የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ለ638 ኢንዱስትሪዎች 891 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ብድር መስጠቱን አስታወቀ። ባለሥልጣኑ 891 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጅያ ብድር እንዲመቻች ያደረገው በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሲሆን፣ ከባለፈው 2012 ተመሳሳይ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ24 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል። የዘንድሮው አፈጻጸም የብድር ተጠቃሚ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች 638 ሲሆኑ፣ የባለፈው ዓመት የሥራ ማስኬጃ ብድር ያገኙ ኢንዱስትሪዎች 935 ናቸው። ይህም በዘንድሮው በጀት ዓመት የብድር ተጠቃሚ ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲነጻጸር የ297 ቅናሽ አሳይቷል።
ባለሥልጣኑ በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለ828 ኢንዱስትሪዎች 869 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ብድር ለማቅረብ በዕቅድ ይዞ ነበር። አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ ባለሥልጣኑ ለ828 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች 869 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጅያ ብደር ለማቅረብ ነበር። ይሁን እንጅ ለብድር አቅርቦት ተይዞ የነበረው በጀት ጭማሪ ሲያሳይ፣ ባንጻሩ የብድር ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ብዛት ቅናሽ ታይቶበታል።
በሌላ በኩል የባለስልጣኑ የ2013 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም እንደሚያሳየው ከሆነ፣ አዲስ ኢንዱስትሪዎችን ከማቋቋም አኳያ ባለስልጣኑ 2 ሺሕ 94 ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋማ እቅድ ይዞ 2 ሺሕ 84 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተቋማትን መፍጠሩን ያመላክታል። አዲስ የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ለ31 ሺሕ 233 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ ኢንዱስትሪዎችቹ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት ለ22 ሺሕ 774 ዜጎች ብቻ ነው።
በበጀት ዓመቱ አዲስ የተቋቋሙት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ819 ኢንዱስትሪ እድገት አሳይቷል። በ2012 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች 1 ሺሕ 265 ሲሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ አዲስ በተቋቋሙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የተፈጠረው የሥራ እድል 15 ሺሕ 533 ነበር።
አዲስ የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎችን በክልል ደረጃ በዝርዝር ያስቀመጠው የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል 210፣ በአማራ ክልል 101፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 119፣ በኦሮሚ ክልል 1401፣ በሲዳማ ክልል 102፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 52፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 2፣ በጋምቤላ ክልል 12፣ በሐረር 3፣ በአፋር ክልል 82ና በሶማሌ ክልል 6 መሆኑን ያስረዳል።
አዲስ የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች በክልል ደረጃ ለዜጎች የፈጠሩት የሥራ እድል፣ አማራ ክልል 2 ሺሕ 927፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል 1 ሺሕ 610፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2 ሺሕ 375፣ ኦሮሚያ ክልል 13 ሺሕ 621፣ ሲዳማ ክልል 1 ሺሕ 9፣ ጋምቤላ 103፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 684፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 12፣ ሐረር 15ና አፋር ክልል 391 መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013



