ኢትዮ ቴሌኮም በአጭር የጽሑፍ አገልግሎት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃድ ሰጥቷቸው የነበሩ የ62 ድርጅቶችን ውል ማቋረጡን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
አዲስ ማለዳ ባለፈው ዕትሟ የኢትዮ ቴሌኮም ሥርዓትን ተጠቅመው በሕገ-ወጥ መንገድ የደንበኞችን ብር የሚወስዱ ድርጅቶች መኖራቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ አዲስ ማለዳ በጠየቀችው መሰረት፣ በአሠራር መመሪያው ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን ሳያሟሉ የቀሩ፣ያለ ደንበኞች ፈቃድ መልዕክት የሚልኩ፣ ደንበኞችን የሚያሳስት መልዕክት የሚልኩና ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጭ መልዕክት የሚልኩ ድርጅቶች እንደነበሩ ገልጿል።
የአሠራር መመርያን በመተላለፍ ለደንበኞች የስልክ መልክዕክት የሚልኩ ድርጅቶች ሲገኙ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ መልዕክት እንዳይልኩ በጊዜያዊነት ማገድና የገንዘብ ቅጣት መወሰን፣ በተደጋጋሚ ጥፋት የተመዘገበባቸውና ከባድ ጥፋት ያጠፉ ድርጅቶች ሲሆኑ ደግሞ ዉል እስከመሰረዝ የሚያደርስ ቅጠት እንደጣልባቸው የኢትዮ ቴሌኮም የአሠራር መመሪያ እንደሚያዝ ተጠቁሟል።
በዚሁ አግባብ ኢትዮ ቴሌኮም ከተፈቀደላቸው አሠራር ሥርዓት ውጭ ተገቢ ያልሆነ ተግባራትን የፈጸሙ ድርጅትችን በአሠራር መመሪያው መሠረት መቅጣቱን አስታውቋል።
በዚህ ዓመት 10 ድርጅቶች ደንበኞችን የሚያሳስት መልዕክት በመላካቸው የሚጠቀሙበት ቁጥር ኮንትራት መሰረዙን ኢትዮ ቴሌኮም ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። እንዲሁም፣ ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጭ የተጠቀሙ ሦስት የኢትዮ ቴሌኮም አጋር ድርጅቶችን ኮንትራት ማቋረጡንም ገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከሕግ ውጭ ሲሰሩ ያገኛቸውን ድርጅቶች በመጀመሪያ ቅጣት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለሦስት ቀናት አገልግሎቱን በማቋረጥ ለማስተካከል የሚሞከር ሲሆን፣ በኹለተኛው ጊዜ ሲሆን ደግሞ ቅጣቱ የ25ሺሕ ብርና ለአምስት ቀናት አገልግሎቱን ማቋረጥ ያካትታል። በሦስተኛው የቅጣት ሂደት ደግሞ የ50ሺሕ ብርና ለ15 ቀናት አገልግሎት እንዲቋረጥ ይደረግና ይህ ቅጣት ውጤታማ ካልሆነ አራተኛው እና ዉል የማቋረጥ ቅጣቱ ተግባራዊ ይሆናል ሲል ለአዲስ ማለዳ በሰጠው ምላሽ ጠቁሟል።
በዚሁ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም እስከ አሁን በ263 ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የገለጸ ሲሆን፣ ለ199 ድርጅቶች የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ16 ድርጅቶች ኹለተኛውንና ሶስተኛ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል። በተቀመጠው የቅጣት መመርያ መሰረትም 980 ሺሕ ብር ሰብስቢያለሁም ብሏል። የ13 ድርጅቶች ዉል እንዲሰረዝና የ35 ድርጅቶች የሚሰጡት አገልግሎቱ በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ አድርጌለሁ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በአጠቃላይ ከ2011 ጀምሮ ከ62 አጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ከሚጠቀሙ አጋር ድርጅቶች ጋር ዉል ማቋረጡን ገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች አንዳንድ ጊዜ ብራቸው ያለ አግባብ እየተወሰደባቸው እንደሆነ ቢያውቁም ማን እንደወሰደው አያውቁም፣ ኢትዮ ቴሌኮም ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን ያደርጋል?
አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ዕትሟ በሠራችው ዘገባ ላይ አጭር የጽሑፍ መልዕክት የሚጠቀሙ ድርጅትች የደንበኞችን ሂሳብ ያለ አግባብ እንደሚቀንሱ ገልጻ ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም በሰጠው ምላሽ “ኢትዮ ቴሌኮም የሲስተም አሰራር በመዘርጋት [SDP System] የሞባይል ተጠቃሚዎች ካለ ፍቃዳቸው ገንዘብ እንዳይቆረጥባቸው ተደረጓል። ከግንቦት 2011 ጀምሮ ሲስተሙ ተግባራዊ ሆኗል። በአሁኑ ግዜ ያለፍላጐታቸው የሚቆረጥ ገንዘብ አይኖርም” ብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም እነዚህ አጭር የመልዕክት ሳጥን ቁጥሮች የሚሰሩትን ሥራ ትክክለኝነት እንዴት እንደሚቆጣጠር ከአዲስ ማለዳ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ የሙከራ ቁጥሮችን በመጠቀም እንደ ደንበኛ ሆኖ በመመዝገብ በአጭር ኮድ ቁጥሮች የሚሰጡ አገልግሎቶች መገምገምና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት የታየባቸው ቁጥሮች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤና ቅጣት እንዲከፍሉ በማድረግ ነው ብሏል።
በኢትዮ ቴሌኮም ሥርዓት ሥራቸውን ለመከወን ሲስማሙ በትክክል ለተመሰረቱበት ዓላማ እየተጠቀሙ መሆኑን፣ በየጊዜው የአገልግሎት አሰጣጥ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግ እና ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጭ ሲጠቀሙ የተገኙትን ወይም ጥራታቸውን ያልጠበቁ መልዕክቶች የሚያስተላልፉት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013



