ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጃትን ለመከለስ አማካሪ መቀጠሩ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የሰበሰባቸው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጃት እና አቀራረብ ደረጃዎች (ኢንተርናሽናል ፋይናንሺያል ሪፖርቲንግ ስታንድርድ( IFRS)) መረጃዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የክለሳ ሥራ ሊሠራ ነው ተባለ።
ክለሳ የሚደረግባቸው 30 የተለያዩ ተቋማት ሲሆኑ፣ አመታዊ የሒሳብ መግለጫዎቻቸው ላይ IFRSን በሚፈለገው መንገድ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ የሚሠራ ነው ሲሉ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አበበ ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እነዚህ 30 ተቋማት የተመረጡት ከ180 የተለያዩ አሪቷ ላይ ካሉ ኹሉም ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አሥተዳደር ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸው ተቋማት እና ትልልቅ ንግድ የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች ውስጥ መሆኑ ታውቋል።
በቦርዱ በኩል አልፎ ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር የተላከው የ2010 ዓመታዊ ሪፖርት በየትኛው ባለሙያ የተሠራ ነው? ምን አይነት የሂሳብ ደረጃ አለው? እንዲሁም የሒሳብ ሥራው ምን ያህል ግልጽ ነው? በማለት የክለሳ ሥራው ተግባራዊ ይደርጋል ተብሏል።
ሥራወ ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ በማሟላት የተደረገው የሒሳብ ሥራ በትክክል መተግበሩን፣ ትክክለኛ መረጃ መያዙንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን መጠበቁን የሚያረጋግጥ መሆኑም ታውቋል።

ይህን ትክክለኛ የሒሳብ አያያዝ ማረጋገጥ በዋናነት የውጭ ኢንቨሰትመንት ወደ አገር ውስጥ አንዲገባ ለማድረግ ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የውጭ ንግድ ተቋማት አገር ውስጥ ካሉ ባለሃብቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን መንገድ ይከፍታል ሲሉ አበበ ገልጸዋል።

ቦርዱ ይህን የክለሳ ሥራ የሚሠራው እንደ አንድ ትልቅ እቅድ በመያዝ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበር ነው ተብሏል። ቦርዱ በራሱ አቅም ብቻ የክለሳ ተግባሩን ማከናወን ባለመቻሉ ምክንያት ከተቋሙ ውጭ ባሉ ባለሙያዎች እና እውቀት ባላቸው ሰዎች ለመሥራት ዝግጅቱን አጠናቋል። ይህን ተከትሎ ለዘጠኝ ወር በሚቆይ የኮንትራት ውል መሰረት አማካሪ መቀጠሩ ታውቋል። ይህ አማካሪ ይህንን ሥራ ለመሥራት በወር 1500 ዶላር ማለትም በአጠቃላይ ለዘጠኝ ወር በ590ሺሕ ብር እንደሚከፈለው አበበ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ይህንን የክለሳ ሥራ ለመሥራት የተገኘው ወጪ የሚሸፈነው የዓለም ባንክ ለቦርዱ ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ክለሳ የተሳሳተ የሒሳብ መረጃ ከተገኘ የተገኘበት ተቋም በ30 ቀን ውስጥ አስተካክሎ እንዲያስገባ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል። የገቢዎች ኦዲት የማስተካከያ ጊዜ 5 ዓመት በመሆኑ ይህ የቦርዱ የክለሳ ተግባር የተበላሹ ሪፖርቶችን በጊዜ እንዲያስተካክሉ ያግዛል ብለዋል።

የተቋማት ሪፖርት ወደ ቦርዱ በመጨረሻ ሰዓት የሚገቡ በመሆናቸው እና ተቋሙ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ስለ IFRS በቂ ዕውቀት ስለሌላቸው በጊዜ ክለሳ ለማድረግ አልተቻለም ሲሉ አበበ ገልጸዋል። መንግሥት የአገሪቱ የሒሳብና የኦዲት ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው መለኪያ (ስታንዳርድ) እንዲመራ በማሰብ፣ ይህንኑ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሪፖርት አደራረግ ሥርዓት እንዲከተሉ የሚያደርግ ሥርዓት መተግበር ጀምሮ ነበር።

ይህንኑ ሥራ የሚመራ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ IFRS በኢትዮጵያ እንዲተገበር በ2007 በጸደቀው አዋጅ መሰረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተቋቁሞ የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ሥርዓቱን ሲከታተል ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የዓለማችን አገራት IFRSን የተቀበሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 13ቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው።

IFRS በፈረንጆቹ 2001 በዓለም አቀፍ የአካውንቲንግ ደረጃዎች ቦርድ (ኢንተርናሽናል አካውንቲንግ ስትንደርድ ቦርድ (IASB)) ተቀባይነት ያገኘ የሒሳብ ሥርዓት ሲሆን፣ ጥራት ያለው የሒሳብ ሪፖርት ለማቅረብ የተመቸ፣ እንዲሁም ንግድ እና ኢንቨስትመንትን የሚፈጥር የፋይናንስ መረጃ አቀራረብ ሥርዓት ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here