የእለት ዜና

ቀልዱን ተው!

Views: 733

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ዕድሜ ይቀጥላል፣ ጤናማ ያደርጋል የሚባልለት ሳቅ እና ፈገግታ ምንጩ ብዙ ነው። በጆሮ ከሚሰሙ ፈገግታና ሳቅ አጫሪ ምክንያቶች ባለፈ፣ መቼም ከክፋት ጽፈነው ባናውቅም፣ አዳልጧቸው በሚወድቁ ሰዎች የበለጠ ይሳቃል። ታድያ አወዳደቁ ጉዳቱ ካላመጣ የወደቀውም ሰው አብሮ መሳቁ አይቀርም! የሚያስቁንን ኹነቶች ልብ ብላችሁ ካያችሁም እንዲህ ያሉት ናቸው። በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሳይቀር የምንጋራቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ከዚህ የራቁ አይደሉም።

ከዚህ ውጪ ሲሆን ደግሞ ኮሜድያንን እናገኛለን፤ ቀልድ ፈጣሪዎች። እንደ ልብወለድ፣ እንደ ፊልም ድርሰት ሁሉ ቀልድ የሚፈጥሩ ሰዎች አሉ። በእርግጥ ሰዉን ማሳቅ መቻል ፈጥኖ ማሰብና ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ ማየት መቻልን ይፈልጋልና ቀላል አይደለም። አሁን የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሁሉንም ዓይን በሰረቁበት ጊዜ ደግሞ፣ እንደ “ኢትዮጵያን ሜም” ያሉ ገጾች ተከፍተው እናገኛለን።

ታድያ ግን ምን ቢቀለድ የማይቀለድባቸው ነገሮች ደግሞ አሉ። ለምሳሌ በተፈጥሮና በሰው ማንነት መቀለድ ትክክል አይደለም። ይህም ስለሆነ ነው ኮሜድያን ሳይቀሩ ቀልድ ለመፍጠር “እኔ” እያሉ በራሳቸው የሚቀልዱት። በእርግጥ እንደ አጠቃቀሙ ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ በሰዎች አነጋገር ‘ዘዬ’ ተመሥርተው የሚቀርቡ ቀልዶች አሉ፤ አሁን ስለተለመዱ ይመስለኛል በዘዬው የሚናገሩት ሳይቀሩ አብረው ይስቃሉ። እንዲህ ያሉ ቀልዶች የሆነን የማኅበረሰብ ክፍል የሚነኩ ቢሆኑ እንኳን ከዛ ይልቅ የቀልዱ ጭብጥ ሊልቅ ይችላልና ነው።

ይህ ግን በብዛት የሚታይ አይደለም። ቀልዶች የሰዎችን ስብዕና የሚነኩ እየሆኑ ነው። በተለይም ሴቶችን በተመለከተ የሚቀርቡ ቀልዶች በእጅጉ የሚያሳዝኑ ናቸው። ቀለድ አዋቂዎች ወንዶች ብቻ ሆነው ይሆን? አላውቅም። ተሸከርካሪዎች ላይ ከሚለጠፉ ጥቅሶች አቅም “የድሮ ሴት እግር፣ የዛሬ ሴት ኪስ ታጥባለች” ዓይነት አባባሎችን ታዝበናል።

ብዙ ተመልካችና ተከታይ ያላቸው የቀልድ ማኅበራዊ ገጾች ታድያ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ብዙ ቀልድ ሊፈጠርባቸው የሚችሉ ሁኔታዎች ባሉበት ሴቶችን የቀልድ ግብዓት ማድረግ ተገቢ አይደለም። በቀልዶቹ ውስጥ ተስለው የሚታዩት ሴቶች ከተለመደው ፊልሞችና የሙዚቃ ቪዲዮዎች ከሚታሙበት የተለየ ስላይደለ ነው።

ቀልድ ተብለው የሚቀርቡ ‘ቀልዶች’ በተባለው መልክ ክብር ሲነኩ፣ አንዱን ‘አስቀው’ ሌላውን ሲያሳቅቁ ቀልድ ሳይሆን ‘ቧልት’ ይባላሉ። በአንጻሩ በውጭ አገራት ከቀልድ ጋር በተገናኘ የተሠሩ ጥናቶች ያሉ እንደሆነ ‘ጎግል’ን ጎራ ብላችሁ ብትጠይቁ፤ የቀልድን ማኅበራዊ አገልግሎት በሚመለከት ትኩረት እንደሚሰጠው ይነግራችኋል። እንደውም በትምህርት ስርዓት ላይ ይህን ማካተት ተማሪን በትምህርት ቤት ቆይታው ሊያግዝ ይችላል የሚሉ ጥናቶችና መጽሐፍትም አሉ።

በእኛም አገር እዚህ ባይደርስ እንኳን “በዚህማ አይቀለድም” ተብለው እንደማይነኩ የሃይማኖትና የብሔር ጉዳዮች ሁሉ፤ የሴቶች ጉዳይም ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። ቀልድ በጋራ ሊያስቀን እንጂ አንዱ በሌላው ላይ ይሳቅ የሚል መርህ ያለው አይመስለኝም። እንዳልኳችሁ ይህን ለማስቀረት ነው ቀልድ ተናጋሪዎችም በራሳቸው መቀለድ የሚያዘወትሩት።

እንዲህ እንድል ያስገደዱኝን ቀልዶች ወዲህ አምጥቶ መዘርዘሩ ተገቢ ስላልመሰለኝ ትቼዋለሁ። እና ግን ምን ለማለት ነው? በማኅበራዊ ድረ ገጽ ቀልድ የምታከፋፍሉ ሆይ! ከተቀለደም አብረን እንሳቅ እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲስቅ አታድርጉ። የሴቶችን ክብር የሚነካ፣ በሴቶች ክብር የሚሳለቅ ቀልድ እንዳታሰፍሩ ‘ሴት እህትህ ናት! እናትህ ናት! ልጅህ ናት!’ የሚል ማባበያ የሚያስፈልጋችሁ አይመስለኝም። ቀልድ መፍጠር የሚችል አእምሮ ይህን ማሰብ ይሳነዋል ተብሎ አይጠበቅምና።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com