የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም የህይወት አድንና መሰረታዊ መድኃኒቶች አቅርቦት 81 በመቶ፣ የመሰረታዊ መድኃኒቶች አቅርቦት ደግሞ 65 በመቶ እንደነበር፣ እንዲሁም ከ13 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒቶችን እንዳሠራጨ አሳታውቋል፡፡
ኤጀንሲው የጤና ተቋማትን ፍላጎት ለማሟላት ባሳለፍነው 9 ወራት 11 ቢሊዮን 173 ሚሊየን 412 ሺሕ 78 ብር የሚያወጡ የመደበኛና የፕሮግራም መድኃኒቶችን ገዝቶ ማቅረቡን የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ ተናግረዋል፡፡
በኤጀንሲው ግዥ በመድኃኒት ማከማቻ መጋዘን ከነበረውና በበጀት ዓመቱ ግዥ ከፈፀመው መድኃኒት በ14 ቢሊዮን 259 ሚሊየን 360 ሺሕ 471 ብር መድኃኒቶችን ለማሰራጨት አቅዶ 13 ቢሊዮን 4 ሚሊዮን 680 ሺሕ 689 ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች መሰራጨታቸው ተገልጿል።
ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን የጤና ተቋማትን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ስላላሟለን፣ አቅርቦት አና ፍላጎት እስከሚጣጣም ድረስ ጠንክረን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
የኮቪድ 19 በሽታን ለመግታትና ለመቆጣጠር 1 ቢሊዮን 743 ሚሊዮን 754 ሺሕ 302 ብር ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያዎችን በማሰራጨት ኤጀንሲው ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013


