የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በክልሉ በ2009 ተጀምረው በ2010 በተከሰተው የግንባታ ግብዓት የዋጋ ንረት ምክንያት ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ ሸዶችን በተጨማሪ በጀት እያስገነባ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ። በ2009 በክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተጀምረው በ2010 በተከሰተው የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ንረት ምክንያት የግንባታ ሂደታቸው ተቋርጦ የነበረው ዘመናዊ የማምረቻ ሸዶች በአዲስ መልክ ጨረታ በማውጣት እንዲገነቡ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ናትናኤል ሚሊዮን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በወቅቱ በግንባታ ግብዓቶች ላይ እስከ 15 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ በክልሉ ግንባታ ላይ የነበሩ 14 የማንፋክቸሪን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሸዶች ግንባታ ቆሞ እንደነበር ሥራ አሥፈጻሚው ጠቁመዋል። ሸዶቹን ለመገንባት ኮንትራት ወስደው የነበሩ ድርጅቶች በወቅቱ በነበረው የግንባታ ግብዓት የዋጋ ንረት ቀድመው ከገቡት ውል የ15 በመቶ ጭማሪ ቢደረግላቸውም፣ እንደማያዋጣቸው በመግለጽ ሸዶቹን ለመገንባት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተመላክቷል።
በመሆኑም ሸዶቹ ባሉበት ሁኔታ እንዲቆሙ የተገደዱ ሲሆን፣ የክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሸዶቹን ግንባታ ለማስቀጠል አዲስ ጨረታ ለማውጣት ተገዷል። በዚህም ግንባታቸው ተጀምሮ ለቆሙ ሸዶች ቀድሞ ተይዞላቸው ከነበረው በጀት ተጨምሮ ግንባታቸው እየተከናወነ ነው ተብሏል። አንዳንዶቹ ሸዶች በአዲሱ ጨረታ መሰረት እስከ 50 በመቶ ቀድሞ ከተያዘላቸው በላይ ተጨማሪ በጀት መጠየቃቸውን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በ2009 ግንባታቸው የተጀመረ ሸዶች በወቅቱ ተይዞላቸው የነበረው በጀት በአማካይ ለአንድ ሸድ ግንባታ ከስምንት እስከ 13 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ፣ አዲስ በወጣው ጨረታ ደግሞ የአንድ ሸድ ግንባታ ዋጋ በአማካይ ከ13 እስከ 15 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ነው የገለጹት።
ግንባታቸው ተቋርጦ የቆዩ ሸዶችን ግንባታ ለማስቀጠል ተጨማሪ በጀት ቢያስፈልግም፣ ባሉበት ከሚቆሙ ይልቅ ተጨማሪ ወጪ ተደርጎባቸው ተጠናቀው ወደ ሥራ ቢገቡ የተሻለ መሆኑን በማመን ኮርፖሬሽኑ ግንባታውን እንዳስቀጠለም ተመላክቷል። አዲስ በወጣው ጨረታ መሰረት ሆሳዕና፣ ዱራሜ፣ አርባ ምንጭ፣ አመያ፣ ጂንካና ወራቤ ላይ የሚገነቡ ሸዶችን ዳግም ሥራ ለማስጀመር ኮርፖሬሽኑ ከኮንትራክተሮች ጋር ውል ተፈራርሞ ወደ ሥራ በማስገባት አሁን ላይ ግንባታው በሂደት ላይ ነው ተብሏል። በግንባታ ላይ የሚገኙት ሸዶች ከአራት አስከ ስድስት ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተጠቁሟል።
በግንባታ ላይ የሚገኙት ሼዶች ሲጠናቀቁ ከ40 በላይ የማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ስራ እንዲጀምሩ እንደሚያስችሉ ተገልጿል። በግንባታ ግብዓት የዋጋ ንረት ተቋርጠው ከነበሩት 14 ሼዶች ውስጥ 2 ባለፈው ሳምንት ግንባታቸው ተጠናቋል። አንደኛው ከ 20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የሀላባ ማኑፋክቸሪንግ ሸድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያካተተው ነው ተብሏል። ኹለተኛው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የቡታጅራ ማኑፋክቸሪንግ ሸድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ሥራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013



