ለጉምቱው ምሁር የመታሰቢያ ፋውንዴሽን እየተመሰረተ ነው

0
766

በቅርቡ ሕይወታቸውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ላጡት ጉምቱው የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የመታሰቢያ ፋውንዴሽን በቤተሰቦቻቸው እና በወዳጅ ዘመዶቻቸው እየተቋቋመ ሲሆን፣ በድሉ ዋቅጂራ (ዶክተር) የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሊቀመንበር መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ እውቅና በማግኘት ሂደት ላይ እንዳለም ከቦርድ አባላቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ፋውንዴሽን ለመመስረት የሚያስፈልገው 100 ሺሕ ብር ከፕሮፌሰሩ ወዳጅ ዘመዶች እንደተገኘም ታውቋል። ልጃቸው ዶክተር መቅደስ መስፍንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ አባላት ጭምር የቦርድ አባል እንደሆኑና ከአገር ውጭ የሚኖሩ ሰዎችም በቦርድ አባልነት እንደተመረጡ ታውቋል።

ፋውንዴሽኑ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሥም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ እስካሁን የሠሩትን ሥራ ለማሰባሰብ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለመዘከር ዓላማ ይውላል። ይህ ፋውንዴሽንን ለመመስረት ማሟላት ያለባቸውትን ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ አሟልቶ የምዝገባ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ እና በአገር ውስጥ ያሉ የቦርድ አባላት በውጭ አገር ከሚገኙት ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ስብሰባዎቻቸውን እንደሚያካሂዱም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ለአንድ ሰው መታሰቢያ ፋውንሽን ሲቋቋም በዝግ አካውንት መቀመጥ ያለበት 100 ሺሕ ብር እንደተቀመጠ እና የማህበሩ ዓላማ ምን እንደሆነ የሚገልጽ በዝርዝር የተቀመጠ መተዳደሪያ ደምብ፣ የአባላት እና የቦርድ አመራር ስም ዝርዝር ተያይዞ ለኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ ቀርቦ የእውቅና ፈቃድ የመውሰድ ሂደት ላይ እንዳለም የቦርድ አባላቱ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን ለማንፀባረቅ ችላ የማይሉ፣ ዕውቀታቸውንና መልእክታቸውን በአደባባይ ለማስተጋባት ይተጉ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም። “ነፃ ሐሳብ ለነፃ ሕዝብ” የሚል አስተምህሮ የነበራቸው ሲሆን ያንንም ለመተግበር፣ ዕውንም ለማድረግ ወደ ኋላ ማለትና ማፈግፈግን ዞር በል የሚሉ ናቸው ይሏቸዋል። ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ከሦስት አሥርት አመታት በፊት ኢሰመጉን በመመሥረት ያሳዩት ተምሳሌትነት ይሁንታን አስገኝቶላቸዋል።

ከዘውዳዊው ሥርዓት እስከ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ ከሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊኩ እስከ አሁን ዘመኑ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥታት ድረስ የሽግግር ዘመኑንም ጨምሮ ገዥ መንግስታትን በገሀድ በመሔስ፣ የሚሰማቸውን በመጣጥፍና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በመግለጽ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በተለይ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ሲጨብጥ በሽግግሩ ዘመን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከወቅቱ የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ ጋር ክርክር የገጠሙበት መንገድም (ሌሎች ምሁራን ጨምሮ) በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል።

ካዘጋጇቸው እና ለኅትመት ከበቁት ሥራዎቻቸው መካከል ኢትዮጵያ ከየት ወዴት፤ አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ፤ሥልጣን፣ ባሕልና አገዛዝ፤ ፖሊቲካና ምርጫ፤ የክህደት ቁልቁለት፤ አገቱኒ፣ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ፤ አድማጭ ያጣ ጩኸት፤ እንዘጭ! እንቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ፤ አዳፍኔ፣ ፍርሃትና መክሸፍ፤ ዛሬም እንደ ትናንትና ተጠቃሽ ናቸው።

ሚያዝያ 15 ቀን 1922 በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በልጅነታቸው ዘመን በ1937 ለድቁና ያበቃቸውን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርት ተከታትለዋል። በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ህንድ አገር በማቅናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ ከሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማገልገል ከመጀመራቸው በፊት በካርታና ጂኦግራፊ ኢንስቲትዩት ውስጥ ሠርተዋል።

ባደረባቸው የኮቪድ ሕመም ሳቢያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ፕሮፌሰር መስፍን ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 2013 በ90 ዓመታቸው ማረፋቸው ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here