ሰሞኑን ወደ መተከል ዞን የተመለሱ ተፈናቃዮች የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው ገለጹ

0
1025

ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል በቻግኒ ራንች መጠለያ ጣቢያ የነበሩ የወምበራ፣ የድባጤ፣ የቡለንና የጉባ ወረዳ ተፈናቃዮች ወደ ዞኑ ቢመለሱም በሰፈሩበት ካምፕ የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በመተከል ዞን የተፈጠረውን የጸጥቻ ችግር ተከትሎ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ ተፈናቃዮች ከሚገኙበት የቻግኒ ራንች መጠለያ ጣቢያ ወደየወረዳቸው የተመረጡ ስፍራዎች የመመለሱ ሥራ በጥንቃቄ እየተሠራ መሆኑን ነው። ኮማንድ ፖስቱ ተፈናቃዮች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚሰጣቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል። ኮማንድ ፖስቱ እንዳስታወቀው ወደ ዞኑ የተመለሱ ተፈናቃዮች የሚሰፍሩት በየተፈናቀሉበት ወረዳ ነው ብሏል።

ከዞኑ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ተጠልለው የቆዩ ዜጎች ወደ ዞኑ መመለሳቸው ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ አሁን ላይ የሰፈሩበት ካምፕ ከጸጥታ ስጋት ነጻ አለመሆኑን እና አሁን ባሉበት ሁኔታ መሰረታዊ ሁኔታዎች እንዳልተሟሉላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ተመላሾች መካከል ከቡለን ወረዳ ተፈናቅለው አሁን ላይ ተመልሰው በካምፕ የሚገኙ ዜጎች ይገኙበታል። በቡለን ወረዳ በተመረጡ ካምፖች ሰሞኑን የተጠለሉ ዜጎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ቡለን ወረዳ ላይ መጠለያ ካምፕ ቢኖርም ጉዳዩን ለአዲስ ማለዳ እስከገለጹበት ስዓት ድረስ የውኃ አቅርቦት እንደሌለ ጠቁመዋል።

ሰሞኑን ቀድሞ ወደሚኖሩበት ወረዳ ተመልሰው በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ በቻግኒ ራንች መጠለያ ከነበሩት ተፈናቃዮች መካከል በዞኑ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን ባለማመናቸው በራሳቸው ፈቃድ ቻግኒ ላይ የቀሩ መኖራቸውን ነው። “ወደ ሞት አንሄድም ብለው የቀሩ አሉ” ሲሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከተፈናቃዮች ለመረዳት አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

በስጋት ውስጥ ሆነው ሌሎች ተፈናቃዮች ሲመለሱ በራሳቸው ፈቃድ ባሉበት የቀሩ ተፈናቃዮች የሚደረግላቸው ድጋፍ እንደሌለ እና በአማራ ክልል ቻግኒ አሁን ላይ ምንም አይነት ድጋፍ እንደማይደረግ አዲስ ማለዳ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስተባብሩ አካላት ሰምታለች። ወደ መተከል ያልተመለሱ ተፈናቃዮች በስጋት ቢቀሩም፣ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ እስከሚሆንና ተረጋግተው መመለስ እስከሚችሉ ድረስ ባሉበት ድጋፍ ሊደረግላችው እንደሚገባ አስተባባሪዎቹ ጠቁመዋል።

ተፈናቅለው የነበሩና ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ አስተማማኝ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል። ተፈናቃዮች በጊዜያዊነት በሚያርፉበት አካባቢ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በትኩረት እንደሚሠራ የሚናገረው ኮማንድ ፖስት፣ በዋናነት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በቀጠናው የዜጎችን ሞትና መፈናቀልን ማስቆም፣ ከዞን እስከ ቀበሌ መዋቅራዊ ሽግሽግ ማድረግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ማመለስና መልሶ ማቋቋም መሆኑንም ጠቁሟል።

በዞኑ አሁንም ድረስ የጸጥታ ችግሩ እንዳልተቀረፈ የሚገልጹት ተመላሾቹ፣ ኮማንድ ፖስቱ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸውን የካምፕ አከባቢዎች በንቃት መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል። በሌላ በኩል፣ ተፈናቃዮች ወደ ተፈናቀሉበት ወረዳ ቢመለሱም በዞኑ ያለው የጸጥታ ችግር አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ በአንድ ላይ ተከማችተው በካምፕ ውስጥ ከመኖር ውጭ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰው የእርሻ ሥራ መሥራትና መንቀሳቀስ አይችሉም። በዚህም ምክንያት ተፈናቃዮች በሰፈሩበት አካባቢ ያልታረሱ መሬቶችን በጋራ እንዲያርሱ ዕቅድ ቢኖርም፣ የጋራ እርሻ ከመሆኑ በላይ ለውጥ የማያመጣ መሆኑን ተፈናቃዮች ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here