‹‹የምርጫ ቅስቀሳዎችን ስናደርግ በገዢው ፓርቲ የሚፈጸም አሻጥር አለ›› ሀብታሙ ኪታባ የኢዜማ እጩ ተወዳዳሪ

0
540

ሀብታሙ ኪታባ ይባላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ን ወክለው ለአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት ምርጫ የወረዳ 12/13 እጩ ተወዳደሪ ናቸው፡፡ የኢዜማ የስልጠና እና አቅም ግንባታ ኮሚቴንም ይመራሉ፡፡

ምርጫው መራዘሙ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ምርጫውን የሚያስተባብረው ምርጫ ቦርድ ነው። ተቋሙ ከፓርቲዎች ጋር እየተመካከረ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች አሉ። ከዚህ አንጻር ለሁለት ሳምንት ለመራዘም የቀረቡት ምክንያቶች በቂ ናቸው ብዬ አስባለው። ከዚህ በላይ ባይራዘም ጥሩ ይሆናል።

የተራዘመው ጊዜ ይበቃል ብላችሁ ታስባላችሁ? ከዚህ በኋላስ የሚራዘም ይመስላችኋል?
ከዚህ በኋላ የሚራዘም አይመስለኝም። የጸጥታ ችግር ያለባቸውንና ቅሬታ እየቀረባበቸው ያሉ እንደ ሱማሌ ክልልን በመሳሰሉ አካባቢዎች ምርጫ እንደሚከናወን ተገልጿል። ስለዚህ እኛም ተቀብለነዋል። ሌሎቹ ቦታዎች ላይ በተባለው ጊዜ እናጠናቅቃለን የሚል እምነት ስላላቸው ይመስለኛል በዚህ መንገድ የሄዱት። በመሆኑም ከሁለት ሳምንት በላይ ይራዘማል ብለን አንጠብቅም። በተባሉት ቦታዎች ላይ በተባለው ቀን እንደሚደረግ እንጠብቃለን።

በተራዘሙት 15 ቀናት ውስጥ ችግሮቹ ይፈታሉ ብላችሁ ታስባላችሁ ?
አሁን ላይ ምርጫውን ለማራዘም ምክንያት የሆኑት ቦታዎች ላይ አይደረገም። ለምሳሌ፣ የኛን መዋቅር ስንመለከት ሱማሌ ክልል ላይ ቅሬታ ያቀረብንባቸው እየተመረመሩ እንዲስተካከሉ እያደረግን ነው። ስለዚህ እነዚህን ቦታዎች በመተው ሌሎቹ ጋር ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ። ችግሮቹ ሙሉ ለሙሉ ይፈታሉ የሚለው እነዚህንም ሲጨምር ነው። እነዚህ ክልሎች የሀገራችን አንድ ክፍል ናቸው። ስለዚህ እዛ አካባቢ የሚደረገው ምርጫ ከዚህ ጋር ስለማይገናኝ የነሱ ችግር ባይፈታም ሌሎች ቦታዎች ጋር ይደረጋል ብዬ አስባለው።

ቅስቀሳን በተመለከተ እስከ አሁን የነበረውን ሂደት እንዴት ይመለከቱታል?
ቅስቀሳን በተመለከተ ኹለት ነገሮች ናቸው ያሉት። የመጀመሪያው በፓርቲ ውስጣዊ ጥንካሬ ምክንያት ቅስቀሳውን በሚገባው መጠን ያለመጠቀም ነገር አለ። ለምሳሌ፣ በጋዜጣ፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተሰጠ ሰዓትን በአግባቡ መጠቀም ያለመቻል አንዱ የፓርቲዎች ውስጣዊ ድክመትን የሚያሳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ሚዲያዎች ሁኔታዎችን አመቻችተው ፓርቲዎችን ቢጠይቁ ለቀጣይ ትምህርት የሚሆን ነገር ይኖራል ብዬ አስባለው። አንድ ፓርቲ ሊኖረው የሚገባውን ጥንካሬ ለማግኘት አባላቶቹ ፓርቲውን እስከምን ድረስ ማጠንከር እንዳባቸው ትምህርት ይወሰድበታል።

የምርጫ ቦርድ የሚለቀው ገንዘብ መዘግየትም በአግባቡ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የያዛቸው ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል። ኢዜማዎች የምርጫ ቦርድ ገንዘብም ሳይመጣ ቅስቀሳዎችን እያደረግን እንገኛለን። ስለዚህ ከቅስቀሳ ጋር በተያያዘ የፓርቲዎችን የውስጥ አቅም የሚያሳይ ሆኖ አየዋለው።

ሁለተኛው ውጫዊ ተጽእኖ ነው። በተለይ ከገዢው ፓርቲ የሚመጣው ውጫዊ ተጽዕኖ በጉልህ የሚታይባቸው ቦታዎች አሉ። እነዚህ ቦታዎች ላይ ምርጫ ቦርድ አሁን ባለው አስተዳደራዊ ቁመናና ልምድ ማነስ፣ እነሱን የመቆጣጠር አቅም ላይ ያልደረሰባቸው ሁኔታዎች አሉ። ገዢው ፓርቲ በሚችለው መንገድ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችልባቸው ቦታዎች ላይ ማድረግ የሚችለውን እያደረገ ነው ያለው። ይህ ማለት ያልተገባ የምርጫ ውድድር አካሄድ እያከናወኑ ነው ያሉት። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች እንደ ሀገር ስናስብ በቀጣይ ከነሱ ምን እንማራለን የሚለውን ማየት ይኖርብናል ብዬ አስባለው። በመሰረታዊ ደረጃ ግን የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ መዳከም አለ።

ገዢው ፓርቲ ከሚፈጥራቸው ተጽዕኖዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ላይ የሚታዩ ግልጽ ተጽዕኖዎች አሉ። ይህ ደግሞ ከፓርቲው ድክመት ብቻም ሳይሆን ከምርጫ ቦርድና ከገዢው ፓርቲ የሚመጡ ስለሆነ የስጋቱ ውጤት ናቸው። የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ አካሎች ደሞዛቸውንና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው የገዢው ፓርቲ ስለሆነ እነሱ ውድድር ነው የያዙት። ሁሉንም ክልል ለመቆጣጠር ካላቸው ፍላጎት አንጻር፣ ሚዲያ በሌለባቸውና የማኅበረሰቡ ንቃት ከፍተኛ ባልሆነባቸው በተለይ ወደ ገጠር አካባቢ እንደዚህ አይነት መንገዶችን የመከተል ምልክቶችን እናያለን። ስለዚህ እንደ ሀገር ትግል ይዘናል ምርጫ ቅስቀሳው በዚህ ይገለጻል ብዬ አስባለው።

ተጽዕኖ ብለው ከገለፁት መካከል የተወሰኑትን ቢጠቅሱልን?
ተጽዕኖ ከምንላቸው መካከል የሩቁን ትተን የቅርብ ጊዜውን ማንሳት እንችላለን። ለምሳሌ፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች በባህሪያቸው የተለያየ ብሔር የያዙ ናቸው። ምንም እንኳን ኦሮሚያ ክልል ቢሆኑም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን እያስተናገዱ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል። እንደ ኢዜማ እነዚህ ቦታዎች ላይ በምንፈልገው መንገድ መንቀሳቀስ አልቻልንም። ለዚህም እንቅስቃሴ መገታት ምክንያት የሆነው የኛ የአቅም ጉዳይ ሳይሆን አስተዳደሮቹ የፈጠሩት ፍርሃት ነው። ለምሳሌ ቢሾፍቱ የሚገኝ አንድ ሆቴል የፍርሃት ድባብ ስላለባቸው ማከራየት አልፈለጉም ነበር። ሆቴል ለመከራየት በምንጠይቅበት ሰዓትም ቢሆን የሚሰጡን ምላሽ፣ “እዚህ እጩ የላችሁም እና አናውቃችሁም፤ ከምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ካልደረሰን አናስተናግድም” በማለት አስተዳደራዊ ሂደቱን የማዳከም ሁኔታዎች አሉ። ቅስቀሳዎችን ለማድረግ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ያለንን ጊዜ እየተሻማን ባለንበት በዚህ ወቅት እንደነዚህ ያሉ አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን በማምጣት ጊዜያችንን እንዳንጠቀም የማድረግ ሁኔታ አለ።

ከዚህ በተጨማሪም እጩዎቻችንን የማስፈራራት ሁኔታ አለ። ስለዚህ እንደ ኢዜማ ትልቁን ምስል እያየን ስለምንሄድ በየቦታው የሚፈጸሙትን ጉዳቶች ወደ ሚዲያ ይዘን ስለማንወጣ በመሃል አሻጥሮች እየተፈጸሙብን ነው። ለምሳሌ፣ እኔ የምኖርበት ግቢ ውስጥ አንድ ለአስር ብለው እየዞሩ ሁሉንም ተከራዮች ቅጽ እያስሞሉ ነበር። ለምን እንደሚመዘግቧቸው አይነግሯቸውም። ነገር ግን እኛ ስንመለከተው ‹‹የብልጽግና ቤተሰባዊ ትስስር ቅጽ›› የሚል ነው። ይህን ስል እኛ አካባቢ ያለ ሰው በሙሉ ኢዜማን ይደግፍ ማለቴ አይደለም። ይህ ተግባር ገዢው አካል ከወረዳ ነው የመጣነው በማለት የሚያደርገው ሴራ ነው። ያላቸውን አመራርነት በመጠቀም የበላይ ለመሆን ሲጥሩ ይታያሉ። በእጃቸው ያለውን መዋቅር የመጠቀም ሁኔታ ይታያል። እኔ በግሌ ከተመለከትኩት ሌላው ጉዳይ ደግሞ አንድ ክፍለ ከተማ ቅጥር ግቢ ውስጥ ብልጽግና ሲቀሰቅስ ታይቶ ነበር። የቀበሌ ቤቶችን የማስተላለፍ ፕሮግራም ላይ ብልጽግና ነበር። በተጨማሪም ፈረንሳይ አካባቢ ቅስቀሳ ሲደረግ በኮድ አራት (ባለቤትነቱ የመንግስት የሆነ) መኪና ሲጠቀም ነበር። እነዚህ ነገሮች ፍትሀዊ የሆነ የውድድር ሜዳ እንዳይኖር ያደርጋሉ። የመንግሥት መዋቅርን በሙሉ ብልጽግና እንደፈለገ እየተጠቀመ ነው።

የክርክር መድረኮችን እንዴት እየተጠቀማችሁ ነው?
በመጀመሪያ በክርክሩ ቦታዎች ላይ ክርክር ይዘው የሚቀርቡ የፓርቲ ተወካዮች ሀሳባቸውን የመሸጥ መርህ መከተል ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ አንዳንድ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን ማኒፌስቶዎቻቸው ላይ አስቀምጠዋል። እነዚህ ማኒፌስቶዎች እያንዳንዱ ቤት ጓዳ መድረስ አይችሉም ። ስለዚህ ያለው አማራጭ በክርከር ያንን ሀሳብ ማድረስ ነው። ክርክር ማለት ሀሳብን ማድረስ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ነው። አንድ ፓርቲ ሃሳቡን በባነር፣ በማኒፌስቶ እና በሚዲያ ማቅረብ ይችላል። ሕዝቡ የሁለት ወገኖችን ክርክር ሰምቶ ለመለየት የሚያስችለው ደግሞ እንዲህ ባሉ የክርክር መንገዶች ነው። ከዚህ የክርክር መድረክ መሸሽ ትርጉሙ ተቃራኒ ሀሳብ በሌለበት ቦታ ላይ የሚጋት ሀሳብ አለኝ እና ዝም ብዬ እሰጥሃለው እንደማለት ነው። ይህንን ደግሞ ብልጽግና የሚከተለው አንዱ መንገድ ነው። እስከ አሁን ድረስ ሕዝብ ባለበት አዳራሽ ፈቃደኛ አልነበረም። ይህንን ጉዳይ ሕዝቡ ትኩረት ሰጥቶት አላየውም። እኛ ስንናገር ደግሞ የፖለቲካ ትርፍ ፈልገን እንደሆነ ይታሰባል። ነገር ግን ወደፊት ጉዳቱ በግልጽ ታይቶ እንደ ሀገር ሀሳብን የማፈን ነጸብራቅ መሆኑ አይቀርም።

ክርክሩ ላይ የማየው መሰረታዊ ችግር ሀሳቦችን ለማንሸራሸር ቁርጠኛ ያለመሆን ሁኔታ ነው። የኢኮኖሚ አሶሴሽን ያቀረበው የክርክር ፎርማት ሕዝብ ባለበት ቦታ ላከራክራችሁ የሚል ቢሆንም እንደዚህ አይነት ክርክር እንደማይፈልግ የገለጸው ብልጽግና ነው። ከዛ በኋላም ቢሆን በተለያዩ ሚዲያዎች ለመቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በመጨረሻ የመንግሥትና የፓርቲው አሻራ ያላቸውን ሚዲያዎች የመጠቀም ፍላጎቱን አሳይቷል። እነዚህ ሚዲያዎች ጋርም ቢሆን ክርክሩ ከተደረገ በኋላ ቆይቶ የማቅረብ ሁኔታ ነበር። በዚህ መሀል የክርክሩን ጭብጥ የሚነኩ ፕሮግራሞች፣ ዶክመንተሪዎችን እና ኢንተርቪዎችን ይሰጣሉ። ቀድመው ህዝብን ሲያዘጋጁ ይቆዩና ክርክሩን የማስተላለፍ ሁኔታ አለ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለት ነገሮች ይታዩኛል። አንደኛው በክርክሩ ላይ የፓርቲዎች ቁመና ችግር አለበት። ለምሳሌ፣ መንግስት ብንሆን ይህን እናደርጋለን የሚሉ ግን ለመንግስት የሚሆን እጩ ያላቀረቡ በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለክርክር መቅረብ አልነበረባቸውም ብዬ አስባለው። ተከራክረው መንግሥት መሆን የሚችሉ ሀሳባቸውን ማቅረብ አለባቸው ብዬ አስባለው። ቢመረጡ መንግሥት ለመሆን የሚያስችል አቅም ከሌላቸው አይ እኛ ይቅርብን ብሎ መተው ይገባቸው ነበር። ሁለተኛው ገዢው ፓርቲ ጋ ያየሁት ችግር የክርክር ፎርማቶችን በሚፈልጋቸው መንገድ የመቀልበስ፣ አንዳንድ የክርክር መድረኮች ላይ የመቅረት እና ህዝብ ባለበት ቦታዎች ላይ የሞቀ የክርክር ድባብ እንዳይፈጠር የመፈለግና በተለያዩ ስሜት ተኮር በሆኑ መንገዶች የህዝብን ልብ ይዞ ምርጫውን ለመጨረስ የመፈለግ ሁኔታዎች አሉ።

ሰሞኑን ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎች ለማሳረፍ እየሞከሩ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
በዚህ ጉዳይ ሦስት ነገሮችን ማንሳት እፈልጋለው። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እየተካሄደ ነው። ይህንን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ የለውጥ ሂደቶች በምታከናውንባቸው በየትኛውም ዘመኖች የውጭ ሀይሎች ፍላጎታቸውን ለማንጸባረቅ ይሰሩ ነበር። ስለዚህ ዛሬም ቢሰሩ ሊገርመን አይገባም። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ የሚባል ነገር በሚመጣበት ጊዜ የዓለም አቀፍ ፖለቲካውን ሚዛን ለማስጠበቅ የሚፈልጉ የትኞቹም ኃይሎች አገር ውስጥ የሚካሄደው ለውጥ ጋር የራሳቸውን ቦታ የመፈለግ ነገር አለ።

ኹለተኛው የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ነው። ግድቡ በዓለም ሰባተኛው ግድብ እንደሚሆን ይታየኛል። ስለዚህ ለውጥም ሆነ ምርጫም ባይኖር ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ እና በዓለም ላይ ያለው ትርጉም ትልቅ ስለሆነ ጫና ይበዛበታል። ከዚህ ፕሮጀክት አንጻር የሚመጣው ተጽእኖ ከባድ ነው። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ያላትን የኃይል ሚዛን እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ ላይ ያለውን የኃይል ሚዛን ጨመረላት ማለት ከግብጽ የኃይል ሚዛኑን ወሰደች ወይም ተጋፋች ማለት ነው። በተጨማሪም በአሜሪካ በኩል ሲታሰብ ከኢትዮጵያና ከግብጽ መካከል ለግብጽ የማዳላት ነገር በተለይ ምዕራባውያን ላይ ይታያል። ሦስተኛው ከምርጫ ጋር በተገናኘ የሚነሳው ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያውያን ወደድንም ጠላንም ሀገራችን የሚያኮራ ታሪክ ያላት፣ ቅኝ ያልተገዛች፣ እምነቷንና ባህሏን የጠበቀች ሀገር በመሆኗ ልንኮራ ይገባናል።

ኢትዮጵያ በድህነት ውስጥ ብትሆንም ጠንካራ አቅም ያላት አገር ነች። ከዓለም አቀፍ ድጋፍ ጥገኝነት ተላቀቀች ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው። ስለዚህ ይህ ምርጫ ተከትሎ የሚመጣው የሕገ-መንግስት ማሻሻል፣ ብሔራዊ መግባባት እና የተረጋጋ አገር መፍጠር ከተቻለ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ያላትን የጦርነት ታሪክ በዲሞክራሲ የምትቀይር ከሆነ በእነዚህ ድምር ውጤቶች ኢትዮጵያ ኃያል መሆን ትችላለች። ምዕራባውያን አፍሪካውያንን በሙሉ ባለንበት እንድንቀጥል ነው የሚፈልጉት። ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ምርጫ የሚመጣው ለውጥ ወደተሻለ የሀገር ቁመና ሲያመጣ፣ እነሱ የተዳከመች እና በእነሱ ላይ ጥገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያ ያሳጣናል የሚል እምነት አላቸው። የትግራይ ህዝብ ከጦርነቱ በኋላ የደረሰበትን ጉዳት በመረዳት እንዲያገግም ማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሥራ ነው መሆን ያለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ መፈናቀል እና የፖለቲካ ሽኩቻ እየበረደ መሄድ አለበት። ይህ ደግሞ የኛ የሀገር ውስጥ የቤት ስራ ነው። አውሮፓውያኖቹ ችግሮቹን መፍታት ሳይሆን በማባባስ በልጠው መገኘት ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ የያዘቸው መንገድ የተዋጠላቸው አይመስለኝም። ለመቀሌም ሆነ ለወለጋ ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ የበለጠ ችግሮቻቸውን ቀርቦ ለመረዳት ኢትዮጵያ እንደምትሻል ይታወቃል። በመሆኑም አገር ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት እንችላለን።

በአጠቃላይ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሀዊ ይሆናል ብላችሁ ታምናላችሁ?
የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት የሕዝብ አስተዋጽኦ ነው። ሕዝቡ በየቦታው ይህ ስርዓት ያስፈልገኛል የሚል እምነት ላይ እየደረሰ ሲመጣ ነው ዲሞክራሲ እየጎለበተ የሚመጣው። ምርጫው በየቦታው እንከን ሊኖሩት ይችላሉ። ነገር ግን መገንዘብ ያለብን እነዚህ ሦስት ባለድርሻ አካላት ማለትም ሕዝብ፣ ምርጫ ቦርድ እና መንግሥት ፍትሃዊ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው።
ከመንግሥት በኩል በሚችለው መንገድ ምርጫ ለማድረግ ይሞክራል። የምርጫው ፍትሀዊነትን በአንድ አካል ላይ የምንደመድመው አይደለም።

በሕዝብ በኩል ደግሞ ፍትሀዊ የሚያደርገው ምርጫ ቦርድና መንግሥት የሚያደርጉት ድምር ውጤት ነው። በግሌ ግን የመንግሥት መዋቅሮች ላይ እምነት የለኝም። ምርጫ ቦርድ እና የሚታዘቡ ሕዝብ ላይ ግን እምነት አለኝ። አሁን ባለው ምርጫ ቦርድ እንደ ምርጫ 97 የኮሮጆ መጭበርበር የሚፈጠር አይመስለኝም።

ማጭበርበር ቢያጋጥም እንኳን ምርጫ ቦርድ ዝም ብሎ የሰጡትን ይቀበላል ብዬ አላስብም። ያሉት ኃላፊዎች ፍጹም ናቸው ባንልም፣ መነሻ የሚሆን የህዝብ ተወካዮችን ወንበር ትርጉም ባለው ሁኔታ ሊቀይር የሚችል ምርጫ ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ።

ፓርቲዎች ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ ናችሁ ወይ?
ሽንፈት መቀበል የሚቻለው የምታሸንፍ ሲሆን ነው። አንዳንድ ፓርቲዎች ከ20 እስከ 50 ወንበር ለመያዝ ነው የሚወዳደሩት። በዚህ ወንበር ብቻ ሀገር መምራት አይችሉም። በእኛ በኩል ምርጫውን በተመለከተ ዝግጁ ነን። ታዛቢዎች አዘጋጅተናል። ለእያንዳንዱ የምርጫ ወረዳ ጣቢያ ላይ የሚካሄዱትን እና ከፍርድ ቤቶች ለምርጫ ቦርድ መቅረብ የሚገባቸውን ጉዳዮች እያስተካከልን እየሄድን ነው።
የምርጫውን ውጤት የመቀበል ችግር የለብንም። ሌሎች ፓርቲዎችም በዚህ መንገድ ማለትም ተቋሞቹ ገለልተኛ ናቸው ብለው ካመኑ፣ በምርጫ ቆጠራ ወቅትም እምነት ካላቸው ይህን ተከትሎ የሚመጣው ጉዳይ ማሸነፍ እና መሸነፍ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ከአሁኑ ያልተደራጀ ፓርቲ ከምርጫ በኋላ ሀገር ይመራል ማለት ከባድ ነው።

ኢዜማን ከሌሎች ፓርቲዎች ምን ይለየዋል ?
ፓርቲያችን የሚለየው ዋነኛ ነገር የመንግሥት እና የፓርቲ መዋቅርን መለየት የቻለ የመጀመሪያው ፓርቲ መሆኑ ነው። ለምሳሌ፣ የሺዋስ አሰፋ የፓርቲው ሊቀመንበር ስለሆነ ለምርጫ አይወዳደርም ። ምክንያቱም የመሪ አቅጣጫ ያለው ክፍል ነው እንጂ የሚወዳደረው የድርጅቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች አይወዳደሩም። ፓርቲው ስልጣን ባይዝ የፓርቲውን ሥራ ይዘው የሚሄዱ ሰዎች አሉ። ይህ በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ምርጫ ወረዳ አለ።

ኹለተኛ እጩዎች ሲመረጡ በበጎ ፍቃድ ሳይሆን በዲሞክራሲ ምርጫ ነው። አባላት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡ ይደረጋል። የምርጫ ወረዳ አባል ውስጥ የአስመራጭ ኮሚቴ ዳኞች ተቀምጠው፣ የተመራጭ ኮሚቴዎችን ማስረጃዎች ተቀብለው አወዳድረው ቅሬታ ካለ ታይቶ ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ እጩዎችን ይመርጣሉ።

ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ መቅረጫ ቤት መሆን አለባቸው በሚል የኢትዮጵያ ፖለቲካን እንዲለወጥ አድርገናል። አንድ ፓርቲ ስለፖሊሲ ሲያወራ በበጎ መንገድ መውሰድ አለበት ብዬ አስባለው። ሌላው ለየት የሚያደረግን በማኀበረሰባችን የተገለሉ አካል ጉዳተኞችን አካታች ለማድረግ የታሰቡ ስራዎች አሉ። እነዚህ አካላት ለማካተት አባል የማድረግና ፕሮግራሞች እንዲቀርጹ እድል በመስጠት ስራዎችን ሰርተናል። ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከብሔር ወደ እምነት ግጭት እየተገላበጠች ያለች አገር ናት። ኢዜማ ሁሉንም የሚያከብር ስለሆነ የሁሉንም እምነት፣ ብሔር እና ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ፓርቲ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here