማሪ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ የጋራ ከተማ መሆኗን እውን እናደርጋለን ብለዋል።

የማኅበረሰቡን የገቢ አቅም ያገናዘበ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ግንባታዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ሥርዓት በመፍጠር መዋዕለ ነዋይ የሚያቀርብ የአዲስ አበባ ወለድ አገድ(Mortage) ባንክ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር እንደሚቋቁም ኢዜማ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ጠቅሷል።

“አዲስ አበባ ከተማ ሳትሆን ህንፃ ነች” ያሉት ክቡር፣ ከተማን ከተማ የሚደርገው ሕዝብ ነው ብለዋል። ነገር ግን አዲስ አበባ ላይ አሁኑ ያለው አስተዳደር ሕዝቡን ያቀራረበ ሳይሆን ህንፃ በመገንባት ላይ ያተኮረ ነው ብለውታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here