በአዲስ አበባ ዙሪያ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች መካሄድ ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ የሚካሄዱት ሕገ-ወጥ ተግባራት ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ ከሚኖሩ ግለሰቦች ጀምሮ እስከ ትልልቅ ባለሃብቶች የሚሳተፉበት፣ ብሎም የፖለቲካ ዓላማ ያነገቡ አካላት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የሚያከናወኑት የወረራ ተግባር ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ የሚገኘው የመሬት ወረራ ደግሞ አድማሱን በክልል አስተዳደሮች ደረጃ በማሳደግ፣ በልማት እና በኢንቨስትመንት ስም የአዲስ አበባን መሬት መሻማት የሰርክ ተግባር መሆን ጀምሯል፡፡ አዲስ አበባ መሬት ላይ የሚታየው የመሬት ሽሚያ እስከ ክልል አስተዳደሮች ማደጉን በተመለከተ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማነጋገር ሰላማዊት መንገሻ በሀተታ ዘ-ማለዳ ተመልክታዋለች፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄዱ የመሬት ሽሚያዎች በግልጽ እየተስተዋሉ መጥተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን አሁን አዲስ አበባ ላይ በልማት ስም በከተማ አስተዳደር ደረጃ መሬቶች እና የተገነቡ ህንጻዎችን በስፋት መሻማት የተለመደ ተግባር ሁኖ ይገኛል፡፡ በቀደሙት ኹለት ዓመታት ውስጥ ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ሲነገር ቆይቷል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ልዩ ዞኖች እየተካሄደ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ የፖለቲካ ፍላጎትንና ትንተናን ተንተርሶ የሚካሄድ እንደሆነም በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች የሚያካሄዱት ዝቅተኛ ኑሮ ከሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ጀምሮ ሀብት ባላቸውና የፖለቲካ ዓላማ ባነገቡ አካላት ከፍተኛ ገንዘብ እገዛ ጭምር እንደነበር ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ የሚገኘው ወረራ ደግሞ አድማሱን በክልል ደረጃ በማሳደግ ክልሎች በልማት እና በኢንቨስትመንት ስም የአዲስ አበባን መሬት መሻማትና መቀራመት ጀምረዋል፡፡
በቅርቡ ለተለያዩ ክልሎች የባህል ማዕከል ግንባታ፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለልዩ ፖሊስ ኃይል መኖሪያዎች፣ ለባንኮች፣ ለብድር እና ቁጠባ ተቋማት እንዲሁም ለተለያዩ የክልል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አዲስ አበባ ላይ መሬት የማቀራመት ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡
የብልጽግና እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) እንደዚህ አይነት የመሬት አሰጣጥ ሁኔታ በምንም መልኩ ብንወስደው የመሬት ወረራ ሊባል አይችልም ብለዋል፡፡
ለማንኛውም የልማት ሆነ ኢንቨስትመንትን ለሚያስፋፉ ተቋም አዲስ አበባ ላይ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ መሬት መሰጠት ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ከማሰብ እንጂ ወረራ ለማካሄድ እንዳልሆነ ሕብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ እድገታቸውን ለማስፋት የት አካባቢ መስፈር እንዳለባቸው የሚታወቅ በመሆኑ፣ አዲስ አበባ ደግሞ ሁሉንም ብሔረሰብ እና የክልል ነዋሪ የያዘች እንደመሆኗ መጠን ቦታ ይዘው መጠቀማቸው በነዋሪው ላይ ምንም ችግር አያመጣም ሲሉ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ የኹሉም ኢትዮጵያዊ ከተማ ነች የሚሉት ሲሳይ፣ የኹሉም ክልሎች ከተማ ነች፡፡ ስለዚህ ሁሉም ክልሎች አዲስ አበባ ላይ የራሳቸው የሆነ የልማትም ሆነ የኢንቨስትመንት አማራጭ ካላቸው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላይ ማድረጋቸውን እንደ ስህተት መመልከት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ መሆኑ ሌላው መታየት ያለበት፣ አዲስ አበባ የቢዝነስ አማራጭ ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን አድማሳቸውን ማስፋታቸው ትክክል ነው ሲሉ ሲሳይ ይናገራሉ፡፡
በርካታ የክልሎች የልማት ሥራዎች አዲስ አበባ ላይ መሠራታቸው ለከተማዋ ልማት እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች የፈጠሩት አሉታዊ እይታ እንጂ እንደዚህ አይነት ተግባር ፍትሐዊ ክፍፍል መኖሩንም የሚያሳይ መሆኑ መታወቅ አለበት ሲሉ ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ ይገልጻሉ፡፡
በዚህ የመሬት ወረራ ጉዳይ ላይ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልጋል የሚሉት በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የሕግ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ሄኖክ አክሊሉ ናቸው፡፡
አንደኛ፣ የከተማ መሬት እንዴት ነው ወደ ግል ይዞታ የሚቀየረው? ወይንም ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ መታወቅ ይገባዋል ይላሉ፡፡ አሁን ያለው ስርዓት ብናይ ማንኛውም ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎችን/መሬት ለመውሰድ በጨረታ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የቀድሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩትን የኢንጅነር ታከለ ኡማን ሌጋሲ እያስቀጠሉ የሚገኙት አዳነች አቤቤ፣ ሲደረግ የቆየው የከተማው መሬት እንዲወረር የማድረግ ተግባር እንደቀጠሉበት ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በአደባባይ እየተጋለጡ ሲመጡ ጥፋታቸውን ለመሸፈን ሲሉ የተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ በማድረግ የባህል ማዕከል፣ የባንክ እና ሌሎች የልማት ተቋም እንዲሰሩ ቦታ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰብ እና በብሔር ብቻ ተደራጅቶ የመጣውን ወረራ እያካሄደ መሆኑን ለመሸፈንና የክልሎችን ልማታዊ ተግባር በአዲስ አበባ ለመከወን የታሰበ ነው ሲሉ ሄኖክ ይናገራሉ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ለአንዱ ክልል ተሰጥቶ ለሌላው አይከለከልም በማለት የተለያዩ ክልሎችን አዲስ አበባ ላይ በማስፈር ወረራ በሚመስል መልኩ እያደራጁ ነው፡፡ መንግሥት ይህን አደረጃጀት እንደ አንድ የዲሞክራሲ ግንባታ እየተመለከተው ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት የከተማ መሬት ዋና የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ እየተደረገው ነው ሲሉ ሄኖክ ያነሳሉ፡፡ አሁን ባለው የመሬት ስሪት ሁኔታ እንኳን የከተማ መሬት የሚወሰደው በሊዝ ነው የሚለውን ሕግ በተላለፈ አይነት መንገድ እየተሰጠ ነው፡፡ የክልል መንግስታትን ወረራዎች እንኳ ብንተወው፣ የልማትና የኢንቨስትመንት ቦታዎች እንኳን ቢሰጣቸው ይስሩበት አይስሩበት ምንም ሳይረጋገጥ የሚሰጥበት ሁኔታ ነው ያለው በማለት ሄኖክ ተናግረዋል፡፡
ማንም እንደፈለገ ተነስቶ መሬት እየወሰደ ያለበት ሁኔታም አለ፡፡ በርካታ ካሬ ሜትሮችን በጅምላ የመሻማት ሁኔታ ይታያል፡፡ መሬቱን ከወሰዱ በኋላ በተግባር የዋለ ሥራ ሲታይ ግን ምንም አለመኖሩን እያየነው ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ቦታዎችን እንደተፈለገ መስጠት የፖለቲካ መጠቀሚያ ከማድረግ የመነጨ መሆኑን ነው ሄኖክ የሚጠቅሱት፡፡ ይህ ደግሞ ያለውን የሕግ ስርዓት የተከተለ አለመሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው የከተማ ነዋሪዎች ከተማውን በሕገ-ወጥ መንገድ የመውረር ሁኔታ ነበር፡፡ በተለምዶ ሕገ-ወጥ ግንባታ የሚባሉው እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ አገር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ያነሱት ሄኖክ፣ ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሕጋዊ መንገድ እና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ዜጎች በፍትሐዊነት እንዲሁም በእኩልነት መሬት ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ግን የመንግሥት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል ለሕብረተሰቡ የማይተገበር ከሆነ መሬትን በሽሚያ የመውሰድ ሁኔታ እንደሚፈጠር ግልጽ ነው፡፡ ዜጎችን ያለመጥቀም ሁኔታ የሚፈጠረው ደግሞ ከመሬት አስተዳደር አሰጣጥ ጋር በተገናኘ የተፈጠረ ረጅም ጊዜ ሲንከባለል የነበረ ችግር ስላልተቋጨ ነው፡፡ ችግሩ የመሬት አስተዳደር እና የመንግሥት አወቃቀራዊ ሁኔታን የተመለከተ ሥርዓት ባለመኖሩ የተፈጠረ ነው፡፡
የአዲስ አበባ መሬትን በከተማ አስተዳደሩ የበላይ ኃፊዎች በፖለቲካ ስም የመውረር ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ ይህ የመሬት ወረራ ጉዳይ አጨቃጫቂ በመሆኑ ያንን ሚዛን ለመጠበቅ በሚያስመስል አይነት መንገድ ክልል እና ብሔር ተኮር የሆኑ ጉዳዮች እየተነሱ መሬት የመስጠት ሀኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ የመሬት አሰጣጥ ብሔርን መሰረት ያደረገ መሆኑ የሚያሳየው፣ ለሁሉም ክልሎች ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻል እኩልነትን አንጸባርቆ እንደማሳየት የመቁጠር ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡
የአዲስ አበባ መሬት በሕገ-ወጥ መንገድም፣ በሙስናም ሆነ በብሔር መወረሩ ተገቢ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ለከተማዋ ሕዝብ ተጠቃሚነት ማዋል እንጂ ከሌላ አካባቢ የተደራጁ አካላት ወረራ በሚያስብል ደረጃ እየተሻሙ መቀጠላቸው ፍትሐዊነት የጎደለው ነው ሲሉ ሄኖክ አንስተዋል፡፡
በብሔርም ሆነ በክልል ስም የሚሰጡ ቦታዎች ትክክለኛ አካሄድ የተከተሉ አለመሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
እንደዚህ አይነት አሠራሮች በግልጽ የከተማውን ሕዝብ የሚያፈናቅሉ እና በቀጣይ ደግሞ ውጥረት ውስጥ የሚከቱ ናቸው፡፡
ባልደራስ እንደ ፓርቲ ከመቋቋሙ በፊት የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባኛል በማለት፣ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የከተማ የመሬት ወረራ ግልጽ ያደረገበት ሁኔታ ነበር ሲሉ ሄኖክ ገልጸዋል፡፡
ፓርቲያችን አዲስ አበባ ላይ ባለአደራ በመሆን የነበሩ በደሎችን፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለማሳየት ሲጥር እንደነበር ይታወቃል የሚሉት ሄኖክ፣ በዚህም በከተማዋ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ስለ ከተማው ሕዝብ የማያስቡና አግላይ የሆነ ፖሊሲ የሚያራምዱትን በማጋለጥ እና ጥናቶችን በማውጣት የከተማው ሕዝብ የመሬት ባለቤት እንዲሆን ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ ላይ የሚደረጉ ወረራዎችን በተመለከተ በጥናት ያረጋገጥናቸው፣ በእጃችን ያሉ እና በሌሎች ተቋማት የተጠኑ በርካታ ጥናቶች በመሰብሰብ የመንግሥትነት ሥልጣኑን ስናገኝ ፍትሐዊና ተግባራዊ የምናደርገው ጉዳይ አለ ብለዋል፡፡
ሥልጣን እንኳን ካላገኘን የመንግሥት በጎ ፈቃደኝነት ላይ የሚመሰረት እንደሆነ ሄኖክ ጠቁመዋል፡፡
የአሁኑ ባልደራስ ፓርቲ አዲስ አበባ ላይ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸውን፣ በኮንዶሚኒየም እና በመሬት ወረራ ጉዳዮች የሚሳተፉ አካላትን ሲያጋልጥ የቆየ ባለአደራ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ባለአደራነቱን ለጊዜው በማቆየት በምርጫ ሂደቱን በመሳተፍ ላይ የሚገኝ ፓርቲ ሆኗል፡፡
በባልደራስ አማካይነት ሲሰሩ ከቆዩ ጥናቶች መካከል 4ኪሎ፣ ልደታ እና ሌሎች መሀል ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ የተደረገው የማፈናቀል ሂደት፣ የሚገኙበትን ማኅበራዊ ሁኔታ እና የደረሰባቸውን ሥነ-ልቦናዊ ተጽእኖ የዳሰሰበት ጥናት መኖሩ ይታወቃል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢ-ፍትሐዊ ዕደላን አስመልክቶ የተደረገ ጥናት ውጤት በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አማካይነት ባለፈው ዓመት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡
የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ ወጥ እና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታና ፕላን ተሰርቶላቸው ለ3ተኛ ወገን በሽያጭ መተላለፋቸው፣ በማኅበር እና በግል ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጋቸው፣ በምንም መስፈርት የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት እና የነዋሪነት መታወቂያ ማግኘታቸው ፣ በመሬት ወረራው ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች የአርሶ አደር ልጆች ነን በማለትና ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶችና መኖሪያ ናቸው በማለት የሕጋዊ ወረራው ተሳታፊ መሆናቸው እየታየ ያለ ችግር ነው፡፡
ከዛም ባለፈ ወረራ ፈጻማዎቹ በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል የሚሉ ግለሰቦች መሆናቸው፣ ወረራ የተፈፀመባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ኃላፊዎች መሆናቸውን፣ በጠራራ ፀሐይ በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች፤ የፍትሕና ጸጥታ አካላት ተጠሪዎች የተሳተፉበትና ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን እነዚህ አካላት የጉዳዩ ዋና ተዋንያን እንደነበሩ ማሳያም ጭምር ነው፡፡ በተለያየ መልኩ የመንግሥት አመራሮች ሊጠቅሟቸው ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወረው እንዲይዙ መመቻቸቱ፣ የመንግሥትን ሥልጣን ለሕገ ወጥ ተግባር ከለላ እና ሽፋን እንዲሆን መደረጉ፣ ከዚህም ባስ ሲል ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር አመራሮቹ እራሳቸው ወረራውን ፈጻሚ በመሆናቸው፣ በጠቅላላው 213,900 ካ.ሜ. ያህል ስፋት ያለው ቦታ ጥናቱ ባያቸው ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ በሕገ-ወጥ መልኩ መያዙን ይፋ የተደረገበት ጥናት ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ከጋራ መኖሪያ ቤት ጋር በተገናኘም በግልፅ የታየው የመንግሥት አካላት ሕገ ወጥ ተግባር፣ ኢ-ፍትሐዊ ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማውጣት እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችን እና ደንቦችን በማሻሻል፣ ለካቢኔው እና ለከንቲባው በተሰጠ ልዩ ሥልጣን ከንቲባውም ሆነ ካቢኔያቸው ቤቶችን እንደፈለጉ እንዲያድሉ ምክንያት መሆኑ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንጻዎች ውስጥ የተሠሩ የንግድ ቤቶች በተመለከተ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች፣ ልጅ እና የልጅ ልጅ ተብለው በገፍ ስለመታደላቸው፣ በእግር ኳስ ደጋፊነት ስም ለተሰባሰቡ ማኅበራት መከፋፈላቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ተገኝተዋል በማለት ጥናቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ከመሬት ሽሚያው ጋር በተገኛኘ ለክልሎች ለባህል ማዕከልም ሆነ ለተለያዩ ተቋማት የሚሰጥ የአዲስ አበባ ቦታ ማብቂያ እንደማይኖረው ስጋታቸውን ያካፈሉን ነዋሪዎች አሉ፡፡፡ በክልል የነበረው ቀርቶ አሁን አሁን በብሔር መደረጉ ከ80 በላይ ለሆኑ ብሔሮች ተመጣጣኝ ቦታዎች ስለሚያስፈልጉ የእርስ በርስ ፉክክሩ የከተማውን ነዋሪ ወደዳር እንዳያወጣው ይሰጋሉ፡፡ ይህ ስጋታቸውን የሚያቃልል መመሪያም ሆነ ሕግ ባለመኖሩ በአመራሮች ይሁንታ መሆኑ በቀጣይ የከተማዋ መሬት ዕታ ፋንታ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ከባድ ያደርገዋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013



