ቅድመ ምርጫ ሂደት ያሳስበናል!

0
316

ኢትዮጵያውያን መሪዎቻቸውን በነጻነት መርጠው አያውቁም። በወደዱት እና በመረጡት አስተዳዳሪ ሥር ሆነው በካርዳቸው ያሻቸውን ሾመው፣ ያልወደዱትን ሽረው አያውቁም። ለሺህ ዓመታት በዘለቀው የነጻነት ታሪክ የውጪ ገዢን እምቢኝ ማለት በለመዱበት ቋንቋ፣የአገር ውስጥ ጨቋኝ ሥርዓቶች እምቢኝ ብለው ያልፈለጉትን አገዛዝ አስወግደው፣ በምርጫ ካርድ ብቻ መተዳደር የሚችሉበትን የረጅሙን የነጻነት ታሪካቸውን የሚመጥን ተክለ ሰውነት ያለው ምርጫ አለማድረጋቸው የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው።
በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ምርጫ ብለን ካነሳን የምናወራው ስለ 1997 እንደሆነ እሙን ነው። እሱን እንድናታውስ የሚያስገድደን መቼስ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ በመሆኑ ሳይሆን በቅድመ ምርጫ ሂደት ከዓይነ ህሊናችን በማይጠፉት የቴሌቪዥን መስኮት ቅስቀሳዎች እና የአዳራሽ ስብባዎችን እንዲሁም የአደበባይ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች እና ክርክሮች እንደሆነ ይታመናል።

በእርገጥ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በአደባባይ ‹እንከን የለሽ› ምርጫ እናደርገዋለን ሲሉ መደመጣቸው መንግስታቸው ለምርጫው ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳየበት ተደርጎ ተቆጥሮ ስለነበር የአያሌ ኢትዮጵያውያንን ብርቱ ተስፋ ያሰነቀ ፣የሕብረተሰቡንም የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር ያደረገ እና ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ምርጫ ካርድ ከመውሰድ አስከ ድምጽ መስጠት የተሳተፈበት ትልቅ ክስተትን ያስተናገደ የምርጫ ዘመን ነበር። የኋላ ኋላ ጭቃ ጅራፉን አዘዘብን እንጅ!

ከሦስት ዓመታት በፊት የተከሰተውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አቢይም በተመሳሳይ ‹በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ምርጫ› እናደርጋለን በማለት በተደጋጋሚ በአደባባይ ሲናገሩ ሰምተናል። በእርግጥ ምርጫው ቦርድን የሚታመን ትልቅ ሰብዕና ባላቸው ግለሰቦች እንዲመራ ለማድረግ እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለሙ የምርጫ ህጎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ይህ ተግባር በራሱ የምርጫውን በነጻ እና በፍትሃዊነት እንዲሁም በተአማኒነት እንዲከናወን መነሻ ይሆን እንደሁ እንጅ በቂ አይደለም።

በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚዎች ከማንም በላይ ለምርጫው ስኬት ትልቅ ሚና አላቸው ብለን እናምናለን። የክልል መንግስታት ምርጫ ቦርድን ማገዝ ይገባቸዋል ብቻ ሳይሆን የማገዝ ግዴታም ጭምር ያለባቸው መሆኑን አውቀው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል።
በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት ምርጫውን ለማከናወን የሚያስፈጉ ቢሮዎች ከመስጠት፣ የፖሊስ አባላት ከመመደብ ባለፈ ሰፊ ተግባር የሚጠበቅባቸው ቢሆንም እያሳዩት ያሉት ትብብር አናሳ እንደሆነ ቦርዱ በሳምንቱ አጋማሽ ካቀረበው ሪፖርት ሰምተናል። በዚህም ምክንያት እስካሁን ሳይከፈቱ ለቀሩት ምርጫ ጣቢያዎች እንዲሁም እሱን ተከትሎ እጅግ ለሳሳው የመራጮች ምዝገባ ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል እንላለን። ከዚሀም በዘለለ በህግ ጭምር ሊጠየቁ እንደሚገባ እናምናለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በመላ አገሪቱ መከፈት ከነበረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ወደ 24 ሺህ ገደማ የሚሆኑት ተከፍተው አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን አስታውቋል። የመራጮች ምዝገባም እየተካሄደ ባሉባቸው ጣቢያዎችም ቢሆን ቀርበው የተመዘገቡ ዜጎች ቁጥር ከ 300 ሺሕ በታች መሆኑ አስደንጋጭ ነው። በመዲናይቱ አዲስ አበባ እንኳን እየተከናወነ ባለው የመራጮች ምዝገባ በርካታ ዜጎች ተመዝግበው የምርጫ ካርድ አለመውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በአዲስ አበባ የተመዘገበው ሰው ብዛት 200,903 ብቻ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።

በመላው አገሪቱ ምርጫውን ለማከናወን በሚከፈቱት 50 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች በአስፈጻሚነት፣ የሚመደቡ 150 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚ አበላትን ግን በቦርዱ ቁጥጥር ስር ብቻ መልምሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉ ቦርዱን የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነ እናምናለን።

በሌላ በኩል ያልተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው ከሎጀስቲክ እና የጸጥታ ችግሮች የተነሳ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።በእርግጥ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ እንረዳለን ፤ ነገር ግን በዚህ ደረጃ ቁጥሩ ለመሳሳቱ በቂ ምከንያት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። የፖለቲካ አባላትን ማስፈራራት፣ ማዋከበ፣ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ማስተጓጎል፣ ፖስተሮችን እንዳይለጥፉ መከልከል፣የተለጠፉትንም መቅደድ፣ ከደጋፊዎችቸው ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ፣ ከስራ ገበታቸው ማባረር፣ ብሎም እጩ ተወዳዳሪዎችን በሰንካላ ምክንያት ማሰር ከምንም በላይ በራፋቸው ላይ መግደል ልንላቀቃቸው ያልቻልናቸው ክፉ የፖለቲካ ነቀርሳዎች ናቸው። እነዚህ እኩይ ተግባርትን እና ኢ-ፍተሃዊ ፖለቲካዊ ኩነቶችን ልንሽራቸው እና ልንሻገራቸው ይገባል በማለት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ይህ ካልሆነ ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ሕዝባችን ባለው ችግር ላ ሌላ ችግር ማከል እና አገራችንን የማትወጣበት የፖለቲካ ቅረቃር ውስጥ መጨመር ነው። በተለይ በታችኛው የመንግስት እርከን ላይ የተቀመጡ የገዢው ፓርቲ አመራሮች የመንግስትን ሥልጣን በመጠቀም ከህግ አግባብ ውጪ የፖለቲካ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎችም ላይ ሆነ አባላት ላይ የሚያደርሱትን ወከባ ፣ እስር፣ ግድያ፣ወዘተ. በአስቸኳይ ሊያቆሙ ይገባል እንላለን።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ ሆኖ ህዝብ የመረጠው የፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣን ላይ ቢወጣ እንዲህ እነሱ ሊያገኙት የሚችሏቸውን ጥቅማ ጥቅሞች ሊያስቀር የሚችል ቢሆንም አገርን ከቀውስ አውጥቶ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ሊያሻግር የሚችል ሂደት ስለሆነ ከራስ ጥቅም አገርን ማስቀደም ተገቢ እንደሆነ አምነው ጠቅላይ ሚንስትሩ ምረጫውን ታሪካዊ ማድረግ አለብን ብለው በአዳባባይ በሚናገሩት ልክ ታችኛው የመንግስት እርከን ያሉ የመንግስት ሹመችም ሊሰሩ ይገባል እንላለን።

በተመሳሳይ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተብለው ለተፈናቃዮች እና ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ይከፈታሉ የተባሉ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችም እስካሁን ድረስ ሙሉ ለመሉ መክፈት አለመቻሉን ለዚህም ከመከላከያ ሚንስቴር ትብብር ማነስ እንደሆነ መስማት ግር የሚያሰኝ ጉዳይ ነው። ቅቡልነት ያለው መንግስት በመጥፋቱ እዚህም እዚያ ኮሽ ባለ ቁጥር ከተልእኮው እና ተግባሩ ውጪ መንደር ውስጥ ሳይቀር እየገባ የሚሞተው የመከላከያ ሰራዊት አገሪቱን ወደ ተሻለ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና መሻገር የሚያስችል ምርጫ እንዲከናወን የሚያስችል መደላድል መፍጠር ሲገባው ለሰራዊቱ አባላት ምርጫ ጣቢያ እንዳይቋቋሙ እንቅፋት መሆኑ እሳት እራስ ላይ እንደመለኮስ እንደሆነ ቆጥሮ ምርጫ ጣቢያዎቹ በፍጥነት እንዲቋቋሙ የሚያስፈልገውን ስራ ሊሰራ ይገባል እንላለን። እነዚህን የቅደመ ምርጫ ተግባራት በተገቢው መንገድ ማሳለጥ የምርጫ ወቅት ተግባራቱ አነጻራዊ በሆነ መልኩ ለማሳካት መነሻ ይሆናል ብለን እናምናለን።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ምርጫው ታሪካዊ ሆኖ አገር የሚያሻግር እንዲሆን የድርሻቸውን ሊያበረክቱ የሚችሏቸውን ተግባራት ሁሉ በትብብር መንፈስ በመስራት ከአሻጋሪ ጠቅላይ ሚንስትር ባሻገር ፣አሻጋሪ የሆነ ምርጫ እንዲደረግ እና እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንድናተርፍ የሚያደርግ ምርጫ እነዲሆን ሊሰሩ ይገባል እንላለን።

መጪው ምርጫ እንደ አገር በአራት ማዕዘን የተጋረጡብንን አደጋዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ከግል እና ከፓርቲ ጥቅም በዘለለ ትውልድን እና አገርን የሚጠቅም እና የሚያሻግር፣ እንደተባለው እውነትም ታሪካዊ እንዲሆን ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብላ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here