መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን እያገኙ ይሆን?

ተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን እያገኙ ይሆን?

መቋጫ ያላገኘው የተፈናቃዮች እሮሮ

ኢትዮጵያ አይታው የማታውቀው ግፍ እያስተናገደች ትገኛለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝቡ የነበረው ተስፋ እንዲሟጠጥ ካደረጉ ምክንያቶች ዋናው ማብቂያ ያልተገኘለት የዜጎች ግድያና መፈናቀል ነው።
ህዝቡ በሰላም ሰርቶ መኖር እንዳይችል ከሚፈፀምበት ደባ መካከል በተወለደበት ቀዬ መኖር አትችልም እየተባለ በገፍ የሚፈናቀልበት መንገድ እያደር መባባሱ አሳሳቢ ሆኗል።
በኢትዮጵያ አሁን ከ2.3 ሚሊየን በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን አለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ይናገራል።
እነዚህ መድረሻ ያጡ ኢትዮጵያውያን በምን አይነት ሁኔታ ተጠልለው እንደሚገኙ፤ ምን ያህል እርዳታ እንዳገኙ ከእነሱ አንደበት፤ እንዲሁም መንግሥት ስለስደተኞቹ ምን እንደሚል የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ አነጋግሯተው የተፈናቃዮችን ጉዳይ የሳምንቱ የሀተታ ጭብጥ አድርጎታል።

ኢትዮጵያውያን በሩቅ የምንሠማ የነበረው ግፍና በድል እዚሁ ደጃፋችን ደርሶ ለምደነው ለሰቆቃ ጆሮ ዳባ ልበስ የምንልበት ጊዜ መጥቷል። አንድ ችግር ሳይፈታ ሌላው እየተደረበ ሞትና መፈናቀልን ውድመትን እንድንላመድ ተደርገናል። ለረጅም ዘመናት ህዝብና መንግሥት ጎራ ለይተው ሲጠዛጠዙ እንዳልነበር፣ አሁን ታጣቂ በህዝብ ላይ ህዝብም በህዝብ ላይ መነሳቱ አዲስ ነገር አልሆነም። ቀደም ባለው ጊዜ “ህገወጥ ሠፋሪ” እየተባለ ለአመታት ያፈራው ሀብት በመንግስት እየፈረሰበት ጎዳና የሚወድቅና በየቦታው ተፈናቅሎ የሚቀር ዜጋ ነበር። በተፈጥሮ አደጋ መፈናቀል ብርቅ እስኪሆን ድረስ ሰው ሰራሽ በሆነ የእኩዮች ተግባር በሚሊዮኖች እየተፈናቀሉ፣አንጀት የሚበላው ነገርተፈናቅለው ዞር ብሎ የሚያያቸው ያጡ መኖራቸው ነው።ማንለምን አፈናቅላቸው የሚለውን ለጊዜው ትተን፣ ሠሞኑ የበአል ወቅት እንደመሆኑ ተፈናቃዮቹ ስላሉበት ሁኔታ፣ ማን እየደረሰላቸው እንደሆነ፣ የት እንዳሉና ብዛታቸው ምን ያህል እንደሚሆን እንመለከታለን።

ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ድህነቷ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ ስደተኞችን ተቀብላ መጠለያ ጣቢያ አዘጋጅታላቸው እየተንከባከበች ታኖራቸዋለች። እንደአለምአቀፉ የስደተኞች ተቋም መረጃ ከሆነ ኢትዮጲያ ከ884ሺ በላይ የ26 ሀገር ስደተኞችን ተቀብላለች። ለተፈናቃዮቹ ከአለም አቀፍ ለጋሾች ብር እየተቀበለች የተሻለ ነገር እንዲያገኙ የምትጥረውን ያህል ለራሷ የውስጥ ተፈናቃዮች እንዳልሆነች ብዙዎች ይናገራሉ። በያዝነው ሳምንት ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ የሶሪያ ስደተኞችን ከጾም እንዲያፈጥሩ ያደረጉት እገዛ ለብዙዎች ማነፃፀሪያ ተደርጓል። ያደረጉ ተግባር የሚያስመሰግን ቢሆንም ሀገራቸውን ጥለው ያልተሰደዱ ከመኖሪያ ቀዬአቸው በጉልበተኞች የተፈናቀሉትን የዘነጉ መሆኑን ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ጠቅሰዋል። ይህ የምን ያህሉ ኢትዮጵያዊ ሀሳብ እንደሆነ መገመት ከባድ ቢሆንም፣ መንግስት ለተፈናቃዮች የሚጠበቅበትን እንዳላደረገ ብዙዎች ይስማማሉ። እስከ ዛሬ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያንብዙ ቢሆኑም፣2.3 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተያዘው የፈረኝጆቹ አመት መኖራቸውን አለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም በድህረገፁ ይፋ አድርጓል።

ተፈናቃዮቹ በቡድን በቡድን ሆነው እንደመጡበት አካባቢ ይለያያሉ። በሱማሌና ኦሮሚያ ክልል መካከል በተፈጠረ ግጭት በሚሊዮን የተቆጠሩ ከኖሩበት አካባቢ መፈናቀላቸው ይታወሳል። እነዚህ ተፈናቃዮች ሌላ ቦታ አስፍሩን ብለው ሳይጠይቁ፣ አዲስ አበባ መጥተው ቤት ተሰርቶላቸው እንዲሰፍሩ መደረጉን የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ለማ መገርሣ ለህዝብ ይፋ አድርገውት ነበር። ለእነሱ የተደረገው ትብብር ግን ብዙ ሳይቆይ በሚሊዮኖች ለተፈናቀሉት ጌዲዮዎች አልተደረገም። ወደ ነበሩበት በግድ እንዲመለሱ ስለመደረጉ የተወራውን ያህል እውነት ይሁን አይሁን ባይረጋገጥም፣ ሁሉም በተለያየ መንገድ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ መደረጉን መንግሥት ይናገራል። በሌላ በኩል፣ ከአዲስ አበባና በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ዞኖች “ህገ ወጥ ሠፋሪ” ተብለው በመንግሥት የተፈናቀሉት መድረሻ አጥተው በክረምት ተቸግረው እንደከረሙ ያለፏት 2 አመታት መነገሩን የሚዘነጋ የለም። ቤታቸው ፈርሶባቸው መጠለያ ያጡት በርካታ የመሆናቸውን ያህል ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ቤታቸውን ያጡ ህፃናት የብዙዎችን ትኩረት ስበው ነበር። የቤት ማፍረሱ ሂደት በጨለማ እንዲደረግ ከተደረገ ወዲህ የክስተቱ አንገብጋቢነት እየቀነሰ የተፈናቃዬቹም መጨረሻ ተዘንግቷል። ቤተክርስቲያን የተጠለሉ ሳይቀር እንዲወጡ ቤተክርስቲያንን እስከ ማስገደድ የተደረሰበት አካሄድ አሁን ጋብ ያለ ቢመስልም ሙሉ በሙሉ እንዳልቆመ ይነገራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ወቅቶች የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ሸሽተው ከሞት አምልጠው ወደ ከተማ የሚመጡ በርካታ ተፈናቃዮች አሁንም አሉ። ግጭት ፈርተው ከሚሸሹት በበለጠ የፍረጃ ስም እየተሰጣቸው በግድ ለቀው እንዲወጡ የሚደረጉት በርካቶች መሆናቸው ይታወቃል። ለነዚህ ሞትን ሸሽተው ንብረታቸውን ጥለው ባዶ እጃቸውን ለቀሩ ተፈናቃዮች ግን መንግሥት ያሳየው ምላሽ ያስተዛዘበ ነበር። ዝም ከማለት አንስቶ በአውቶቡስ እያሳፈሩ ባህር ዳርን የመሳሰሉ የክልል ከተሞች በማፍሰስ ብዙዎችን ያሳዘነ ተግባር ተፈጽሟል። የአዲስ አበባን ገጽታ ታበላሻላችሁ በሚል አመለካከት በፖሊስ እያስገደዱ ከተጠለሉበት ማፈናቀሉ የመንግስት መንታ መመዘኛዎችን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር።

ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈናቀሉት አብዛኞቹ በ1977 ድርቅ ምክንያት ከወሎና አካባቢው መንግስት ወስዶ ያሰፈራቸው ነበሩ። ከቀዩአቸው ሲወሰዱ ተገደው የሄዱት እነዚህ መድረሻ ያጡ ዜጎች አሁን ደግሞ ከለመዱበት ወልደው ካሳደጉበትና ንብረት ካፈሩበት በግድ ውጡ ሲባሉ ዘመድ አዝማድ ወደሌለበት አማራ ክልል ለመመለስ ተገደዋል። በቆቦ በወልዲያ በሀርቡና በመሳሰሉት የአማራ ክልል ግዛቶች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያና በየሰው ቤት ጥገኛ ሆነው ለመኖር የተገደዱት ተፈናቃዮች፣ አመታት ቢያስቆጥሩም መቋቋሚያ የሚሆን መሬትም ሆነ ዘላቂ ዕርዳታ እንዳላገኙ ይናገራሉ። በየተወሰነ ጊዜው ከሚያገኙት እህል ሌላ መኖራቸው እንኳን እንዳይታወቅ ጎብኝን የሚያመላልሱበት ጊዜም ነበር። “ወደመጣችሁበት ካልተመለሳችሁ አንረዳም” በሚል ተፈናቃዩ እንዲደናገርና እንዲጨነቅ ተደርጎም ነበር። አንዳንዶች አገር አቋርጠው ተመልሰው ቤታቸው ሲሄዱ በጎረምሳ ተወርሶ ለነፍሳቸው ሲሉ ዝር እንዳይሉ ተመክረው በድጋሚ ተሰደው የቀሩ አሉ። በሌላ በኩል፣ በቤኒሻንጉል ክልልም ተመሳሳይ የመግደልና የማፈናቀል ተግባር ተፈጽሞ ከ200 ሺህ በላይ ቤት ንብረታቸውን ትተው ህይወታቸውን ለማትረፍ እየባዘኑ ይገኛሉ።

የተፈናቃዮች መጠን መቀነስ ሲገባው እያደር እየጨመረ የሌሎች ስጋትንም እንዳይቆም አድርጓል። በቅርቡ በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ የአማራ ክልል ግዛትበተፈጠረ ጥቃት የተፈናቀሉት ቁጥር ለስጋቱ መቀጠል በቂ ማስረጃ ነው። ለ4 ጊዜያት ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ ማረጋጋትም ሆነ ችግሩን መፍታት ባለመቻሉ ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች በቀናት ውስጥ ተፈናቃይ ሆነዋል። አንድ ከተማ ሙሉ በሙሉ በመውደሙ የለበሱትን እንደለበሱ ህይወታቸውን ለማትረፍ በየአቅራቢያ ከተሞች የገቡት በርካቶች ናቸው። እነዚህ ከሞት አፋፍ ያመለጡ ዜጎች ሀብት ንብረታቸው ወድሞ በጊዜያዊ መጠለያና በየግለሰብ ቤት እንዲሁም በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች በመሃል ሜዳ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኝ አንድ የአጣዩ ከተማ ነዋሪ ግለሰብ ብሶቱን ተናግሯል። በቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ ከተጠለሉ በርካታ ቀናት ቢሆናቸውም ከመንግሥት በኩል መጋዘን እንዲጠለሉ ከመደረጉ ባሻገር መጥቶ የጎበኛቸው እንደሌለ እኚህ ተፈናቃይ ነግረውናል። በዚህ በኮሮና ዘመን እንዲህ በመጋዘን ተጨናንቀን ከጥይትና እሳት የተረፍን ሰዎች በወረርሽን እንዳናልቅ ሲሉ ስጋታቸውን አሳውቀውናል። የአካባቢው ህብረተሰብ ሳይሰለች ምግባችንን እያቀረበልን ነው ያሉን ሲሆን፣ ከነዋሪው አብዛኛው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ ስለሚገኝ እንደ መጀመሪያው እኛን ማገዝ ስለማይችል መንግሥት ሊደርስልን ይገባል ብለዋል።

ግለሰብ የእርዳታ አስተባባሪዎች ለምነው ባገኙት በጎደለው እየሞሉልን ነው ማለታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ረጂዎችን በማስተባበር ላይ የነበሩትን ገዛኸኝ ፀጋዬን አነጋግረናል። እንደ እሳቸው አመለካከት ህብረተሰቡ ጥሩ እየረዳ ቢሆንም በቂ አይደለም። በጥቃቱ የተፈናቀሉትን 250 ሺህ ለመርዳት አስቸጋሪ መሆኑን የነገሩን ሲሆን፣ አብዛኛው ከመጠለያ ውጭ በየግለሰብ ቤትና በየበረንዳው ስለሚገኝም ለማዳረስ አስቸጋሪ መሆኑን አሳውቀውናል። በተመሳሳይ “ደራሽ ለአጣዩ” በሚል ስያሜ እርዳታ በማሰባሰብ ላይ የሚገኘውን ኮሚቴም አዲስ ማለዳ አግኝታለች። የዕርዳታ ማሰባሰቡን ሂደት የሚያስተባብሩት በአዲስ አበባ የሚገኙ ወጣቶች ሲሆኑ፣ በበጎ አደራጎት ስራ በተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመታገዝ በጣይቱ ሆቴል ዕርዳታ እየሰበሰቡ እንደሆነ ነግረውናል። ገንዘብ በእጅ እንደማይቀበሉ የተናገሩት አስተባባሪዎቹ በንግድ ባንክና በአቢሲኒያ ባንክ በኩል አሊያም በዕቃ መልክ የሚሠጡትን ሆቴሉ ሆነውእንደሚቀበሉ ነግረውናል። ከዚህ ቀደም ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉ እንድ FSR ሙሉ እቃ እንደላኩ ያስታወሱ ሲሆን፣ አሁንም ለተረጂዎቹ የሚሆን ቁሳቁስን እንደሚያከፋፍሉ ተናግረዋል። የተረጂዎቹን መጠንና ያሉበትን ሁኔታ አጣርተው ራሳቸው ሄደው ለማከፋፈልና እስካሁን ድጋፍ ያላገኙ ተፈናቃዮችን ቅድሚያ ለመስጠት ማሰባቸውን ሠምተናል።

የግለሰብ አስተባባሪዎች የነገሩን እንዳለ ሆኖ፣ ተፈናቃዮቹ የነገሩንን ስሞታ ይዘን ወደ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አምርተናል። የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ደበበ ዘውዴ እንደነገሩን፣ በአማራ ክልል ካሉ 600 ሺህ አጠቃላይ ተፈናቃዮች ውስጥ 253 ሺህ የሚሆኑት ከአጣዮና አካባቢዋ የተፈናቀሉ ናቸው። በአማራ ክልል በ11 ዞኖች ውስጥ በጊዜያዊ መጠለያና በማህበረሰቡ ውስጥ ለሚገኙት ተፈናቃዮች መንግሥት የምግብ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ይናገራሉ። በትግራይ ክልል ከ2.4 ሚሊዮን እስከ 4.5 ሚሊዮን ለሚሆን ተረጂ ምግብ መከፋፈሉን ያስታወሱ ሲሆን፣ 70 በመቶው በመንግስት ሲሸፈን የተቀረው ቃል የገቡ ረጂዎች ያሉትን ያህል ሳይፈጽሙ እነሱ የሰጡት ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ ከክልሎች በሚመጣለት መረጃ መሠረት አስልቶለየክልሉ ቢሮዎች እርዳታውን እንደሚያስረክብ ነግረውናል። የሰሜን ሸዋ ተፈናቃዮችን በተመለከተ እስካሁን ደብረ ብርሃንና ደብረሲና ከተሞች ላሉት እህል ተልኮ እንደደረሰ መረጋገጡን አሳውቀውናል። በተጨማሪም በተያዘው ሳምንት ለክልሉ እንዲደርስ መደረጉን ያወሱ ሲሆን፣ የማከፋፈሉ ተግባር የክልሉ ነው ብለዋል። በማዕከል ደረጃ የመቆጣጠር ኃላፊነት ነው ያለብን ያሉት ኃላፊው፣አልደረሰንም የሚል ተፈናቃይ ካለ መጠየቅ የሚኖርበት ክልሉን ነው ብለውናል። ተረጂዎች እየተሰጣቸው አልተሰጠንም የማለት ልምድ እንዳላቸው ከጌዲዮ ተፈናቃዮች ያስተዋልነው እውነታ ነው ያሉን ሲሆን፣ ጋዜጠኞች ግለሰቦችያሉትን ብቻ ተመርኩዘው ለህዝብ ማቅረብ የለባቸውም በማለት በአካል ተገኝቶ ማጣራት እንደሚጠይቅ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። እርዳታ በሚከፋፈልበት ወቅት ጋዜጠኞች እንዲገኙ ይደረጋል ያሉን ሲሆን፣ እስካሁን ግን ከመንግሥት የሚጠበቀው እየተደረገ ነው ብለዋል። በተመሳሳይ፣ ከ200 ሺህ ለሚበልጡ የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮች በመተከልና ካማሺ ዞን በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ አስታውሰዋል። ከቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ 8 የምግብ ማከማቻ መጋዘኖች በተጨማሪ ሌላ ለመገንባት ታቅዷልም ብለዋል።የእሳቸውን ሰምተን የክልሉን ቢሮ ለማናገር ብንሞክርም መልሰን እንደውላለን ተብለን ሳይሳካ ቀርቷል።

ለተፈናቃዮች መንግሥት በተገቢው መጠን እንዳልደረሰላቸው ለማንም ሚስጥር አይደለም። ሲጀመር እንዳይፈናቀሉ ማድረግ ሲገባው ያን ሳይችል ቀርቶ ተፈናቅለዋል። ቤት ንብረታቸው ወድሞ ጥገኛ ሆነው ለመኖር የተገደዱትን መልሶ ለማቋቋም አቅሙ ባይኖረው እንኳን የውጭ ሀገር ስደተኞች የሚያገኙትን እንክብካቤ ያህል መንፈግ እንደሌለበት ግልጽ ነው። ግለሰቦች የሚሰበስቡትን እየነጠቁ፣“እኔ ነኝ የማከፋፍለው” ማለቱ ተገቢ ባይሆንም፣ሂደቱ ለህገ ወጥ ተግባራት እንዳይጋለጥም በመቆጣጠር፣ ሰው መርጦም ቢሆን ለፈለገውየመርዳት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። ዜጋን ሳይለይ የሚያስገብረው መንግሥት ግን፣ ዜጋው ባይሆንም ሰውን ከሰው ሳይለይ የአቅሙን ማድረግ ይጠበቅበታል። ካልቻለ አልቻልኩም ይበል እንጂ፣ እየረዳሁ ነው ብሎ ሌሎችን ከመደገፍ እንዳይገድብም እውነታውን ማሳወቅ አለበት። ምን ያህል ተፈናቃይ የት የት እንዳለ በመዘርዘር፣ ለአንድ ግለሰብም ሆነ አባወራ ምን ያህል እርዳታ ለምን ያህል ጊዜ እንደደረሰው ሪፖርት እየተዘጋጀ ረጂውም ሆነ ተረጂው በግልጽ እንዲያውቀው መደረግ አለበት።

“አላገኘሁም ብሎ ማማረር ልምድ ሆኗል” እንዳሉን ኃላፊም፣ እውነታው ያ ሆኖ ከተገኘ የረጂዎችን መንፈስ የሚረብሽና “ባጎረስኩ ተነከስኩ” አስብሎ የባሰ ችግር ውስጥ ስለሚከት ለሌላው ለባሰበትም ማሰቡ ለሁሉም ይበጃል። መንግሥት በበኩሉ ንብረት ለወደመባቸው ጥቂት ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ኦሮሚያ ክልል ላይ እንዳደረገው አሁንም ከአጥፊው ወይም መጠበቅ ከነበረበት አካል ካዝና መዝዞ በካሳ መልክ ማቋቋም ይጠበቅበታል። በተፋፈገ ሁኔታ ታጭቀው ከጥይት ተርፈው የመጡት ዜጎች በኮሮና እንዳያልቁ ሠፋ ወዳለ ቦታ ማዘዋወር፤ ይህ ካልተቻለም ጊዜያዊ ደንኳን እንደሌሎች ሀገራት በማዘጋጀት የአደጋ ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እንደሚገባው ችግሩን የተመለከቱ ይናገራሉ።

አሁን ወቅቱ የበአል እንደመሆኑ ተፈናቃዮቹ የደስታ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ባይቻልም፣ የበለጠ እንዳይከፋቸው መንግሥት ሰሜን ለዘመተው መከላከያና ልዩ ኃይል ባስተባበረው መልክ በግፏአን ለተፈናቀሉትም ሁኔታዎችን ማመቻቸት ግድ ይለዋል። የትንሳኤ በአልን አዝነው እንደሌላው ቀን ከሚውሉ ቢያንስ የጾመ ሰውነታቸው ጾመ ልጓሙን እንዲፈታ ከስንዴ የተሻለ ነገር የሚያገኙበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው። የአዲስ አበባ አስተዳደር ለችግረኞች በሬ እየገዛ ሲያድል ከነበረው ተግባር በመማር ለተፈናቃዮቹም ተመሳሳይ እጅ ሊዘረጋ ይገባል። ከህዝብ ሀብት እየቆነጠሩ ለክልል መንግሥታትም ሆነ ለፈለጉት ግለሰብ በሚሊዮን ብር የሚለግሱ ባለስልጣናትም፣ የሀገር ሀብትን ብቻ ሳይሆን ከደሞዛቸውም እንደ ግድቡ እያዋጡ መስጠትን ሊለምዱ ይገባል።

ከወቅቱ ሁኔታ አንፃር ወረርሺኝ ከምርጫ ሂደት ጋር ተደራርበው የመጡበት እንደመሆኑ እርዳታ ለተፈናቀሉት ማድረሱ ብቻውን በቂ አይሆንም። ከተለያዩ አካባቢዎች እንዳይወጡ ታግተው ያሉት መፍትሄ እንዲያገኙ መጣር ያስፈልጋል። በመንግስት አካልም ሆነ በታጣቂዎች መተላለፊያ መንገድ እየተዘጋ ምርት ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋውር ማድረጉ መዘዙ ከፍተኛ ስለሚሆን አስቀድሞ ሊታሰብበት ግድ ይላል።

በሌላ በኩል፣ ሚሊዮኞች ተቸግረዋል ተብሎ እህል በብዛት የሚላክበት ትግራይ ክልል ልብ ያልተባ ጉዳይ አለ። በጦርነቱ ሳቢያ በርካቶች እንደሚፈናቀሉ የታወቀ ነው። አቅም ቢኖራቸው እንኳን የገበያ ስርአቱ ወደ ነበረበት በቶሎ ስለማይመለስ በርካቶች የሰው እጅ መጠበቃቸው የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን፣ ይህ እንዳለ ሆኖ በርካታ እህል ወደ ክልሉ እየተላከ አንዳንድ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችም ይሠማል። ከዚህ መካከል በቅርብ ቀናት ውስጥ ከትግራይ ክልል ተጭኖ በመጣ እህል ውስጥ የተደበቁ የጦር መሣሪያዎችተያዙ የሚል ዜና ነው። ሲዘዋወር ተያዘ የተባለው ከትግራይ ክልል ብዙ ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ደቡባዊ የወሎ ግዛት ውስጥ ነው። የሚገርመው በርካታ የእህል እጥረት አለበት ተብሎ ብዙ ሚሊዮን ኩንታል ከሚላክለት ክልል እህል ሲወጣ ደንበሩ ላይ ለምን ? ተብሎ አለመጠየቁ ነው። የጦር ቀጠና እንደመሆኑ ሁሉም የሚወጣና የሚገባ ክትትል ሊደረግበት ሲገባ እህል ተጭኖ መውጣቱ ያን ያህል መነጋገሪያ አልሆነም። ጦር መሳሪያ መገኘቱ እንጂ፣ እህሉ በክልሉ ተመርቶ ወደ ሌላ ለሽያጭ የሚውል ይሁን የእርዳታ እህል ተሸጦ የተባለ ነገር የለም። በተመሳሳይ ጎጃም ውስጥ በመጋዘን ተከማችቶ የነበረ የእርዳታ እህል በእሳት መጋየቱ ይታወሳል። ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉ ይሆናል ተብሎ የተቀመጠውን እህል ማን እንዳቃጠለው እስካሁን የተረጋገጠ መረጃ ከመንግሥት ይፋ ባይደረግም፣ ተፈናቃዮች ያሰሙት የነበረውን ስሞታ ያስተባበለ አካል ግን የለም ። “ከተረጂ ጉሮሮ ላይ ነጥቀው በህገ ወጥ መልክ እየሸጡት ነው” ብለው ሀዘናቸውን በመግለፃቸው የበላይ አካል መጥቶ እንደሚገመግም ተነግሮ ነበር። እንደ ወቅቱ ወሬ ከሆነ የመንግስት አካል ይመጣል ከመባሉ አስቀድመው የጎደለው እንዳይታወቅ የሸጡት አካላት አቃጠሉት መባሉ ብዙዎችን አሳዝኗል። ተረጂዎችን ክፏኛ የማሳዘኑን ያህል ባይሆንም ረጂዎችንም ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት ነበር። ይህ አይነት አሳፋሪ ተግባር በሌሎች አካባቢ አይፈፀምም ብሎ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል መንግሥት ተቆጣጣሪዎችን በየጊዜው በመመደብ የአካባቢውን ማህበረሰብ ስሞታን መቀበል አለበት። ህዝቡም ቢሆን የአስፈፃሚ አካላትን ተግባር በአይነ ቁራኛ በመከታተል እንዲያሳውቅ፤ የበላይ አካልም ትክክለኛ ሂደቶችን በመዘርዘር ወይም በአደባባይ በመለጠፍ ተገቢውን ከህገወጡ በቀላሉ ሊለዩየሚችሉበትን አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ብዙዎች ይናገራሉ።

መንግሥት አጥፊዎችን እያወቀ እንዳላወቀ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ማወቅ እየቻለ ለማወቅ አለመጣሩ እንዳለ ሆኖ ማስረጃ ሲቀርብለትም የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድም ሆነ ቅጣት ለመፈፀም ቁርጠኝነቱ እንደማይታይበት ይታመናል።“የአንደበት ቅድስና” በሚል መፀሐፍ ላይ የቀረበ ምሳሌ ይህን የመንግሥት ባህሪ ይገልፀዋል። አንዲት እናት መርፌ ጠፍቶባት ደጃፏን ስታስስ ጎረቤቷ ትደርሳለች። “ምን ጠፍቶሽ ነው?” ስትላት “መርፌ ናት” ብላ አብረው ፍለጋ ይገባሉ። ለበርካታ ደቂቃዎች ፍለጋው ከጦፈ በኋላ ተስፋ ወደመቁረጡ የተቃረበችው ጎረቤት፣“የቱ ጋር ነው የወደቀብሽ” ስትላት “የጠፋብኝስ እቤት ውስጥ ነው” ትላለች። ግራ የተጋባችው ጎረቤት፣“እና እዚህ ምን ታስሻለሽ” ስትላት “እቤት ብርሃን ስለሌለ ነው” ብላ መልሳላታለች። ሴትየዋ የጠፋባት ቦታ ለመፈለግ መብራት በመፈለግ ፈንታ የማታገኝበት ቦታ ብርሃኑ አለ ብላ መባከኗ ለጎረቤቷም ተርፏል። መንግስትም የችግር አምጪዎችን ማንነት እያወቀ እነሱን ፈልጎ ማግኘት ሳይሳነው በዚህ መልክ ህዝብን ጫካ ለጫካ ሲያሳድድ ከርሟል።

- ይከተሉን -Social Media

መፍትሄ ለማምጣት ቁርጠኝነት ከመንግስት ቢጠበቅም የሀገሪቱ ችግሮች የመወሳሰባቸውን ያህል ቅድሚያ ለሚሰጠው አትኩሮትን አስቀድሞ መስጠት ይጠበቅበታል። የዜጎች ደህንነት ለነገ የማይባል የሚደራደሩበት ባለመሆኑ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ የመኖር መብት ሊጠበቅ ይገባል። ህዝብ ተስፋ ከቆረጠ መልሶ ተስፋው እንዲለመልም ለማድረግ ስለማይቻል፤ ከተቻለም ከባድና ብዙ ነገር የሚጠይቅ በመሆኑ ከአሁኑ ሊታሰብበት ወደ ተግባርም ሊገባ ይገባል። ሁሉም ክልል ማለት ይቻላልየሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ያፈናቀለ ወይም ያስተናገደ ነው። ይህ በዚሁ ካልቆመ ያልተፈናቀለውም ላይ ከፍተኛ ስጋት ስለሚፈጥር እንደሀገር መሻሻል ቀርቶ ቁልቁል ለመምዘግዘጋችን ማቆሚያአይኖርም። ኢትዮጵያ የአማኞች ሀገር እንደመሆኗ ቢያንስ ይህ ሰሞን ክርስቲያኖች የጾም ጊዜያቸውን አጠናቀው የትንሳኤ በአልን የሚያከብሩበት፤ የእስልምና እምነት ተከታዩችም ጾሙን አጋምሰው የኢድ አልፈጥር በአልን የሚጠብቁበት ጊዜ እንደመሆኑ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል። በረመዳን ጾም ወቅት በየድንኳኑና መጋዘን ታጭቀው የሚገኙ ተፈናቃዮች ከእኛ ሌላ የሚደርስላቸው ስለሌለ ከሁላችንም የሚጠበቅብንን ማድረግ እንዳለብን እርዳታ አስተባባሪዎች ይናገራሉ። የመንግሥት ግዴታ የመሆኑን ያህል፣ ህዝቡም ነግ በኔ ነውና ተጋግዞ መረዳዳቱ የኃይማኖትም ሆነ የህሊና ግዴታው ነው። ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሌለበት አለም ሠርተንም ሆነ እድለኛ ሆነን ካከማቸነው ማካፈል ይጠበቅብናል። “በአሉን በሀዘን ልናሳልፍ ነው” ያሉን ተፈናቃዮችን ማስደሰት ባንችልም፣ ሰቆቃቸውን ለመቀነስ የአቅማችንን እንድናደርግ አዲስ ማለዳም ጥሪ ታቀርባለች። በየቤታችሁ እያስተናገዳችሁ ያላችሁ የምትሰሩት በጎ ተግባር እንደመሆኑ፣ በዘላቂነት ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ከሌሎች ጋር በመመካከር ልትተገብሩት ይገባል።

መንግሥት በተፈናቃዮች ዙሪያ ያለውን ችግር ሳይፈታ ሌሎች እንዳይጨመሩ እስካሁን የሄደበት መንገድ እንዳላዋጣ ገምግሞ የተሻለ አማራጭ ቢወስድ መልካም ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን፣ ቅድሚያ የሚሠጣቸውን ጉዳዮች በመለየት ኃላፊነቱንም በመከፋፈል ሁሉም በዘመቻ መልክ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲሠራ መደረግ አለበት። ግድ የውጭጠላት ፊት ለፊት እስኪመጣ ተጠብቆ አንድ ለመሆን ከመቀስቀስ ውስጣችን ያለውን ጉድፍ በማጽዳት ችግሩ የት እንዳለ ለይቶ መቅረፍ ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው የችግሩ ተጠቂዎችን በመጠየቅ፣ የአጥፊዎችን ማንነት በመለየትና ማስቆም የሚችሉበትን አማራጭ በመፈለግ ነው። በዚህ ጉዳይ በመሰባሰብ የባለሙያዎችን ምክር መስማትም ግድ ይላል። እንደ ሀገር እድገት እየተባለ መውደቅ፤ ራስን ለመቻል እየተባለ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ ቅድሚያ ህዝቡ ራሱን ችሎ ሊኖር የሚያስችለው ሁኔታ መፈጠር አለበት። ሀብት ያለው የፈለገበት ሄዶ መኖር የመቻሉን ያህል አቅም የሌለው ድሃ በፈለገበት የመኖር መብቱ ሊነፈግ አይገባም። ሰርቼ ልኑር የሚልን ሠርቶ እንዲኖር ጥበቃ ማድረግ እንጂ፣ እርዳታ ማከፋፈሉ ስለማያዛልቅ የችግሩን ምንጭ ሳይሰወር ማድረቁ ጊዜ የሚሠጠው መሆን የለበትም። ወቅቱ በአላት የተደራረቡበት የምርጫ መንደርደሪያ እንደመሆኑም፣ ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ሆነው የተፈናቀሉበትን አካባቢ ተወካይ መምረጥ የሚችሉበት ሁኔታዎች በምርጫ ቦርድ ሊዘጋጅ ይገባል። የኃይማኖት አባቶችም የታመመንና የታሰረን ጠይቁ ድሃን እርዱ እንደሚሉትየተፈናቀሉትም በበአላት ወቅት እንዲታሰቡ መልዕክታቸውን አጠናክረው ቢያስተላልፏ መልካም ይሆናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች