አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ግድያና መፈናቀል እንዲሁም ጦርነት ምርጫውን ሊያደናቅፈው እንደሚችል በመገመት ምርጫው ይተላለፍ እያሉ ነው። በወለጋ፣ በመተከል፣ በአጣዬ፣ በቀወት፣ በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች፣ በአማሮ ኬሌ እና በሌሎችም ቦታዎች ያሉት ሰብዓዊ ቀውሶችና በትግራይ ክልል ያለው ጦርነት እልባት ሳያገኝ ምርጫ መደረግ የለበትም የሚሉ ወገኖች አሉ።
በሌላ ወገን ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ያለችም ቢሆን ምርጫው መደረግ አለበት የሚሉ ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትርና የምርጫ ጉዳይ ደህንነትና ጸጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ ምርጫ በሽግግር ሂደት ውስጥ የሚካሄድ በመሆኑ አንዳንድ የጸጥታ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ መግለጻቸው ይታወሳል። የመንግሥት አጠቃላይ ግምገማ ከአገሪቱ ስፋትና የምርጫ ሰፊ ዝግጅት አንጻር የጸጥታ ችግር የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ተጽዕኖ የከፋ እንደማይሆን እንደሚያመለክትም ገዱ ገልጸዋል።
የሕግ ባለሙያው ውብሸት ሙላት ለአል ዐይን አማርኛ በሰጡት አስተያየት ፣ ከትግራይ ክልል በተጨማሪ “ምርጫ የማይደረግባቸው ሌሎችም አካባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ” ገልጸው ፣ ይህ ሁኔታ አገሪቱ በጸጥታ ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንዳለች በራሱ ምስክር እንደሆነ ያነሳሉ። አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ችግር እስከ ምርጫው ቀን ድረስ ሊባባስ ወይም ሊሻሻል እንደሚችል ያነሱት አቶ ውብሸት ፣ በምርጫው ላይ በትክክል ሊፎካከሩ የሚችሉ ፓርቲዎች መኖር አለመኖራቸውን በሚመለከትም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ ግልጽ ነው ይላሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013



