በአዲስ አበባ ከተማ ከኹለት ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞችን በማሰማራት አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን የሕብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶች እና በጎ ፍቃደኞች ማስተባበሪያ ቢሮ የበጎ ፍወቃደኞች ዳይሬክተር አክሊሉ ትእዛዙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዘንድሮው አመት የክረምት መርሃ ግብር ላይ ኹለት ሚሊዮን በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ አምስት መቶ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ በጉልበት፣ በእውቀት እና በቁሳቁስ ማዳን ይቻላል ተብሏል። ተግባሩ በበጎ ፍቃደኞች እና በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነጻ ድጋፍ ብቻ እንደሚከናወን የገለጹት አክሊሉ፣ ከመንግስት ምንም አይነት ድጋፍ ወይንም በጄት እንዳልተመደበ አስረድተውናል።
ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦችም ቢሆኑ ነጻ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ያላቸውን ገንዘብ፣ ጉልበት እና እውቀት ከማጋራት ውጪ ምንም አይነት ክፍያ እንደሌላቸው አንስተዋል። የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመዲናዋ አዲስ አበባ ተግባራዊ በማድረግ አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ማድረግ ከተጀመረ በርካታ አመታትን ማስቆጠሩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ እየተሰማሩ ያሉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ አገልግሎቱን ይበልት ማስፋት እንደሚገባ እና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን መሥራት እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል። በዘንድሮ የክረምት ወቅት በተለያዩ የሥራ መስኮች በጎ ፈቃደኞችን ለማሰማራት በቂ ዝግጅት መደረጉን ያሳወቁት አክሊሉ፣ “በጎ ፍቃደኝነት በመደጋገፍና መግባባት” በሚል መሪ ቃል እንደሚከናወን ነግረውናል። ቆይታውም ከሰኔ 30 እስከ መስከረም 30/2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በፕሮግራሞቹ ውስጥ በዋናነት የሚከናወኑ ተግባራት አስራ ስድስት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ከነዚህም ውስጥ በዋነኝነት የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ማደስ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን መደገፍ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረግ በተለይም ማዕድ ማጋራት፣ አዲስ አበባን ውብ እና ጽዱ ማድረግ፣ በክረምት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋን መከላከል፣ የትራፊክ አገልግሎት መስጠት፣ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን እና የኮሮና ቫይረስ ፕሮቶኮልን ማስጠበቅ በበጎ ፍቃደኞች ከሚከናዋኑ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አያይዘውም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የሚወጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ከመሄዳቸው በፊት ሙሉ በሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ የሚሟላበት መርሃ ግብርም ይኖራል ሲሉም ተናግረዋል። አክለውም ወጣቶች ስለ አገራቸው ታሪክ እና ባህል እንዲያውቁ ለማስቻል የዩኒቨርስቲ ምሁራን እና ታዋቂ ሰዎች በክረምቱ በጎ ፍቃድ አገልግሎት እውቀታቸውን እንዲያጋሩ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን አክሊሉ አብራርተዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013


