እነ እስክንድር ነጋ ከተከሰሱበት ክስ ጋር በተገናኘ ዋስትና ሊያስፈቅድላቸው የሚችል ምንም አይነት አዲስ ነገር ስላልመጣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ሊሰጥ አይችልም ብሎ ዐቃቤ ሕግ መከላከያ ማቅረቡን የባልደራስ የሕግና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ ሄኖክ አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቆች ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ክሱ ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት ለዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ እንደተሰጠ ይታወሳል።
በዚህም ረገድ ከዚህ ቀደም የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እና ዕጩዎች ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ፣ አስቴር ስዩም ፣ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሌ በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸው ታስረው መቆየታቸውን ተከትሎ በ6ኛው ምርጫ ዕጩ ሆነው በባልደራስ እንዲቀርቡ መደረጉ ይታወቃል።
በዚሁ መሠረት ዕጩ ሆኖ የቀረበ ሰው እጅ ከፍንጅ በከባድ ወንጀል እስካልተያዘ በስተቀር ያለመከሰስ መብት እንዳለው ሕጉ እንደሚደነግግ የገለጹት ጠበቃው በችሎቱ ዐቃቤ ሕግ ዕጩ ሆነው ከተመዘገቡ በኋላ የሚፈጸም ወንጀልን የሚመለከት ነው ብሎ ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል።
በዚህም ረገድ ዐቃቤ ሕግ እስክንድር ነጋ የሕግ ጉዳይ የአዋጁ ልዩ ተጠቃሚ መሆንን የሚመለከት አይደለም መባሉን ሄኖክ ጠቅሰዋል።
ጠበቃው አያይዘውም እኚህ የፓርቲው መሪ በቅርቡ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዕጩ ሆነው ለ2013 ዓ.ም ምርጫ መወዳደር እንዲችሉ የተወሰነላቸው እንደነበሩ ገልጸዋል ።
ይሁን እንጂ ዕጩ ተወዳዳሪ እስክንድር ነጋ በአሁኑ ሰዓት በእስር ቤቱ ውስጥ ለህይወታቸው፣ ለሥነ ልቦናቸውና ለጤናቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆናቸውን ፓርቲው በተደጋጋሚ ገልጿል ብለዋል ጠበቃው።
ማረሚያ ቤቱ እኚህ ሰው የሕዝብ ተመራጭ ዕጩና የፖለቲካ ከፍተኛ መሪ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለደህንነታቸው አስጊ ባልሆነ ቦታ እንዲያቆያቸው ተጠይቋል።
ከዚህ ባለፈ መሪው ላይ ማንኛውም አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ቢደርስ ከማረሚያ ቤቱ አያያዝ ችግር የሚመጣ በመሆኑ የማረሚያቤቱ አስተዳደር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጠየቅም ፓርቲው አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዕጩ ተወዳዳሪ ቀለብ ስዩም እንደዚሁ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው የገለጸው ፓርቲው ፣ለኹለቱም ዕጩ ተወዳዳሪዎች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቋል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዘዳንት እና ዕጩ የሆነው እስክንድር ነጋ በአዲስ አበባ ቃሊቲ በከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚገኝበት ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል ብሏል ፓርቲው።
የእስክንድር ነጋ አያያዝ ፓርቲው ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ከግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀድሞ ታስሮበት ከነበረው “ዋይታ” ተብሎ ከሚጠራው ዞን በደረሰበት የሰብዓዊ በደል ምክንያት 8ኛ ዞን ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ እንዲዛወር ተደርጓል ተብሏል።
ይሁን እንጂ ከሰሞኑን በተወሰነባቸው ብይን በፊት ከነበሩበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ቂሊንጦ መዘዋወራቸው ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል።
ሆኖም አሁን ታስሮ ባለበት ቦታ በእስረኞች የደህንነቱ ሁኔታ አደጋ ላይ እንደወደቀ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ማረሚያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ለማረጋገጥ ችለዋል ነው የተባለው።
ጠበቃው አክለውም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው አስተያየት ላይ ምላሽ ለመስጠት ለሰኞ ቀን 07 /10/ 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013



